Tuesday, February 9, 2016

"የፍቅር ምርጫዬ" የEBS ፕሮግራም ጉዳይ ሲቀጥል ?!?

(መላኩ አላምረው)
...
ጎበዝ !... የፍቅርን ሕይወት በትክክል መኖር ባንችል እንኳን ትርጉሙን አዛብተን በመረዳት ለትውልዱም የተሳሳተ ግንዛቤ ለመስጠት ባንደክም አይሻልም ? "ፍቅር" እንኳን ሳይተያዩ ተያይቶና ተጠናንቶም በሥጋ ስለተዋደዱ ብቻ ዘው ብለው የሚገቡበት ሕይወት አይደለም። የሰው ልጅን ሦስት ባሕርያት መግባባትና መዋሐድ ከሚጥይቁ ነገሮች አንዱና ዋናው ፆታዊ ፍቅር ነው። የስሜት (በአጠቃላይ የስሜት ህዋሳት) የአዕምሮ እና የመንፈስ። በእነዚህ ነገሮች ለመግባባት ደግሞ ምን ያህል ጊዜና ትኩረት ሊጠይቁ እንደሚችሉ ለመገመት አያዳግትም፡፡
……………….
የሰሞኑን ebs "የፍቅር ምርጫዬ" ፕሮግራም አስተያየት ተከታትላችሁ ከሆነ... ቴሌቪዥን ጣቢያው ምን መልእክት ማስተላለፍ እንደፈለገ ግልጽ ነው። "ምንም በሉ ምን እንቀጥላለን" አይነት ነው። ምክንያቱም የመጨረሻው አስተያየት "በርቱ" የሚል ነውና። ይህንንማለት ፕሮግራሙን መቀጠል መብታቸው ነው። እኔም ትዝብቴን እየጻፍሑ መቀጠል መብቴ ነው።
({J> በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጽፌው ከነበረው የግል አስተያየት ጋር በተያያዘ ለምን ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› ፕሮግራምን እንደምቃወም ebs ቴሌቪዥን ጋር ረዘም ያለና የተላዘበ ቃለ መጠይቅ አድርጌ ነበር። ነገር ግን የተቆራረጡ ደጋፊ አይነት ሃሳቦች ተመርጠው ነው የቀረቡት። ወይ ሚዲያዎቻችን... ግርምምም ይሉኛል:J))
ቃለ መጠይቁ ላይ የቆርጦ መቀጠል ሥራው (Editing) በተቃውሞ ጎራ የተሰለፍን ተጠያቂዎችን መልእክት ጭብጡን እንዳሳጣው ከእኔ በላይ ምሥክር የለም። ለአንድ ሀሳብ መነሻ ሳይኖረው መደምደሚያ የለውም፡፡ አንድ አካል የአንተን መነሻ አመክንዮ ቆርጦ መደምደሚያህን ወይም መድረሻ ሃሳብህን ትቶ መነሻ ምሳሌዎችህን ካቀረበው ምን ያህል መልእክትህ እንደሚዛባ ደርሶብህ እየው፡J)
………
›) ለማንኛውም ለማኅበራዊ ድረ-ገጽ አንባብያን በፕሮግራሙ ዙሪያ በአመክንዮ የተመሠረተ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ለማድረግ ግልጽ ውይይት ማድረግ ግድ ነውና በዚያው በቃለ መጠይቁ አንስቻቸው የ‹ኤዲተሩን› መቀስ ማለፍ ስላልቻሉ ያልተሰተናገዱ እና እንዲሁ ብንወያይባቸው ይጠቅማሉ የምላቸውን አንዳንድ ተጨማሪ ነጥቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁ። (ቴሌቪዥኑ ቢቆራርጠውም ማንም የማይቆርጥብኝ በእጄ ያለ መድረክ ላይ ነኝና)

1. ስለ ፕሮግራሙ ርዕስ እና ይዘት...
ለእነርሱም በግልጽ እንደነገርኋቸው... በእኔ እምነት "ፕሮግራሙ የማይመጥነውና የማይስማማው" ርዕስ ነው የያዘው። "የፍቅር ምርጫዬ" ብሎ ሳይተያዩ (በደንብ ሳይተዋወቁ) መመራረጥ የለም። ቢኖርም ስህተት ነው። እርግጥ ነው በሥጋ ዓይን የማያዩ ሰዎችም የፍቅር አጋራቸውን ይመርጣሉ። ነገር ግን በሕሊናቸው ዓይተውና በሚያዩ ሰዎችም አሳይተው እንጅ እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። "ባዶ እጄን ከምሄድ፣ ብቻዬን ከምኖር..." ብለውም አይደለም። የሀገራችን የጋብቻ ባህል ከቦታ ቦታና የሚለያይበት ነገር ቢኖረውም… "ልጆች ሳይተዋወቁ ነው የሚጋቡት" ከምንላቸው ጋብቻዎች ጀርባ ትልቅ የሆነ የወላጅና የማህበረሰብ ትውውቅና ለልጅ አሳቢነት የሚታይበት በጥንቃቄ የተሞላ አመራረጥ ነው ያለው ዝም ብለን በኋላ ቀርነት የምንነቅፈውና ልናርመው የምንሮጥ ባህል የለንም። ማረም ያለብን ይልቅ ከየትም ሀገር ያየነውን ኮርጀንና ከሀገራችን ባህልና ወግ ጋር መሄድ አለመሄዱን ሳናስተውል ለሚዲያ የምናበቃውን ነገር ነው። እናም ፕሮግራሙ የግድ እቀጥላለሁ ካለ ወይ ስሙን ወይ ይዘቱን ይቀይር። እኔ በግል ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› የሚል ስም የያዘ ፕሮግራም አይኑር አልልም፡፡ አሁን በሚቀርብበት መልኩ ግን ላየው አልፈልግም፡፡

2. የሕዝባችን አዲስ ነገርን የመቀበል ጉዳይ...
ስለ ፕሮግራሙ ያለው አንዱ የአዘጋጆች እይታ ይህ ነው። "ሕዝቡ አዲስ ነገርን የመቀበል ልምዱ ደካማ በመሆኑ ነው የሚቃወመን" የሚል። ለዚህም በትላንቱ የአስተያየት ፕሮግራም "ለቴክኖሎጅ" የተጠቀሰውን ሀገርኛ ምሳሌ... ምንም አዲስ ላልሆነው ለዚህ የማስተዋወቅ (በዘመንኛ አጠራር ለማጣበስ) ፕሮግራም በመጥቀስ "ሕዝቡ አዲስ ነገርን መቃወሙ አዲስ ነገር አይደለም" የሚል ድምዳሜ እንዲያዝ ለማድረግ ተሞክሯል። ያው ምንም ይባል ፕሮግራሙ ይቀጥላል አይነት መልእክት ለማስተላለፍ ነው። እኔ (ለቃለ መጠይቅ አድራጊውም በግልጽ የነገርሁት) ይህ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ለሀገራችን አዲስ አይደለም። አዲስ ነገር አመጣን ብለን "ሕዝቡ አዲስ ነገርን የመቃወም ልማድ ስላለው ነው የሚቃወመን" የሚል ራስን መደለያ ሃሳብ መያዝም መሳሳት ነው። ሕዝቡ ሲቃወማቸውና የሰይጣን ሥራዎች ናቸው ሲላቸው የነበሩ (ለምሳሌ የሚኒልክ ዘመን ወፍጮ፣ የቧንቧ ውሃ፣ ስልክ፣ መኪና...) ለሀገሩ እንግዳ ለሕዝቡ ባዳ የነበሩ አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች ናቸው። እነርሱንም ቢሆን ጥቅማቸው ሲገባው ተላመዳቸው... እንዲያውም አብዝቶ ፈለጋቸው እንጅ ተቃውሟቸው አልቀረም።
እርግጥ የእኛ ባህልና ሃይማኖት አዳዲስ ነገሮችን እንዳንቀበል ተጽእኖ ያደርጉ እንደነበረ ታሪክ ምሥክር ነው፡፡ አሁንም ድረስ የሚስተዋል ሀቅ ነው፡፡ ይህ "የፍቅር ምርጫዬ" ብሎ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ግን ለሀገራችን አዲስ አይደለም። (አዲስ ሆኖ ነገር ግን ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ከሆነ ማንም ሊያስቆመው አይችልም)፡፡ ግን አይደለም፡፡ ወላጅ ለልጅ አጭቶ በሚያጋባበት ማህበረሰብ ዘንድም እንኳን አባቶቻችን "ማስተዋወቅ" የሚለውን በመረዳት በኩል የተሻሉ ነበሩ። ልጃቻቸው ከማግባተቸው በፊት (በድብቅም ቢሆን) እንዲተያዩ ያደርጋሉ። ልጆች ባይተዋወቁም ወላጆች በደንብ ያውቋቸዋል። ወላጅ ለልጁ የሚበጀውን ለመምረጥ ብዙ ይደክማል።
ይህ ፕሮግራም ግን "ባለመተያየት ነገር ግን አዘጋጆች በሚያወጧቸው ውስን የጥያቄ መልሶች ለፍቅር አጋር መምረጥ" የሚልና "ሰውን ከሸቀጥም በታች ማድረግ" ነው። ሸቀጥን እንኳን ስንመርጥ በደንብ አይተን ወደን እንጅ በሰማነው ብቻ አይደለምና። ይህ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራ ካለበት በጋብቻ አማካሪዎች በኩል ቢሠራ፡፡ እንጅ በሚዲያ ያውም በቴሌቪዥን ለመቅረብ ሀገሩ ኢትዮጵያ አይደለችም፡፡ የሚቀርብበትን ሀገር ይፈልግ፡፡ አይ እምቢ ካለ ግን መብቱ ነው፡፡ ነጻነት እንደዚህም ነውና፡፡

3ኛ. ስለ ባህል መሻሻል/ማደግ/መጥፋት…
አንደኛው የፕሮግራሙ ደጋፊዎች እይታ ይህ ነው፡፡ ባህላችን ለዚህ ፕሮግራም ባይመችም ባህል በራሱ የሚሻሻል/የሚያድግ ነገር በመሆኑ ቆመን ለመቅረት አንከራከር የሚል፡፡ ይህኔ ነው ማፈር ! ገና ለገና ባህል ሊያድግ/ሊለወጥ/ሊጠፋ/ሊሸጋገር የሚችል ነገር ነው ተብሎ እንዲህ ይባላል ? ዛሬ ላይ መነጋገር ያለብን እኮ ስለ ዛሬ/አሁን ነው፡፡ ነገን ማንም አያውቃትምና፡፡ ይህ ፕሮግራም ከአሁኑ ባህላችን አፈንግጧል ካልን በቃ ፍርጃው አሁን ነው፡፡ አይ ችግር የለበትም ካልንም ከአሁኑ የሀገራችን ነባራዊ የባህልና ወግ ሁኔታ አንጻር አይተንና አሳይተን ነው፡፡ ይህ የአሁኑ ባህላችን ነገ መቀየሩ ስለማይቀር አስቀድመን የፈለግነውን ሁሉ ለማድረግ አይከለክለንም ካልን በእውነት ተሳስተናል፡፡ ደግሞም ቆመው መቅረት (አለመለወጥ አለመሻሻል) ያለባቸው ጠቃሚ ባህሎች ካሉ በሙሉ ህልውናቸው ቆመው መኖር አለባቸው፡፡ የእኛን ጠቃሚ ባህል እየጣልን የሌላን ስናሳድድ ነው ራሳችንን ሳንሆን የምናልፈው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ሁኔታ ከሀገራችን የከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተቀይሯል፤ እናም ለ‹‹ፍቅር ምርጫዬ›› ዓይነት ፕሮግራሞች ምቹ ሁኔታዎች አሉ እያልን ከሆነ እንግዲህ የባህሉ ባለቤት ሕዝቡ ይፍረድ፡፡
እኔ በግል ከፕሮግራሙም ሆነ ከአዘጋጆቹ ጠብ የለኝም/አንተዋወቅምም፡፡ የሕዝቡ አካል እንደመሆኔ ግን ሕዝቡ የሚቀበለውንና የማይቀበለውን (አማራጭ አጥቶ ዝም ስላለ ተቀበለ ማለት አይደለም) አውቃለሁና ተቃውሞውን በአቅሜ አሰማለሁ፡፡ ይህንን ለማወቅ የተለዬ ጥናት አይጠይቅም፡፡ ‹‹ደጋፊም አለን›› ካላችሁ አዎ ይኖራል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፍ ሰው ከማየት በላይ ደጋፊ እንዳለ ማረጋገጫ አይኖርምና የለም አልልም፡፡ ግን ጥቂት ደጋፊ ያለው ነገር ሁሉ ለሕዝቡ የሚቀርብበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ ማየት ያለብን አብዛኛውን ሕዝብና ሕጻናትን ወይስ እነዚህን ‹‹እንደ አማራጭ እየወሰድነው ነው›› የሚሉትን ?

4ኛ. ግልጽነት/የእኩልነት መብት…
ፕሮግራሙን የሴቶችን መብት የማስጠበቅና ግልጽ የመነጋገር አማራጭ አድርጎ ማይት ለእኔ አይገባኝም፡፡ ግልጽ መነጋገርን በዚህ መልኩ ከሆነ የምንረዳው ማለቴ ለሕጻናት መጥፎ ትምህርት የሚሰጡ የአልጋ ላይ ንግግሮችን ወደ አደባባይ በማውጣት ከሆነ በእውነት ተሳስተናል፡፡ መናናቅንና መነቃቀፍን በግልጽ ለሚዲያ ማቅረቡን ግልጽነት ካልነው ግልጽነት በራሱ ግልጽ አልሆነልንም፡፡
የሴቶች መብትስ የሚጠበቀው በዚህ መልኩ ሳይተያዩ በመምረጥና በመመረጥ ነው እንዴ ? የሀገራችን ባህል ለሴቶች ያሳጣቸው መብት ፍቅርን በግልጽ የመናገር (ለምሳሌ የወደዱትን መርጦ የመጠየቅ) ከሆነ ይህ ፕሮግራም በምን መልኩ ነው መብታቸውን ያስከበረላቸው ? እውን የወደዱትን ነው እየመረጡና እየጠየቁ ያሉት ? ብቻ ግራ የገባው መረዳት የያዝን ይመስለኛል፡፡
……
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተላለፉ የሚዲያ ፕሮግራሞች ሀገራችን የሃይማኖትና የባህል ሀገር መሆኗን መርሳት የለባቸውም። ባህልንና ሃይማኖትን አክብረው... ሲሆን ማኅበረሰቡን ወደተሻለ የአስተሳሰብ ከፍታ ለማምጣት ቢጥሩ ባይቻል ደግሞ ያለውን መልካም እሴት እንዲጠብቅ ቢያደርጉ ጥሩ ነው። በተለይ ግን ያለውን ጥሩ ነገር እያጠፉ የባዕድን ልቅነትና ሥርዓት አልባነት ለትውልዱ የሚያለማምዱ "የምንአለበት" ፕሮግሞች ከሚኖሩ ይልቅ ባይኖሩ እመርጣለሁ። አዘጋጆቻቸውም ሕዝቡ ቀድሟቸው ወደተሻለው ከፍታ ሄዷልና ለማውረድ ከሚጥሩ ይልቅ ከሕዝቡ ቢማሩ ይጠቀማሉ።

....... 

Monday, February 1, 2016

የትውልዱ የሥነ ምግባር ጉዳይ የማን ጉዳይ ነው?



(መላኩ አላምረው)
ከ2 ዓመታት በፊት በታተመ አንድ ጋዜጣ ላይ (የእኛ ፕሬስ) አንድ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም፣ አሳዛኝም ዘገባ አነበብሁ። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የግል ት/ቤቶች ውስጥ በአንዱ (ምንአልባትም የእኛ ቋንቋዎች በማይነገሩበትና ልጆች እንግሊዝኛ በመናገራቸው ብቻ የእውቀት ጣሪያ ላይ የደረሱ በሚመስሉበት) የተፈፀመ አስነዋሪ ተግባር።
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ሰባት ተማሪዎች (3 ወንድና 4 ሴት) የማጠናከሪያ ትምህርትና ጥናት አለን በማለት በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ያመሻሉ። ከዚያም (ከጥበቃዎች ጋር በመስማማት ይመስላል) ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአንድ ክፍል ውስጥ በቦርሳቸው ደብቀው ያስገቡትን ሁለት ጠርሙስ ውስኪ እየጠጡ ጭፈራ ይጀምራሉ። ይጠጣሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይጮሀሉ… ድምፁ በጣም እየተሰማ ተው የሚል ግን አልነበረም። እስከ ምሽቱ 7 ሰዓት አስረሽ ምችው ከጨፈሩ በኋላ ድምፃቸው ይጠፋል።
በማግስቱ ጠዋት ተማሪዎች ወደ ክፍል ሲገቡ የታየው ነገር በጣም አስደንጋጭም አሳፋሪም ነበር። ሴቶችም ወንዶችም እርቃናቸውን በወንበሩም በወለሉም ላይ ተረፍርፈዋል። ክፍሉ በትውኪያና ሽንት ተጥለቅልቋል። ሁለት የውስኪና ሦስት የአምቦ ውሃ ጠርሙሶች በየቦታው ወድቀዋል። የምግብ ፍርፋሪም በክፍሉ ይታያል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በ’ላፕቶፓቸው’ ሲመለከቱት (ምንአልባትም ያንኑ ሲለማመዱት) የነበረው አፀያፊ የ“ኦንላይን” ልቅ የወሲብ ፊልም አልተዘጋም ነበር። አገር ሰላም ያሉት ቀበጦቹ ተማሪዎች ግን እንቅልፍ ላይ ነበሩ።
እኔን በጣም የገረመኝ ነገር በሌሊት ክፍል ውስጥ ሲጨፈር ድምፁ እየተሰማ ጥበቃዎች ተው አለማለታቸውና ወላጆችም ልጆቻችን የት ቀሩ ብለው አለመጠየቃቸው ነበር። ለማንኛውም ይህ በአገራችን በተለይም በመዲናችን እየተፈጠረ ላለው አዲስ የወጣቶች መንፈስ እንደ አንድ ማሳያ ይሆናል እንጂ ሌላም ብዙ አሳዛኝና ዘግናኝ ነገሮች እየተፈፀሙ መሆኑን በየጊዜው እየሰማን ነው።
የአባቶች ውብ ባህል ወደ ልጆች እየተሻገረ አይደለም። የሥነ ምግባር መበላሸቱ ብቻ ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር አለማየቱ እየበዛ ነው። ሀገርኛ ቋንቋችንን መናገር አሳፋሪ ነገር እየሆነ መጥቷል። ገና በ’ሃይስኩል’ና ከዚያ በታች በሆኑ የትምህርት ደረጃዎች የሚጀመረው ከአገር ወግና ባህል ማፈንገጥ ነው አድጐ ነገ ሀገር የሚያጠፋው። በሥነ-ምግባር ያለታነፀ ትውልድ ለአገር ይጠቅማል ማለት ከንቱ ህልም ነው። ጥያቄው ግን ሥነ ምግባርን ማን ያስተምር የሚለው ነው። ወላጆች? ጓደኞች? ትምህርት ቤቶች? ወይስ የምዕራባውያን ፊልሞች? የእያንዳንዳቸው ድርሻስ በምን መልኩ መሆን አለበት?
ሁሉም ድርሻ አላቸው (መጥፎም ጥሩም ለማድረግ)። የአንዱ ግን ከሌላው ይለያል። ትልቁን ድርሻ መውሰድ ያለበት እና ለዚህም ጠንክሮ መስራት ያለበት ግን ከትምህርት ቤቶች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው አካል ይመስለኛል። ምክንያቱም ትውልዱን በእውቀትና በሥነ ምግባር አርሞና ኮትኩቶ የማሳደግ ድርሻው በአብዛኛው በትምህርት ቤቶች ላይ የወደቀ ነውና፡፡ የትምህርት ቤቶችን አጠቃላይ ሁኔታ መፈተሽ ያስፈልጋል። የሥነ ምግባር ትምህርቶች ውጤታማነት መታየት አለበት። ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ የትምህርት ስልት ማስተማር አለማስተማራቸው ሁሉ ሊጠናና የተጣመመው ሊቃጠጥ ግድ ነው፡፡
የተደበላለቀ ዓይነት ትውልድ የሚፈጠረው ወጥ ባልሆነ ሥርዓተ ትምህርት ነው። ዛሬ የአገራችን ነቀርሳ ሆኖ ታላቅ ዋጋ እያስከፈለ ያለው ሙስና መነሻው ትምህርት ቤት ነው። የሥነ ምግባር አስተምህሮታችን ውጤት ነው ሙስና። ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በአንድ ጀምበር አይፈጠርም። ትምህርት ቤቶች ላይ ብዙ መድከምን ይጠይቃል። ልጆች ሥነ ምግባርን መማር ብቻ ሳይሆን የሕይወት መርህ ማድረግ መቻል አለባቸው።
እንዲህ የሚባል ተረት አለ። “በእንግሊዝ አገር አንድ ገበሬ ነበር አሉ። ከእርሻ ሥራው ጐን ለጐን ድመቶችን በማሰልጠን የገቢ ማስገኛ ሥራ ይሰራባቸው ነበር። ገበሬው በልደት፣ በሠርግ፣ በምርቃትና በመሳሰሉት ልዩ ልዩ የደስታ ቀናት /በዓላት ላይ ስልጡን ድመቶቹን በመደዳ ያሰልፋቸውና በሁለቱ የኋላ እግሮቻቸው ቆመው በሁለቱ የፊት እግሮቻቸው ደግሞ የተለኮሰ ሻማ ይዘው እንዲታዩ በማድረግ ነበር ገቢ የሚያገኝባቸው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ታዲያ ገበሬው በአንድ ልዑል ሠርግ ተገኝቶ የተለመደውን ትርዒት እንዲያሳይ ይጋበዛል። ከ20 በላይ የሆኑት ድመቶችንም ግራና ቀኝ ተሰልፈው ሻማ እንዲያበሩና ሙሽሮቹ በመካከል እየተጀነኑ እንዲያልፉ በማድረግ ልዩና ዘና የሚያደርገውን ትዕይንት በማሳየት ላይ እያለ አንድ አሳፋሪ ክስተት ተከሰተ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ድመቶቹ በሚያሳዩት ልዩና ቀልብ የሚስብ ትዕይንት ሰው ሁሉ ማጨብጨቡን ትቶ ፈዞ በመመልከት ላይ ነው። የሙሽሮቹ ደስታ እጥፍ ድርብ እየሆነ ነው። ሁሉም ቀልቡ በትርዒቱ ተስቦ በአግራሞትና በአድናቆት ሲከታተል ከየት እንደመጣ ያልታወቀ አንድ የደነበረ ወደል አይጥ በድንገት ዘው ብሎ አዳራሹ ውስጥ ይገባል። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ሆነና የገበሬው ድመቶች ያን ወደል አይጥ ባዩ ጊዜ የተሰጣቸውን በልዑል ሠርግ ፊት እየተደረገ ያለ እጅግ ታላቅ ኃላፊነት ከምንም ሳይቆጥሩ ሻማቸውን እያሽቀነጠሩ በመጣል አይጡን ማባረሩን ተያያዙት። አዳራሹም በቅፅበት በትርምስና በሁከት ተሞላ። ገበሬው ታላቅ ሐፍረት ተሰማው። አንድ ነገር ግን ትዝ አለው። ድመቶቹን ስለ ሻማ አያያዝና አሰላለፍ ለማስተማር ያን ያህል ጊዜ ሲደክም ቢያንስ እንደዚህ ባለ የተከበረ ትርዒት ወቅት አይጥን አይቶ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል አላስተማራቸውም ነበር።” (የተረቱ ምንጭ፡- ምጥን ቅመም መጽሐፍ)
ከታሰበበትና ከልብ ከተደከመበት ሰውን አይደለም እንስሳትን አሰልጥኖ ልዩ ተአምር መፍጠር ይቻላል። የሰው ልጅ በባህርይው ባስተማሩትና በደከመበት ልክ የማወቅ ፀጋ አለው። መጥፎ ነገር ላይ ካተኮረ መጥፎን ይማራል። ጥሩን ካዘወተረም ጥሩውን ነገር የህይወቱ አካል ያደርጋል። ያልተማረውን መልካም ነገር ከየትም ሊያመጣው አይችልም። ትውልዳችንን ምን አልባት ፊደል እያስቆጠርነውና ሳይንስን እያስተማርነው ይሆናል። ለዲፕሎማ፣ ለዲግሪ፣ ለዶክትሬት… የሚያበቃውን እውቀትና ክህሎትም ሰጥተነው ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ግን ሥነ ምግባር ከጐደለው ከንቱ ነው። በትምህርት ውጤት አራት ነጥብ (4.00) ሊኖረን ይችላል። በክህሎትም ምስጉኖች ልንሆንና ሰው ሁሉ የእኛን ጥበብ የሚመኘው ሊሆን ይችላል። ሥነ ምግባር ከሌለን ግን ይህ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ሊተገበር አይችልም።
ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ማስተማር አንድ ነገር ነው። በሥራ ሂደት የሚመጡ መሰናክሎችን ሁሉ አልፎ ከሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ እንዴት እንደሚቻል ማሳወቅ ደግሞ ሌላ። ሥራን በልዩ ፍጥነትና ክህሎት እንድንሰራ ብቻ ሳይሆን ለማን እንደምንሰራና ለምን እንደምንሰራ ሁሉ ማወቅ አለብን። ሥራችን እየተደነቀ ባለበትና ልዩ ተስፋ በተጣለብን ወቅት ወፍራም ብር ሲመጣ ቃላችንን የምናጥፈውና ህዝብን ሳይሆን ግለሰብን0 የምናገለግለው እኮ እንዴት መስራት እንዳለብን እንጂ ወፍራም ብርን እንዴት ማለፍ እንዳለብን ስላልተማርን ነው። እነዚያ ድምቶች እኮ ገበሬውን ያዋረዱት አይጥ የማሳደድ ተፈጥሮ ስላላቸው ብቻ አይደለም። አይጥ መቼና የት ማባረር እንዳለባቸው እና መቼ እንደሌለባቸው አልተማሩም። በትርዒት ወቅት አይደለም አንድ አይጥ ሺህ አይጥ ቢመጣ አቋርጦ መሄድ እንደማይቻልና ይህንን የማለፍ ጥበቡና ሥርዓቱ (ምግባሩ) እንዴት እንደሆነ አልተማሩም። ለዚህም ነው ገበሬውን ያዋረዱትና ሠርጉን የረበሹት።
እኛም እኮ ዛሬ ገንዘብ የመውደድ ባሕርይ ስላለን ብቻ አይደለም ሙስና የምንበላው። ገንዘብን ከወደድን እንዴት ሠርተን ማግኘት እንደምንችል፣ ካሰብን እና ከጣርን ማግኘት እንደምንችል እንጂ የህዝብን ተስፋ ገድለን ኪሳችንን ማሳበጥ ፍፁም ቆሻሻና ወራዳ ሥራ እንደሆነ አላወቅንም። እንዲሁ ሰማነው እንጂ አልተዋሃደንም። በወሬ እንጂ በተግባር ያሳየን የለም። የሚያስተምሩንም እራሳቸው ሲዘርፉ እያየን ይሆናል። በልጅ አዕምሮአችን ያልተማርነውን የት እናምጣው። ሙስና ወንጀል ነው ተባልን እንጂ ሙሰኛው በተጨባጭ ሲወነጀልና ሲቀጣ አላየንም/አልተማርንበትም። ሙሰኛው ሲቀጣ በተግባር አሳይቶን የሚያውቅ መምህርም የለም። ታዲያ ሙስና እንደሚያስቀጣ እንዴት እንመን? ሥነ ምግባር የሚያስተምረንን ነገር ግን በተግባር የማያሳየንን መምህር እንዴት እኛ በተግባር እናሳየው? የምንማረው ሁሉ እንደሚሆን እንጂ እንዴት እንደሚሆን ካላየን እንዴት እንፈፅም? ይህ ሁሉ የትምህርትን ጉዳይ ጉዳየ ነው ባለው አካል ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል። ወላጆችም ሆንን መምህራን ትውልድን ብሎም ሀገርን የመገንባት ድርሻው የእኛ ነውና የሥነ ምግባሩን ጉዳይ አንዘናጋበት፡፡
   

Wednesday, December 30, 2015

ብቻችንን አይደለንም! - የሚጠብቁን መላእክት አሉ!


(መላኩ አላምረው)

እኔ እስካሁን ባለኝ ግንዛቤ መላእክት እንዳሉ የማያምን ሃይማኖት/የእምነት ተቋም በእኛ ሀገር እንዳለ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለምእመናን ባላቸው ድርሻ አንዱ ከሌላው የተለዬ አስተምህሮና እምነት ቢኖራቸውም በመላእክት መኖር ግን ያምናሉ፡፡ ኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት… ሁሉም የመላእክትን መኖር ይቀበላሉ፡፡ መላእክት ለሰው ልጆች በሚሰጡት አገልግሎት ግን አንዱ ከሌላው ይለያያሉ፡፡ የተወሰኑት መላእክት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚላላኩ መናፍስት ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሰው ከኃጢአቱ ይድን ዘንድ በአማላጅነት ይራዳሉ፣ ለጽድቅ ሥራ ሰውን ያግዛሉ፣ በነገረ ድኅነት ውስጥ ድርሻ አላቸው… ብለው ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ መኖራቸውን ተቀብለው አማላጅነታቸውን (ለድኅነት ያላቸውን ድርሻ) በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የመላእክትን አማላጅነት/አለማማለድ ወይም ሌላ የአገልግሎት ድርሻ ለመስበክ አይደለም፡፡ ‹‹የሰው ልጆች ብቻችንን እንዳልሆንና በመላእክት እንደምንጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?›› የሚለውን ለማሳየት እንጅ፡፡ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ መጽሐፍ ነው ብሎ የሚቀበል ሰው ይህንን እውነት ያውቅ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመላእክት መኖር የሚያምን ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ሰውም ቢሆን ይህንን ጽሑፍ ቢያነበው ስለ መላእክት ያለውን እውቀት ያሰፋለታል እንጅ አይጎዳውም፡፡
ወደ ጥቅስ ከመሄዳችን በፊት እንዲሁ በአመክንዮ (Logical Reasoning) ለማየት እንሞክር፡፡ መላእክት አሉ ብለን ካመንና መኖራቸውም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው ካልን… ‹‹የእነርሱ መኖር ለእኛ አስፈላጊነቱ ምንድነው? እነርሱ ባይኖሩ ምን ይቀርብናል? ወዘተ…›› የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ አለብን፡፡ የመላእክት መኖር ለሰው ልጅ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም ብለን ካመንን ደግሞ ‹‹ለሰው የማያስፈልግ ነገር ግን ከሰው ጋር ወይም በሰውና በፈጣሪ መሐል የሚኖር ፍጥረት ሊኖር ይችላልን?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለብን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ግን መለስ የሚኖረን አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ ለእኛ የማያስፈልግ ምንም ነገር በዙሪያችን ሊያኖር አይችልም፡፡ እኛ ጥቅማቸውን አላወቅንም ማለት አይጠቅሙንም ማለት አይደለም፡፡
ፈጣሪ አምላክ የማይታይ መንፈስ ነው ካልን በቅርበት ሊያገለግሉት የሚችሉት መናፍስት ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ለመንፈስ ባሕርይ ከሥጋ ለባሽ ፍጥረታት ይልቅ መናፍስት ይቀርባሉና፡፡ ለዚህም ነው ሰው ሥጋ እንደለበሰ ወደ ሰማይ (ወደ መናፍስት ዓለም) መሄድ የማይችለው፡፡ ነገር ግን በሥጋ ከሞተ በመንፈሳዊ ባሕርይው (በነፍሱ) እስከተገባው ቦታ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይቀርባል ብለን እናምናለን፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ሥጋው ተለውጦና እንደ መናፍስት የማይሞት ባሕርይን ይዞ ነው የሚነሳው (በትንሣኤ ሙታን)፡፡
መንፈስ ለሆነው አምላክ መናፍስት የሆኑ አገልጋዮች አሉት/ሊኖሩት ይገባል በሚለው ከተስማማን ደግሞ አገልግሎታቸው በፈጣሪና በፍጡራን መሐከል ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ (በቀላል ምሳሌ ለመመሰል… የአንድ ሀገረ ገዥ የቅርብ አገልጋዮች/ሹማምንት ማለት የሚገዛውን ሕዝብ ከእርሱ ጋር የሚያገናኙ፣ መልእክትን ከእርሱ ወደ ሕዝቡ፣ ከሕዝቡም ወደ እርሱ የሚደርሱ ናቸውና - ይህ ካልሆነም የቅርብ አገልጋይ አስፈላጊነቱ ምንም ነውና)፡፡
መላእክት ለፈጣሪ ከሰው ልጆች ይልቅ ቅርብ የሆኑ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ፍጡሩን ሁሉ ሲገዛ በየደረጃው ለፍጡራኑም የገዥነት ሥልጣንን በጸጋ ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ አዳም ለምድር ፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፡፡ መላእክትም በየደረጃቸው ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ የፍጡራን ሥልጣን ግን ከፈጣሪ ዘንድ በጸጋ የሚገኝና ከፈጣሪ ፈቃድ ውጭም ሊሆን የማይችል መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ፈጣሪ የዓለም ሁሉ ገዥ ነው፡፡ በየፍጥረቱ (በየወገኑ) የሾማቸው መናፍስት የሆኑ ፍጥረታት ደግሞ ይኖሩታል/አሉት፡፡ እነርሱም መላእክት ናቸው፡፡ ፈጣሪ ዓለምን ሲገዛ በጸጋ ሌሎች ገዥዎችን እንደሚሾም ከአዳም ተፈጥሮ መረዳት ይቻላል፡፡ እርሱን የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማለክት አምላክ የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡ ከሁሉም ግን ለእርሱ በባሕርይ መናፍስት የሆኑ መላእክት ይቀርቡታል፡፡ እነርሱንም ወደ ሌላው ፍጥረት ሁሉ ይልካቸዋል፡፡ ወደ ሰውም ጭምር፡፡ መላእክት ከመላው ፍጥረት ጋር ስላላቸው ግንኙነት በዚህ ጽሑፍ ማንሳት አልፈልግም (ካስፈለገ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)፡፡
የመላእክት ጠባቂነት ለሰው ልጆች እንዴት ?
በመጀመሪያ ደረጃ መላእክት እኛን የሰው ልጆችን ከልጅነት ጀምሮ በመንከባከብ ይጠብቁናል፡፡ ለዚህ ማስረጃነት ከመጽሐፍ ቅዱስ 2 ጥቅሶች ብቻ እንመልከት፡፡ ከብሉይ ኪዳን ለመጀመር ከደጋግ አባቶች አንዱ የሆነው ያዕቆብ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ የመገበኝ እግዚአብሔር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ የጠበቀኝ/ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች/ሕጻናት ይባርክ›› በማለት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እንዳዳነውና እንደጠበቀው ያስረዳል …ዘፍ 48፥16፡፡ ይህም መልአክ ልጆቹንም ይባርክለት/ያከብርለት ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ቃል በትንቢተ ዳንኤል ላይ… ዳንኤልን መልአኩ እንዴት ይጠብቀው እንደነበር… በኋላም ሠልስቱ ደቂቅን (ሦስቱን ሕጻናት) የእግዚአብሔር መልአክ ከእቶን እሳት እንዴት ጠብቆ እንዳዳናቸው ተጽፏል፡፡
አይ… ይሄ የሐዲስ ኪዳንን አምልኮ አይወክልም ካልን ደግሞ የሚከተለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል እንመለከት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.18፡ቁ.10 ላይ… ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ ‹‹አንዱን›› እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ ‹‹መላእክቶቻቸው›› ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።›› ይላል፡፡ ይህ ቃል ሁሉም ሰው መላእክት እንዳሉት ያሳያል፡፡ እነዚህ መላእክት ሊጠብቋቸው ካልሆነ ለምን ከታናሾች ጋር ይኖራሉ? ልብ ብለን እንመልከት… ‹መላእክቶቻቸቸው› ‹ዘወትር› የፈጣሪን ፊት ያያሉ… ማለት ስለሚጠብቋቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ይጠየቃሉ፣ ይናገራሉም፡፡ ‹ፊቱን ያያሉ› ማለት ለአገልሎት/ለመልእክት መቅረብን እንጅ ፈጣሪን እንደ ሰው ገጹን ማየትን አያመለከትም፡፡ ይህ ለፍጡራን አይቻልምና፡፡
ከዚህ ላይ ሌላ ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ… ማንንም ሰው ታናሽ ነው… አቅመ ቢስ ደካማ ነው… ብሎ መናቅና በእርሱም ላይ በደል ማድረስ በሰው ፊት ባይሆን እንኳን በፈጣሪ ፊት እንደሚያስከስስ ነው፡፡ ሰው ብቻውን አይደለም፡፡ ዘወትር ስለበደላቸው ለፈጣሪ የሚናገሩ መላእክት አሉና፡፡ ለዚህም ነው ምዕመናን የመላእክትን ጥበቃ ተስፋ የሚደርጉት፡፡
እስኪ ማጠቃለያ ጥያቄ እናንሳ… ለመሆኑ አንድ መልአክ በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላልን ? ለምሳሌ የገብርኤል በዓል ዕለት በሁሉም ቦታ ሕዝቡ ወጥቶ የሚያነግሰው በሁሉም ቦታ ካልተገኘ ለምን? ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የመላእክትን ተፈጥሮ ነው፡፡ መልአክ በባሕርይ ተፈጥሮው መንፈስ ነውና ይችላል፡፡ በሥጋ ስሌት ካላሰብነው በቀር ይህ ለመናፍስት የተሰጠ ጸጋ ነውና በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላል፡፡ በመዝ. 33፥7 ላይ የተጻፈውን ልብ እንበል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ‹መልአክ› ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹ዙሪያ› ‹ይሠፍራል›፣ ‹ያድናቸውማል››› ይላል፡፡ ‹‹መልአክ›› ብሎ አንድ መሆኑን… ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹‹ይሰፍራል›› ሲል ደግሞ ለብዙ ቁጥር የሚሆነውን ቃል ተጠቀመ፡፡ ሰፈረ… ብዙ ቦታ ላይ ተገኘ… እንደማለት ነው፡፡ እንዲያውም በብዙ ሰዎች ‹ዙሪያ› ነው ሚሰፍረው፡፡ አንድ ሰው ቢሆን ኖሮ በሌላው ሰው ‹‹ዙሪያ›› ሳይሆን ወይ በፊት ወይ በጎን ነበር ሚቆመው፡፡ እዚህ ላይ አንዱ መልአክ ግን በዙሪያቸው ሲሰፍር ያሳያል፡፡
በመጨረሻም… ለሰው ልጆች የመላእክት ጥበቃ ያስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት ፈጣሪ በራሱ ፍጡሩን መጠበቅ ስለማይችል ወይም በደላችንን የማያውቅ ሆኖ ሳይሆን ለፍጡራኑ የአገልግሎት ድርሻ ለመስጠት ነው፡፡ በመላእክትም ጠበቀን በራሱም ጠበቀን ዞሮዞሮ ጥበቃው የፈጣሪ ነው፡፡ ፍጡር በየደረጃው እያገለገለ መንግሥቱን ይወርስ ዘንድ የአምላክ ፈቃድ ነውና… በምድርም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ምድርንም እርሱ ፈጥሮ ይገዛት ዘንድ ለሰው ልጅ ሰጠ፡፡ የሰው ልጅም አገልጋይነቱን ከተረዳና በሥርዓት ከኖረ ለሌላ ሰማያዊ መንግሥት ይበቃል፡፡ መላእክትም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአገልግሎታቸው ካልተጉ እንደ ሣጥናኤል ከፈጣሪ ክብር ይርቃሉና ዘወትር በትጋት ያገለግላሉ፡፡
ይቆየን……
.....
(ይህ ጽሑፍ በእኔ የመረዳት ደረጃ ብቻ የተጻፈ ነው፡፡ ለእርማት ዝግጁ ነኝ)
……………….

በሃይማተኞች ሀገር ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች ባይዘነጉ …




(መላኩ አላምረው)
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን እየሠራ ያለ አንድ በጣም የምወደው ጓደና አለኝ፡፡ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀን በሥራ ዓለምም ለ4 ዓመታት ያህል በአንድ ግቢ ነው ተከራይተን የኖርነው፡፡ ብዙ ጊዜ… ስለብዙ ነገሮች እንወያያለን፡፡ ስለ ሀገር ፣ ሃይማኖት ፣ ፍቅር ፣ ትዳር ፣ ጓደኝነት ፣ ትምህርት ፣ … ብቻ የማናነሳው ነገር የለም፡፡ በተለይ ወቅታዊ ጉዳዮችን አናልፋቸውም… እንዲያውም ብዙ ጊዜ የውይይት አጀንዳዎቻችን እነርሱው ናቸው፡፡ የችግሮችን መንስኤ በአቅማችን ለመተንተን እንሞክራለን… እንከራከራለን… ከዛም መፍትሔ ያልነውን (ለራሳችን) እናስቀምጣለን፡፡ ነገር ግን እኛ መፍትሔ የምንለው… ያው ለአዕምሯችን እረፍት ይሆን ዘንድ እንጅ… ከእኛ ወጥቶ አያውቅም፡፡ በተለይ በሀገራዊ መፍትሔ ሰጭ አካላት ዘንድ እንኳን መፍትሔዎቻችን የእኛ መኖርም አይታወቅም፡፡
[ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር… ሁሉም በየቤቱ (በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ) ይወያያል… ይከራከራል… የየራሱን መፍትሔም ያስቀምጣል፡፡ ሕዝቡን በነፃነት የሚወያይበትና አማራጭ ሀሳቡን የሚያካፍልበት ሥርዓት ቢዘረጋለት… ‹ትክክለኛ› መፍትሔ የሌለው ነገር ይኖር ይሆን? አሁን ለተለያዩ ነገሮች መፍትሔ ናቸው የሚባሉትስ እውነት ለመፍትሔነት የመጨረሻ አማራጭ ይሆኑ ይሆን? እውነት ለመናገር በሕዝብ ውስጥ ላሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ በዚሁ ሕዝብ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሕዝብ መፍትሔ ደግሞ….. በቃ መፍትሔ! ነው፡፡ ሕዝቡ ተወያይቶ ፣ ተከራርክሮና ተስማምቶ ያደረገው ምንም ነገር ቢሆን መፍትሔው ያ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ ከልቡ አመንጭቶ በአንደበቱ ያላጸደቀው መፍትሔ… ትክክለኛ ቢሆንም እንኳን የመፈጸሙ ነገር እምብዛም የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ‹ሕዝቡ ይናገር ! ሕዝቡ ካልተናገረና ሲናገርም ካልተደመጠ እርሱም ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጠውና አዳምጦም በተግባር የሚያውልለት የመፍትሔ አካል አይኖርም፡፡›]
እናም ይህ ጓደኛዬ… ትላንት ምሽት ላይ ለተለመደው ውይይታችን እንደተገናኘን ያነሳው የመወያያ አጀንዳ… ‹‹ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችና የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ›› የሚል ነበር፡፡ ርዕሱ ብዙ አላከራከረንም፡፡ ባጭሩ ‹‹ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት ፤ ስለዚህ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ችግር ሲከሰት (ከፖለቲካዊ መፍትሔዎች ጎን ለጎን ወይም በራሳቸው ጊዜና ቦታ) ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችም መሰጠት አለባቸው፡፡ ለዚህም የሃይማኖት/የእምነት ተቋማት የቤት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ውይይታችንን በጊዜ ቋጨነው፡፡
ለሁላችንም አዲስ ባይሆንም… በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ ከተከሰቱት ድርቆች ሁሉ የከፋ የተባለው ድርቅ ተከስቷል፡፡ ከ10 ሚሊዮን ሕዝብ በላይም ለእርዳታ እጁን ዘርግቷል፡፡ መንግሥትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች እየሠሩበት ቢሆንም… የሃይማኖት ተቋማት ግን ‹ሃይማኖታዊ መፍትሔ› ሲወስዶ አላየንም፡፡ እርግጥ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ አሉ፡፡ ለተራበ ሰው መጀመሪያ መደረግ ያለበት ድጋፍ የገነንዘብ መሆኑንም እረዳለሁ፡፡ ይህ ግን ለሃይማኖታዊ ተቋማት በቂ መፍትሔ አይደለም፡፡ ገንዘብ ያላቸው እሺ ይርዱ… የሌላቸውስ? እንደ ሃይማኖት ተቋም (ከገንዘቡ ባሻገር) መወሰድ ያለባቸው መፍትሔዎች የጾም ፣ የጸሎት (ምኅላ) እና ተያያዥ መንፈሳዊ ክዋኔዎችም መሆን አለባቸው፡፡ እስካሁን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ተብሎ በየትኛውም የሃይማት ተቋም የታወጀ ጾምና ጸሎት አልሰማሁም፡፡ (ካለ ይቅርታ… የመረጃ ክፍተት ነው)፡፡
በተለይ በእንደዚህ ዓይነቱ ችግር ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች በአዋጅ ሲተገበሩ ካልታዬ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገርነት ለመቼ ነው? ገንዘብማ ማንም ዓለማዊ ተቋም ሊረዳ ይችላል፡፡ ሃይማኖት ግን ከገንዘብ ባሻገር የሚረዳው ምሥጢራዊ መፍትሔ አለ፡፡ የሰማይን በር የሚያንኳኳ መፍትሔ… ጾም ፣ ጸሎት ፣ (ምኅላ)….፡፡
በድርቁ ብቻ ሳይሆን… በተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች (ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ጉዳይ) ላይ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ… ‹ዝምምም›… ነው እንዴ መሆን ያለበት? ይህችን የሃይማኖት ሀገር በፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ማስተዳደር ሊቻል ቢችልም… ለእኔ ትክክል አይደለም፡፡ ምዕመኑ (ከመሪ እስከ ተመሪው) በየሃይማኖቱ… የሚመከረው መመከር ፣ የሚገሠጸው መገሠጽ ፣ የሚወገዘውም መወገዝ አለበት ባይ ነኝ፡፡ በሃይማኖተኞች ሀገር ያለ ሃይማኖታዊ መፍትሔ ችግሮችን መጋፈጥ….??? አይከብድም? የሃይማኖትም የሆነ የተቋማቱ የመኖር ትርጉም በተግባር ካልታየስ ለምን ይኖራሉ?
….

Sunday, November 1, 2015

ስግደቴ ...


...
በቤትህ ላስቀድስ ስገኝ...
"ስግዱ" ይላል ዲያቆኑ - ራሱም እየተንበረከከ
"ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ ወንሰብሐከ"
ይመልሳል ምዕመኑ - በተግባር እየገለጠ
መሬታዊ ጉልበቱን - ለፈጣሪው እየሰጠ...
...
የእኔ ልብ ግን ጠማማው - ፖለቲካዋን ጨማምሮ
ብሶቱን ለአምላኩ ይጮሃል - በስንኝ ነገር ቋጥሮ
...
<<አምላክ እንኳንስ ላንተ - በፍቅርህ ለምትገዛ
በባለጊዜ ወጠምሻ - ጉልበቴ በጽኑ ተይዛ
መንበርከክን ለምዳለች - መስገድ አይደለም ብርቋ
ባይሆን ለኋላ ርስቷ - ለሰማያዊ ጽድቋ
የአምልኮ ስግደቴን ተቀበል - ከመሬታዊው ለይና
ሥጋዬን ቢገዟትም - ነፍሴ በተስፋ ትጽና!>>
...
(መላኩ - መስከረም 30/2008)