Friday, August 12, 2016

‹‹ለራበው ሰው ብትዘምርለት የሚሰማህ በጆሮው ሳይሆን በሆዱ ነው››

(መላኩ አላምረው)
-----//-----
አንድ ‹‹ሕዝባዊ ነኝ›› የሚል አካል፡-
ሕዝብ የሚለውን ካልሰማ... ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ መደመጥን ከጠበቀ ፣
ሕዝቡን የንቀት በሚመስል እይታ እያየ... ነገር ግን ከሕዝቡ ዘንድ ክብርንና ፍቅርን ከፈለገ ፣
ሕዝቡ ‹‹ስህተት ነህ›› እያለው... በደፈናው ‹‹ትክክል ነኝ›› ካለና ትክክልነቱን ማስረዳትም ማሳመንም ከተሳነው ፣
ሕዝቡ ‹‹ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉኝ›› እያለው... ‹‹ጥያቄህንም መልስህንም ማውቀው እኔ ነኝ - መልሸልሃለሁም›› ካለ፣
ሕዝቡ ‹‹ብሶቴን ልገልጽ አደባባይ ወጥቻለሁ›› እያለው... ‹‹የት አለህ የሚታዩኝ ጥቂት አንተን የማይወክሉ ሰዎች ናቸው›› ብሎ ከመለሰለት......
በቃ ይህ አካል ወይ ሆን ብሎ ሕዝቡን ለማናደድ እየተናገረ ነው ወይም ደግሞ ‹‹የሚታዩም ሆነ የሚነገሩ መልእክቶች ተቃራኒ የሚሆኑበት ልዩ ፍጡር›› ነው፡፡ የመጀመሪያውን ከሆነ (ሆን ብሎ ሕዝብን ለማናደድ ከተናገረ) ወደ አእምሮው ይመለስና ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቅ፡፡ ሁለተኛውን (መልእክቶች ሁሉ በተቃራኒው የሚደርሱት ፍጡር) ከሆነ ግን በግልጽ ይታወቅና ሕዝቡ በጸሎትም ሆነ በህክምና ወደ ትክክለኛ ሰውነት ይመለስ ዘንድ ያግዘው፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን (እኔ በግሌ) ከምሰማው ይልቅ የማየውን የማምን ጤነኛ ሰው ስለሆንሁ (እግዚአብሔር ይመስገንና) በዚህ ሰዓት በሀገራችን ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ግልጽ ተቃውሞ የለም የሚለውን አልቀበለውም፡፡ መሠረቱ ምንም ይሁን ምን፣ ከጀርባ ሌላ አካል ኖረም አልኖረም፣ በሌሎች መገለጫዎች ጠራነውም አልጠራነውም... በግልጽ የሚታይና ኃላፊነት የሚወስድ አካል እንኳን ባልኖረበት... አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰና የሚቀጥልም የሚመስል ሕዝባዊ ተቃውሞ አለ፡፡ ያውም ሞት እንኳን ሊመልሰው ያልቻለና አንድ ሰው በሞተ ቁጥር እየተባዛና እየተፋፋመ እየሄደ ያለ ተቃውሞ፡፡
እንዲያውም በእኔ ዕድሜ ካየኋቸውም ሆነ በታሪክ ካነበብኋቸው ኢትዮጵያዊ የሕዝብ ተቃውሞዎች ሁሉ በዚህ መልኩ በስፋትና በተከታታይነት የተካሄደ የለም ባይ ነኝ፡፡ ከሐቁ መራቅና ሌላ ፍረጃ መስጠት መፍትሔ አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም የበለጠ ወደተውሰበሰበ ችግር ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ እንዲያውም... እንዲያውም..... የመፍትሔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን የበለጠ የሚያስከፋና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው የሚሆነው፡፡ ለሚያስተውልና ልባም ለሆነ ሰው ደግሞ ይህ በራሱ የሌላ መጻኢ-ችግር መነሻ ነው፡፡ ባለመፍትሔዎች ተስፋ የቆረጡና ዝም ያሉ ዕለት... ያኔ መላ ቅጡ ይጠፋና ማጣፊያው ያጥረናል፡፡
የምናገረው ዝም ብሎ የቅዠት ትንበያ አይደለም፡፡ በመረዳት እቅሜ ልክ የተረዳሁትን መፍትሔ አዘል ሐቅ እንጅ፡፡ የሚሰማ ኖረም አልኖረም... እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛልና የማስተውለውን እውነት በተላዘበ መልኩ ከመግለጽና መፍትሔዎችን ከመጠቆም አልቦዝንም፡፡ ማንም ሊጠቀምበት ባይችል እንኳን ለእኔ የአዕምሮ ዕረፍት ስል እናገራለሁ፡፡ የእኔ ሐሳብ ብቻ ነው ትክክል አልልም፡፡ ነገር ግን... ሐሳቦችን የመናቅና ያለመቀበል፣ በራሳችን መንገድ ብቻ የመሄድ አባዜ ካተጠናወተን በቀር... ከእንደኔ ዓይነቱ ጀምሮ በብዙዎች የሚወጣጡ ሐሳቦች ናቸው ተደምረው መፍትሔ የሚሆኑት፡፡ የምንባለውን እየናቅን ጆሮ ባልሰጠን መጠን ወደ ባሰ ችግር እየገባን መሆኑን ማስተዋልም ትልቅነት ነው፡፡
በእኔ እምነት... ከምንም ነገር በፊት ለዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ሕዝቡ ራሱ የመፍትሔ አካል እንዲሆን ነፃ እናድርገው፡፡ ‹‹ጉዳዬና ችግሬ›› ላለው ነገር እውቅና ካልሰጠንለት ሕዝብ ጋር መደራደር ብሎ ነገር አይገባኝም፡፡ እውቅና በነፈግነውና ሌላ ስም በሰጠነው መጠን እየተባባሰ የሄደ እንጅ የረገበ ነገር እንደሌለ እያየን ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡ በተግባር ያለበትንና የሚሳተፍበትን ጉዳይ ‹‹ያንተ አይደለም፣ የለህበትም...›› በማለት ብቻ መፍትሔ አመጣለሁ ማለት... ከንቱ ድካምና ሕዝቡንም መናቅ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ‹‹ነገሮችን የመረዳትም ሆነ ራስህ የምታደርገውን እንኳን የማወቅና የመተርጎም ችግር አለብህ›› እንደማለትም ነው፡፡ ትክክለኛ ጥያቄውን በመመለስ እንጅ ‹‹ለመሞት ቆርጦ ወደወጣ ሕዝብ›› የታጠቀ ፖሊስ በመላክ የሚመጣ መፍትሔ... ለእኔ አልታይህ ብሎኛል፡፡ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ከመፍትሔነቱ ይልቅ ችግርነቱ ያመዝንብኛል፡፡
ራበኝ ላለ ሰው ምግብ እንጅ ሙዚቃ አይጋበዝም፡፡ ‹‹ለራበው ሰው ብትዘምርለት የሚሰማህ በጆሮው ሳይሆን በሆዱ ነው›› የምትለዋን የአባቶቻችንን አባባል ልብ ይሏል፡፡ ‹‹ጠቢብ ከሌሎች ስህተት ይማራል›› የሚለውንም እንዲሁ፡፡
-----//-----

አታስቢው ፍቅሬ - ከቶ አንለያይም !!!

(መላኩ አላምረው)
-----//-----
መለያየት አልሽው - መለያየት ዋዛ...
ቀኑ ሳይጨላልም - ይልቅ ልብ እንግዛ !
.
እኔ ልሙት ፍቅሬ - ስጋሽን ያስበላኝ
ማንም የፍቅር ደሃ - ደርሶ ስለጠላኝ
የሰዳቢውን ዘር - ከዘርሽ ገምጄ
ከከፋፋዩ ልብ - ጥላቻን ወስጄ
ንጹኋን አጋሬን - ከእርሱ ጋር ደምሬ
እኔ አንችን ልለይሽ ? - አታስቢው ፍቅሬ !
...
ተይ ! ከአፍሽ አይውጣ !
የምን መለያየት ? ቆይ ምን ስለመጣ ?
‹ኢትዮጵያዊት› ፍቅሬ - ፈጽሞ እንዳትፈሪ
ይህን ክፉ ሐሳብ ፣
እንኳንስ ለእኔ’ና - ለ’ራስሽ አታውሪ !

ይልቅ ስሚኝማ....
እንዳይከፋፍለን - ትንሹም ትልቁም
ለጋራ ነፃነት - ነይ በጋራ እንቁም
ነይ ሰላም እንስበክ - ነይ ፍቅር እንዝራ
የዘር ዘራዝርቱ - ፍሬ እንዳያፈራ !
.
የመለያየት ድምጽ - ጎልቶ እንዳይሰማ
ወንድም በወንድሙ - ጥይት እንዳይደማ
ወገን ከወገኑ - ቂም እንዳይቋጠር
ከዛሬው የባሰ - ሞት እንዳይፈጠር
ነይ የፍቅሬ መልአክ - ነይልኝ ሰላሜ
ነይ የምድሬ ገነት - ነይልኝ ዓለሜ
ወይ ሕይወትሽ አልፎ - ወይም ፈ’ሶ ደሜ
ሳይጫነን አፈር - ምድር ሳትበላን
ነይ እንወቅበት - በገባብን ሰይጣን
አንች’ና’ኔን ገፍቶ - ካ’ገር ሳያስወጣን
ነይ በአንድነታችን - በኅብረት ይቀጣ
በፍቅር ተቃጥሎ - ‹‹ሰባት ጮሆ›› ይውጣ !
.
እንጅ መለያየት - እንዴት ይታሰባል ?
ከማስነቀፍ አልፎ - ቃሉም ያሰድባል !
.
በምን እንለያይ ? ብሔር ዘርን ቆጥረን ?
ማነው ከማን ሚለይ ?
ሰው ከመሆን ዘር ነው - እርሱ የፈጠረን !
ጤነኛ ሕሊና - ይህንን አይከዳም
እናታችን ሔዋን - አባታችን አዳም ፡፡
...
በዓለሙ ስሌት - አሁን ያንች’ና’ኔ
ዘራችን ቢቆጠር… ይገርመኛል ለእኔ !
.
የተወለድሽ አክሱም - ያሳደገሽ ጅማ
ውልደቴ ግሽ ዓባይ ፣
እድገቴ ዓባይ ማዶ ፣ ወለጋ... ሲዳማ
አካላችን አዲስ - መንፈሳችን ዲማ !
በአባትሽ ከትግራይ - በእናትሽ ኦሮሞ
በአባቴ ከጎጃም - በአያቴ ከጋሞ
በአንዱ አያትሽ ጅማ - በሌላው ሀረሬ
በአንዱ አያቴ ባሌ - በአንደኛው ጎንደሬ
የተማርነው አዲስ - ያፋቀረን ፀባይ
ያጣመረን ፍቅር ፣
ሥጋችን ከምድር - ነፍሳችን ከሰማይ
ቆይ የምን ዘር ቆጥረን - እንዴት እንለያይ ?

አየሽልኝ አይደል - የዓለምን ቅሌት
ማናችን ምን ሆነን - በየትኛው ስሌት ?
‹‹እንለያይ ይሆን?›› - ብለሽ የምትፈሪው
እባክሽን ፍቅሬ ፣
ይህን ክፉ ሀሳብ - እንኳንስ ለሌላው - ለራስሽ አታውሪው፡፡

በትላንት ስህተቶች
በዛሬ ክስተቶች
በነገ ቅዠቶች….
ምን ልቤ ቢቆስል - ምን ልብሽ ቢደማ
መለያየት ብሎ…? - አይታሰብማ !!!
...
ቆይ አስበሽዋል ?
የፍቅር መምህራችን - ሐዲስ ዓለማየሁ
በዛብህን ልሆን - አንችን ሰብለን ያየሁ
ጥበብን የቀዳን - እኔ ከተዋነይ አንች ከበዓሉ
በየኔታ ትምህርት - ያደርን እንደቃሉ
ከቁልቢ ገብርኤል - ቁርባን ተቀብለን
ከጻድቃኔ ማርያም - ጸበል ተጠብለን
በግሸን ቃልኪዳን - በላሊበላ ጽድቅ
በአክሱማዊ ጥበብ - በሐረር ድንቃድንቅ
በአፄ ፋሲል ግቢ - በጅማ አባ ጅፋር
በኤርታሌው እሳት - ተደመ’ን በአፋር
ከዓባይ ጠጥተን - በባሮ ተራጭተን
ሐዋሳ ተዝናንተን - ሐሸንጌን ጎብኝተን
በጣና በዝዋይ - በአባያ በጫሞ
መንፈሳችን ከንፎ - ልባችን ተደ’ሞ

በተፈጥሮ ምሥጢር - ከአፈሯ የመጣን
ኢትጵያዊነት ! - ከወንዟ የጠጣን
ከምንጯ የቀዳን… ከሐይቅ ከኩሬዋ
ከአዝዕርቷ የበላን… ከዛፍ ከፍሬዋ…

ኧረ እንዴት ሲደረግ ? - እኮ ምን ሲፈጠር ?
የትኛው ሕዝባችን - በማን ሲጠረጠር ?
‹‹እንለያይ ይሆን?›› - ብለሽ የምትፈሪው
እባክሽን ውዴ !
ይሄ ክፉ ሐሳብ - ከአፍሽ እንዳይወጣ ! ለልብሽ አታውሪው !
------------------------፡፡
.....
...

ለሕዝቡ ‹‹እናውቅልሃለን›› ካልን በቀልን ሳይሆን ይቅርታን እናሳየው!

(መላኩ አላምረው)
-----//-----
በየቀኑ... በትጋት... በተደጋጋሚ... ‹‹የእገሌ ብሔር በእነ እገሌ ንበረቱ እየወደመ ነው ፣ እየተገደለም ነው... ወዘተረፈ›› እያልን የዘር-ተኮር ብጥብጥ ቀስቃሾች የሆን ‹‹አዋቂ ነን - ጸሐፊ ነን›› ባዮች ግን ትንሽ ማስተዋል የሚባል ነገር አልፈጠረብንም ? ደግሞ እኮ የምንለጥፈው ነገር እራሱ ምንም ያልተጨበጠና እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡ አንዴ ሕዝቡ ጨዋ ነው አንዴ ገዳይ ነው... አንዴ ለሕዝቡ ስንሠራ ስለኖርን ሕዝቡ ይወደናል ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘር ለይቶ እያጠቃን ነው... ዝብርቅርቅ ያለ መልእክት፡፡
ዓላማችንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በዘር እየተጠቃ ነው ለምንለው ወገን አስበን ነው እንዳልል... በተዛባና ባልተረጋገጠ መረጃ እያወናበድንና ተረጋግተው የሚኖሩትን የበለጠ እየረበሽን ‹‹ለሕዝብ ማሰብ›› ብሎ ነገር አይገባኝም፡፡ በተለይም ይህ በሆነ ባልሆነው የምናራግበው ዘር-ተኮር መጠቃቃት ሌላ በቀልና ሌላ ጥቃት እንደሚያስከትልም የገባን አይመስለኝም፡፡
ደግነቱ ሕዝቡ ከእኛ የተሻለ ያስባል፡፡ በስሜት የበደለ ካለ ይክሳል፡፡ በስህተት የተበደለ ካለም ይቅር ይላል.. ይታረቃል፡፡ ሕዝቡ በክስተቶች (ራሱ ሳይሆን ሌሎች በራሳቸው ዓላማ በሚፈጥሩበት ችግር) ቢገዳደልም እንኳን በደም ካሳ ታርቆ የመኖር ባህሉም የአዕምሮ ልዕልናውም አለው፡፡ አሁን ‹‹በዘር ተጠቃህ›› የምንለው ሕዝብ በእርግጠኝነት ነገ (በስሜትም ሆነ በስህተት ጉዳት ያደረሰበት ካለም) ይቅርታ አድርጎለት አብሮ ይኖራል፡፡ ሕዝቡ የመኖር ምሥጢር ማለት ‹‹ይቅርታ ማድረግ - የበደለ ክሶ የተደበደ ተክሶ›› መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ አላዋቂዎች እናውቅልሃለን በማለት፣ ከወንድምና እህቶቹ ጋር ልናገዳድለው ብዙ ብንደክምም ይህንን እኩይ ዘር-ተኮር ጠብ አጫሪነት የመስሚያ ጆሮ የለውም፡፡
እኛ በአላዋቂነታችን መጠን ብዙ እንለፈልፋለን፡፡ ሕዝቡ ግን ‹‹አብሮ በመኖር ግጭት፣ በግጭትም እስከመገዳደል የሚደርስ ችግር ሊመጣ ቢችልም... ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በይቅርታ አብሮ መኖር›› እንደነበረ፣ እንዳለና እንደሚቀጥል ያውቃል፡፡ ይህንን አላውቅ ብለን ለመኖር የተቸገርነው እኛ ‹‹ተማርሁና አወቅሁ›› ያልን ዘረኞች ነን፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር የበቀል ጦርነት የምናውጀው እኛው ነን፡፡ ግራ በተጋባ አዕምሯችን ትልቅ አብሮ የመኖር እሴትና የይቅርታ ባህል ያለውን ሕዝብ ሌላ አዲስ እኩይ ትምህርት ልንሰብከው የሚዳዳን እኛው ነን፡፡ አንዳንዴማ እንፈር እንጅ፡፡
ለሕዝቡ በጎውን እንጅ ክፉውን እንድናወርሰው ከሆነ ድካማችን ወላጆቻችንን ‹‹የወላድ-መካን›› እያደረግናቸው ነው፡፡ ሌላ ወልደው እንዳይተኩም ዘር አጥፊ መንገድን እያሳየናቸው ነው፡፡ የምንናገረውን የማናውቅ ከሆነ ዝም ብንል አዋቂዎች ይናገሩና መፍትሔ ይመጣ ነበር፡፡ ግን በድፍረት ብቻ ቦታውን ይዘን ነገር እያበላሸን ነው፡፡ ምን ተሸለን ? ‹‹ድፍረት ብሔራዊ ቋንቋ እየሆነባት ያለች ሀገር›› አለ እያዩ ፈንገስ........
እባካችሁ... ፖለቲከኞችን ተዋቸው። ሁሉም በየራሳቸው ዓላማ ሊቃዡም ሊያልሙም ይችላሉ፡፡ ለእኛ ከተመቹን ብቻ ይመሩናል፡፡ ካልተመቹንና እኛን ካልሰሙን ይወገዳሉ፡፡ ሕዝብን የማያመችም ሆነ የማይሰማ ፖለቲከኛ በሕዝቡ ከመወገድ የሚያድነው ምንም እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከሕዝቡ ውጭ ሆነው መኖር እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የእነርሱ ጉዳይ ሳይሆን የሕዝብ አንድነት ጉዳይ ነው ሊያሳስበን የሚገባው፡፡ እኛ ‹‹አዋቂ ነን - ጸሐፊ ነን›› ባዮች እንደ ሕዝቡ አካል ሕዝቡን እንምሰል፡፡ አብሮ የመኖር ዋስትናችን የተመሰረተው ‹‹ነፃ አውጥቸሃለሁም ነፃ አወጣሃለሁም›› በሚሉን ፖለቲከኞች ላይ ሳይሆን በእኛው (በአባቶቻችን) ‹‹የኖረና ያኖረን የሚያኖረንም›› የዳበረ የአብሮነት ባህልና ፍቅር ነው። እንደሕዝብ አንድ እንሁን። እኛ አንድ ስንሆን ፖለቲከኞች ልብ ይገዛሉ። ከሕዝብ ልብ የሌለውን አጀንዳቸውንም ይተውታል። ሕዝብ ለሕዝብ ምንም ቂም በቀል የለንም። ተዋደን፣ ተጋብተን፣ ተዋልደን፣ ተዋሕደን... እየኖርን ነው ፣ ገናም እንኖራለን። የሃይማኖትም፣ የቀለምም፣ የባህልም፣ የቋንቋም ልዩነታችን ውበታችን እንጅ መከፋፈያችን አይደለም። ሺህ ዓመታትን እንደኖርን በፍቅርና በአንድነት እንቀጥላለን።
ማስተዋሉን ያድለን፡፡
-----//-----

Sunday, May 8, 2016

እናቱ - እናቴ ! ልደትሽ - ልደቴ !



(በመላኩ አላምረው)
     + + +
ለእናትነት ክብር እርሱ ከመረጠሽ
በዮሐንስ በኩል ለእኔ ከተሰጠሽ
እኔም እርሱን ጌታ ብዬ ከተቀበልሁ
ማዳኑን አምኜ - በሕጉ ስር ከዋልሁ
እናቱን እናቴ ብየ ለመቀበል...
ጥያቄ ልደርድር? ለምን? እንዴት? ልበል?
      + + +
ልጅሽ በምድር ላይ ሥጋሽን በመልበስ
አዳምን ሊያድነው ለእኛም ጽድቅን ሊያወርስ
የረገጠው መሬት የቆመበት ቦታ
ከቤተልሄም ዋሻ እስከ ጎለጎታ
ቅዱስ ከተባለ ውሎ ያደረበት
ልዩ ክብር ካለው የተሰቀለበት...
አንችማ እናቱ - ማህፀን ዓለሙ
የሰውነት ልኩ - ሥጋውና ደሙ
እንዴት አትከብሪ!? እንዴት አትቀደሽ!?
እንዴት አትወደጅ!? እንዴት አትወደሽ!?
     + + +
እንኳንስ ለእኔና...
ለእርሱም ለጌታችን ፈጣሪ ለሆነ
እናቱ መባልሽ ይህ እውነት ከሆነ
እናቴ መሆንሽ እንዴት አልታመነ???
     + + +
በሥጋ ያይደለ በረቀቀ መንፈስ
እናቴ ሆነሽኝ ያንችን ክብር ብወርስ
ይሄንን መታደል እንዴት እገፋለሁ?
እናቱ እናቴ ነሽ! ተቀብየሻለሁ!!!
     + + +
ፈጣሪን ልትወልጅው አምላክን ልታ’ዥው
ሰማይና ምድር የማይወስኑትን-
                በእቅፍሽ ልትይዥው
ከድንግልና ጡት ወተት ልታጠቢው
የዓለሙን መጋቢ ከደኃ ማጀትሽ-
                ሲራብ ልትመግቢው
እናት አባትሽን ከእስር ልታስፈቺ
የክፋትን አባት በፍቅር ልትረቺ
ከሀና ከኢያቄም የተወለድሽ አንቺ
እናትና ድንግል ንግሥትና አገልጋይ
ሰማየ ሰማያት ጽርሐ አርያም ሆይ!
የአንቺ ግሩም ልደት ለእኔም ነው ልደቴ
የጥምቀት መሥራቹ ልጅሽ ነው አባቴ
ዳግም የተወለድሁ ከውኃና መንፈስ
ባንቺ መወለድ ነው የአዳም ተስፋው ሲደርስ
ሕይወት የሆነልን የልጅሽ ሥጋና ደም
ከአንቺው ነው የነሳው ከላይ አልወረደም
ዝም ማለት ያልቻልኩት ለዚህ ነው ድፍረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እና ነሽ - ልደትሽ ልደቴ
    + + +
(፡›አበው ስለክብርሽ ቃላት አጠራቸው
ስለ ደም ግባትሽ ምሳሌ ጠፋቸው
እኔ ግን ደፋሩ እዘባርቃለሁ
ባልበሰለ ብዕር - ቃላት እመርጣለሁ
በተንሸዋረረ ዓይን - ክብርሽን አያለሁ
ምልጃሽን እያሰብሁ በተስፋ እኖራለሁ‹፡)
       + + +
የብርሃን እናቱ የፀሐይ ምሥራቁ
የአዳም ሙሉ ተስፋ የሰይጣን መብረቁ
ስለ አንቺ መወለድ ዓለም ተፈጠረ
ስለ አንቺ መወለድ የሰው ልጅ ከበረ
አዳምና ዘሩ በኃጢአት ቢረክሱ
በአንቺ መወለድ ግን በክብር ነገሡ
በአንቺ ልዩ ልደት አዳም አምላክ ሆነ
በአንቺ ልዩ ልደት ክብራችን ገነነ
በአንቺ ልዩ ልደት ዲያብሎስ ታሰረ
በአንቺ ልዩ ልደት ባሪያ መሆን ቀረ
እኔም ደፋር ሆንኩኝ ፍርሃት ተሰወረ
ባዶው አዕምሮዬ ክብርሽን ነገረ፡፡
     + + +
ሰማይና ምድር ልደትሽን ሲያከብሩ
ሊቃውንት ሲቀኙ መላእክት ሲዘምሩ
ክብርሽን ተማምነው በምልጃሽ ያደሩ
በምህረት ቃል ኪዳን ለክብር ሲጠሩ
እንደልጅነቴ ለእኔም እንዲደርሰኝ
እንባሽን አስታውሶ ልጅሽ እንዲምረኝ
ዝም ማለት ያልቻልኩት ለዚህ ነው ድፍረቴ
የአንቺ መወለድ ነው የጽድቅ መሠረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እናቴ ነሽ - ልደትሽ ልደቴ፡፡
       + + +
.
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
በዓለ ልድት በሰላም አደረሰን - አደረሳችሁ !!!

Tuesday, April 12, 2016

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ?!?

(መላኩ አላምረው)
ብዙ ጊዜ ሲባሉ ከሚገርሙኝ ንግግሮች መካከል፡-
‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ጭፈራ ቤት ከከፈትሁ ወዲህ ጥሩ ገባያ እያገኘሁ ነው››
‹‹ፈጣሪ ፈቃዱ ከሆነ የመጠጥ ቤቱን አስፋፍቼና የመጠጥ ዓይነቶችንም ጨምሬ ለመስራትና ሀብቴን ለማሳደግ አስቤአለሁ… ሁሉም ፈቃዱ ይሁን!››
‹‹እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዓመት የዘፈን አልበሜን እጨርሳለሁ… በተለያዩ ጭፈራ ቤቶችም ሥራዎቼን በማቅረብ ገቢ አገኛለሁ፡፡ ከአምላኬ ጋር መጭው ጊዜ መልካም ይሆናል፡፡ ክብር ለእርሱ ይሁን!››
‹‹አምላክ ፈቅዶልኝ የዚህ ቢሮ ኃላፊ ብሆን… የምሠራውን አውቅ ነበር፡፡ በተለይ ምስኪን ቤተሰቦቼን ቀን አወጣላቸው ነበር››
…ሌላም ሌላም፡፡
ብቻ እኛ ሰዎች ስንባል… የምንናገረውን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ ወይም መጽሐፍ እንዳለ… ከእውቀት ማነስ የተነሳ ጠፍተናል፡፡ በእውኑ ሰው በሙስናና በዘረፋ፣ በመጠጥና በዳኪራ፣ በማጭበርበርና በወንጀል ለሚያገኘው ምድራዊ ኮተት የእግዚአብሔርን እርዳታና ፈቃድ ሰበብ ሊያደርግ ይችላልን? አንድ ሰው በስሜታዊ ባሕርይው ብቻ እየተነዳ የሚያደርገውንና የሚከናወንለትን ነገር ሁሉ የአምላክ ፈቃድ ነው ማለት እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርስ የሰው ልጅ በኃጢአት ሥራዎች ባገኘው ምድራዊ ድሎት ምክንያት ያመሰግነው ዘንድ የሚወድ አምላክ ነውን?
የእግዚአብሔር ፈቃድ መልካም ነገር ሁሉ እንጅ በተቃራኒው ኃጢአት የሆነና የሰውን ልጅ ስማታዊ አድርጎ ወደ ኃጢአት የሚመራ ነገር አይደለም፡፡ ከመልካም ነገር በተቃራኒ ያሉ ሰውንም በስሜት የሚነዱና ለኃጢአት ባሪያ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ አምላክ የፈቃዳቸው ናቸው ማለት የአፍ ልማድ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችም፡፡ ሰው በተሰጠው ነጻነት የሚያደርገውን፣ በራሱ የአዕምሮ ፈቃድና የልብ መሻትም የሚፈጽመውን ሁሉ አምላክ ፈቅዶልኝ ነው ይል ዘንድ እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርስ ሰው ይሰርቅ፣ ይዘሙት፣ ይገድል፣ ይቀማ፣ በስሜት እየተነዳ ይጠጣ፣ ይጨፍርና መንፈሳነቱን ይረሳ ዘንድ ፈቅዶ ከሰው ጋር የሚተባበር አምላክ ነውን? እንዲህ የምናስብ ከሆነ የአምላክን ባሕርይ አላወቅንም ማለት ነው፡፡ እነዚህን የሥጋ ፍሬዎች እንድናፈራ አምላክ ፈቅዶልናል፣ ረድቶናልም እያልን ፈጣሪን ከፍጡር ያውም በስሜት ከሚነዳ ዓለማዊ ሰው ጋር እየደመርነው እንደሆነም እናስተውል፡፡
አምላክ የሚፈቅደውና የሚወደው ሥራ ግን መልካምና ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላ ነው፡፡ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣት፣ እንግዳን መቀበል፣ የተራዘን ማልበስ፣ የታመመን መጎብኘት፣ የታሠረን መጠየቅ እና የመሳሰሉት ሁሉ መልካም ፈቃዱ ናቸው፡፡ ሰላምን መሻት፣ ፍቅርን መስበክ፣ ከስሜታነት ይላቀቅና በአዕምሮው ያስብ ዘንድ ሰውን ማስተማር፣ መከባበርንና መተሳሰብን ሕይወት ማድረግ ሁሉ ፈቃዱ ናቸው፡፡ ምድርን ማልማትና ፍሬዋን መብላት፣ በአግባብና በሥርዓት የሥጋን ፈቃድ መፈፈፀም፣ በተሰጠን አዕምሮ ተመራምሮ ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር  ሁሉ የተፈቀዱ ናቸው፡፡ (ሰው የፈጣሪነት ጸጋ ተሰጥቶታልና)፡፡
(፡› ነገር ግን የሰውን ልጅ ከአዕምሯዊነትና ከመንፈሳዊነት ባሕርይው ይልቅ በስሜታዊ ባሕርይው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ በግብታዊነት ይኖር ዘንድ ቀፍድደው የሚይዙ ነገሮችን ሁሉ ባደረግን ጊዜ… ይህ በተሰጠን ነጻ ፈቃድና ምርጫ ተጠቅመን የምናደርገው እንጅ ፈጣሪ ፈቅዶልን እያገዘንም የምናደርገው አይደለም፡፡ አምላክ ለሰው ልጅ ነጻ ፈቃድና ምርጫን ያለገደብ መስጠቱ የነጻነት አምላክ መሆኑን እንጅ የኃጢአት ተባባሪነቱን አያሳይም፡፡ ይህ ራሳችንን እያጸደቅንና ለክፋታችን ይቅርታ እያደረግን የመኖር ልምምድ አወዳደቃችንን ያከፋው ካልሆነ በቀር የሚጠቅመን አነዳች ነገር የለም፡፡
የሰው ልጅ በምድር ብቻ የተወሰነ ሕይወት እንዳለው ካሰበ ግን… ኃጢአትና ዘራዝርቱ ሁሉ ለጊዜውም ቢሆን ይስማሙታል፡፡ ራሱን ጻድቅ እያደረገና ወንጀሉን በድፍረትና በማናለብኝነት እየፈጸመ ይኖራል፡፡ ይህንንም አምላክ ፈቅዶልኝ ነው ሊል ይችላል፡፡ ይህ ግ የአለማወቅና የአለማስተዋል ጥግ ነው፡፤ አምላክስ ከመልካም ነገር ውጭ እናደርግ ዘንድ የሚፈቅድ ባሕርይ የለውም፡፡ መልካም ነገርን ማያደርግና በተቃራኒው የተሰለፈ ሁሉም ከእርሱ ጋር ኅብረት የለውም፡፡
ለራሳችን ኃጢአት ራሳችን ይቅርታ እያደረግን የመኖር ልምምድ አወዳደቃችንን ያከፋዋልና ወደ ሕሊናችን እንመለስ፡፡

Tuesday, March 8, 2016

የጾም ነገር ! (1)



(መላኩ አላምረው)
‹‹ይቅርታ አድርጉልኝና ጋሽ ጣሰው… በዓለም ላይ ከሚገኙና ሃይማኖታዊ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ሀገሮች ውስጥ እንደ ኢትዮጵያውያን የሚጾም አለ ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያውያን ጾም ለሀገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ መፍትሔን ሳይሆን ችግርን ከሰማዬ ሰማያት እያወረደ የሚደምር… የሚከምር… የሚጭን… መስሎ ከታዬኝ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ጾም ቢቆም የተሻለ ቀን የሚመጣ ይመስለኛል…›› አለ የኪራይ ጓደኛዬ ፈላስፋው ጣሴ የዐቢይ ጾምን በጀመርንበት የመጀመሪያ ቀን ምሽት፡፡ ጣሴ መጠየቅ ይወዳል፡፡ ሰው ዝም ሲል አይወድም፡፡ ብዙ ጊዜ ዝምታዎችን የሚሰብርበት መንገድ ደግሞ ጥያቄ ማንሳት ነው፡፡
ትላንትና ምሽት ከአከራያችን ከጋሽ ጣሰው ቤት የጾሙን መጀመር ምክንያት በማድረግ ቡና እንድንጠጣ ተጠርተን ገባን - ጣሴ እና እኔ፡፡ በጥቁር ቡና ግብዣው ላይ እኛ አይተናቸው የማናውቅ የጋሽ ጣሰው ጎረቤቶችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ መምህሬ ለይኩንን አይተናቸው አናውቅም፡፡ (ተከራይ የአከራዩን ጎረቤቶች ሳያውቅ የሚኖርባት ከተማ አዲስ አበባ ናት የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም ትላንት ግን ውስጤን የተሰማው ስሜት የባዕድነት ነበር፡፡ በጋሽ ጣሰው ግቢ ከ2 ዓመት በላይ ስንኖር ቢያንስ መምህሬ ለይኩንን የመሰለ ሊቅ ጎረቤት ማወቅ አልነበረብንም?)
የጣሴን የዝምታ መስበሪያ ጥያቄ በሌላ ጥያቄ በመመለስ የቀጠሉት መምህሬ ነበሩ፡፡
‹‹ለእኔም ይቅርታ አድርግልኛና… ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊት ጾምን የሚጾማት ምዕመን ቁጥር ስንት ይሆናል? እንዴት ባለ ጥናት ላይ ተመርኩዘህ ነው የእኛን ሀገር ጿሚዎች ቁጥር ከሌላው ዓለም ከፍ ያደረግኸው?››
(፡›መምህሬ ለይኩን በ50ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ ያሉ ጎልማሳ ቢሆኑም የፊታቸው ቆዳ መሸበሸብና የወገባቸው መጉበጥ… ባጠቃላይ የሰውነታቸው ሁኔታ የ70 እና የ80 ዓመት ሽማግሌ አስመስሏቸዋል፡፡ ጎረቤቶቻቸው እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች በሚነሱ የሃይማኖት ነክ ውይቶች ላይ የሚሰጡትን ጥልቅ ማብራሪያ መሠረት በማድረግ ‹‹መምህሬ›› ይበሏቸው እንጅ በየትኛውም ደብር አያገለግሉም፡፡ በትምህርት በኩል ግን የሐዲስ ኪዳን መምህርነት ምስክር አላቸው፡፡ ቅኔና አቋቋምም ተምረዋል፡፡ ልክ የዛሬ 15 ዓመት ከጎጃም መጥተው አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ አድባራት ውስጥ በአንዱ ለመቀጠር ቤተ-ክህነቱን ደጅ ቢጠኑም ‹‹ሲሆን 7ቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ካልሆን ደግሞ 5ቱን አዕማደ ምሥጢራት አጥንተህ ተመልሰህ ና፤ ከዚያ ትቀጠራለህ፡፡ ያለበለዚያ በከንቱ አትድከም›› የሚል መልስ ተሰጥቷቸው ይህንን ማድረግ ስላልቻሉና በአሠራሩም እጅግ ስላዘኑ መጽሐፍ አዟሪ ሆነው ቀሩ፡፡ የተጠየቁት ምሥጢር ሳይሆን 7 እና 5 ሺህ መሆኑ ሲገባቸው አዕምሯቸው ቆስሎ እንደቀረ በምሬት ይናገራሉ፡፡)
ጣሴ በመምህሬ ድንገተኛ ጥያቄ ደንገጥ ብሎ… ‹‹ይሄ እኮ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ የሀገራችን ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም በጾም አይታማም፡፡ በአጽዋማት ወቅትም አድባራቱና መስጂዶቹ ሁሉ በሕዝብ ይጨናነቃሉ፡፡ በተለይ በዓቢይ ጾምማ ይለያል፡፡ ሳይቀደስበት የሚውል ደብርና ገዳም የለም፡፡ እ….›› እያለ ነገር ሊያሰፋ ሲል መምህሬ አቋረጡት፡፡
‹‹ይቅርታ አድርግልኝ ወንድሜ… የምትለው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ‹መንፈሳዊት ጾምን› አይገልጽም፡፡ በልማድ የሚደረግንና በብዙ ሕዝብ የታጀበን ጾምና ቅዳሴ በመመልከት ብቻ ‹የሃይማኖተኞች ሀገር ፣ ሀገረ እግዚአብሔር … ምናምን› እያሉ መተረት ትርጉም የለውም፡፡ ወዳጄ… ለአንተና ለመሰሎችህ ብዙ ያልተገለጠላችሁ ነገር አለ፡፡ በተለይ የሀገራችን ሃይማተኝነት ጉዳይ፡፡ የጠመጠመ ሁሉ ቄስ አይደለም፡፡ ለንግሥ የሚወጣ ሁሉም ሃይማኖተኛ አይደለም፡፡›› አሉ መምህሬ ሀዘን በሚነበብበት አነጋገር፡፡
‹‹ንግግርዎት ሊገባኝ አልቻለም… ሃይማኖት በተከታዮቹ ቁጥር እንጅ በምን ይለካል? ጾምስ በጿሚው ምዕመን ካልሆነ በምን ይታወቅ?›› አለ ጣሴ ግራ በተጋባው ስሜት፡፡
ጋሽ ጣሰው ጣልቃ ገብተው… ‹‹አይ ጣሴ… ምነው ፈላስፋ ነኝ ምናምን እያልህ ስታደነቁረንም አልነበር? እንዴት የመምህሬ ንግግር አልዘለቀህም ጃል? ነው ፍልስፍና የሃይማኖትን ነገር ማለቴ የጾምንና አጿጿሙን ጉዳይ አያካትትም? አሂሂ… ያንተ ፍልስፍና ሊታይ ነዋ!›› አሉት ፌዝ በተቀላቀለበት ድምጸት፡፡
‹‹በሃይማኖት ውስጥ ‹አምኖ መቀበል› እንጅ ፍልስፍና ቦታ እንደሌላት ስለማውቅ ነዋ !›› አለ ጣሴ ለጋሽ ጣሰው ጥያቄ መልስ፡፡
‹‹አይ… እንደዚህ አይነት መረዳት አይኑርህ ወዳጄ ! ፍልስፍና ጥበብ ነው፡፡ ጥበብን በማስተናገድ በኩል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን የሚቀድምም የሚበልጥም የለም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ ዘመን የሥጋውያንና የብዑላን መሰብሰቢያ ሆነች እንጅ…›› መምህሬ ለይኩን ተናገሩ፡፡ ፊታቸው ሀዘን እንጅ ቁጣ አይነበብበትም፡፡
‹‹የጾሙን ጉዳይ ያጠቃሉልንማ… መምሬ›› አሉ ጋሽ ጣሰው የመምህሬን ንግግር መርዘም ያልፈለጉ በሚመስል ጣልቃ ገብነት፡፡
‹‹የጾሙ ጉዳይማ… ባጭሩ በሀገራችን በተለይም በከተማችን ‹መንፈሳዊት ጾም› እየተጾመች ስላልሆነ ነው ልጁ (ጣሴን ነው) ያለውን ሁኔታ የምናስተውለው፡፡ በየደብሩ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ኪዳን ይደረሳል፤ ሕዝቡም በተለይ በዓላትንና አጽዋማትን እየጠበቀ ይሰበሰባል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በዓለማውያን ዘንድ እንኳን የሌለ ዘረኝነትና አድሏዊነት፤ ጥላቻና መገፋፋት ያለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ… ያውም አገልጋዮች ነን በሚሉትና በተለያዬ የሊቅነት ማዕረግና ሥልጣን በተሸከሙት ዘንድ ነው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ውጩ ነጠላ ለብሶ እንደሚታየው ንጹህ አይደለም፡፡ ከተንኮልና ከክፋት ሳይጾሙ ከእህልና ውኃ ቢከለከሉ ምን ትርጉም አለው? ከክፉ ሥራ ሁሉ ርቀውና ንሰሐ ገብተው ያልጾሙት ጾም… ልጁ እንዳለው ምን አልባት መዓትን እንጅ ምህረትን እንዴት ሊያመጣ ይችላል? መነፈሳዊት ጾምስ እንዲህም አይደለች፡፡››
መምህሬ ይህንን እንዳሉ በቀጣይ ተገናኝተን ስለ ብዙ ጉዳዮች እንደምንነጋገር ቃል አስገብቻቸው ወጣሁ፡፡
ሰላም ይብዛልን !

Monday, February 22, 2016

ዓባይ ለምን ጨሰ ?

ረጅም ወንዝ ሆኖሚፈሰው ዘላለም
ለካስ ዓባይ ማለት ውኃ ብቻ አይደለም 
ጭስ ነው በመንፈሱ እሳት ነው ካሉ
ሆድ ሲብሰው ጭሶ ያቃጥላል አሉ
ይኸው አየሁ ባይኔ ዓባይ እሳት ሆኖ
ውስጡ ሲንቀለቀል በነጭ ጭስ ታፍኖ
የእሳቱ ነበልባል ቁልቁል ሲወረወር
የሚታየው ዓባይ በብሶት ሲዘረር
ምን ጎድሎበት ይሆን እንዲህ የሚጨሰው
በክብር በዝና ዓለምንሚያደርሰው
እኔ በእኔው ሀሳብ እንዲያው ስመረምር
ዓባይ እሳት ሆኖ የመጨሱ ምሥጢር
ስደቱ ታይቶት ነው ከአገር መውጣቱ
ጣናን እንዳለፈ ሲጨስ መታየቱ
ምን በስም ቢገኑ ታውቀው ቢከበሩ
ከባህል ከእምነት ጋር በሀገር ካልኖሩ
መች ሰላም ይሰጣል መች ኑሮ ይደላል
ውስጥ የታፈነ ሳት ጭሶ ያቃጥላል!!!
...

(መላኩ አላምረው- ሚያዝያ 24/2006- ጭስ ዓባይ ከፏፏቴው ጥግ)