[መላኩ አላምረው]
ዕለተ ሚካኤል ጠዋት ነው፡፡ ሰዓት ሳይረፍድብኝ
ለትምህርት ለመድረስ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍጥነት በመጓዝ ላይ ነበርሁ። ዕለቱ የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል በመሆኑ
በቅ/ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ምዕመናን እንደሚበዙ ብገምትም ከ6 ኪሎ ሰማዕታት ሃውልት ጀምሮ መንገዱ ይዘጋጋል ብዬ ግን
አላሰብኩም ነበርና ወደ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ ለመግባት አምስተኛ በርን ምርጫዬ አደረግሁ። ልክ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልቱን
እንዳፍኩ ጀምሮ ግን አይደለም በፍጥነት ተጉዤ በሰዓቱ ክፍል መግባት ቀርቶ ለመንቀሳቀስም ተቸግርሁ። ከአስፓልቱ የቀኝ ጠርዝ
እስከ ዩኒቨርስቲው አጥር ድረስ የጤፍ መጣያ እስኪጠፋ ድረስ በሸቀጣሸቀጦችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም በሰዎች ተሞልቷል።
ሰው ማለፊያ ሲያጣ ወደ አስፓልቱ እየገባ፣ መኪኖቹንም
ግራ እያጋባቸው፣ ሾፌሮችም እየተቆጡና ክላክስ እየነፉ. . . ይህ ሁሉ ደግሞ ከሸቀጣሸቀጥ ግዙን ባዮች ልፈፋ፣ በሞንታርቦ
ከተለቀቁ መዝሙሮች “ጩኸት”፣ ከ “ባህታውያን” ነን ባዮች “ስብከት” ጋር ተደማምሮ ለአካባቢው ልዩ ትዕይንትን ፈጥሯል።
አንዳንዴ መርካቶን፣ አንዳንዴ መዝሙር ቤቶችን፣ አንዳንዴ ደግሞ የሀብታም ሰርግን (የታክሲዎችን ክላክስ) ያስታውሳል። ውስጤን
ሁለት ሀሳቦች ወጠሩት፡ አንደኛው የትምህርት ሰዓቴ መርፈድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስመቼ እንዲህ ይደረጋል? ለምን እንዲህ
ይሆናል? ይህን የማስቆም ኃላፊነቱስ የማነው? የሚለው የብስጭት ሀሳብ። ወርሃዊ በዓላት በመጡ ቁጥር አብያተ ክርስቲያናት ወደ
ገበያ ማዕከልነት ይለወጡ የሚል ህግ ወጣ እንዴ?(ብዙ ህጎች ደርሰው ስለሚወጡ)፣ ወይስ እኔ ያልሰማሁት ልዩ ዐውደ ርዕይ ይኖር
ይሆን? የዛሬው ደግሞ ልዩ ነው። እንዲህ ሰው መንቀሳቀሻ እስከሚያጣ ድረስ. . . ግሩም ነው መቼም። እሺ ቤተ ክርስቲያን
ለመሳለም የሚፈልጉ እንዴት ይለፉ?
በርካታ ሀሳቦችን በአዕምሮዬ ሳውጠነጥን ከጫጫታው መሀል
የአንዲት እናት ድምፅ ጎልቶ ተሰማኝ። “የህግ ያለህ! ኧረ የዛሬውስ የጉድ ነው ወገኖቼ. . . ሰው ለማን አቤት ይላል?ኧረ
እባካችሁ አሳልፉኝ ስለት አለብኝ. . .” እጅግ በጣም ያመረሩ ይመስላል ሴትየዋ። ሲናገሩ ጉሮሯቸውን ሲቃ ይተናነቀዋል።
ዓይኖቻቸውም እምባ አዝለዋል። ጩኸታቸውን ግን ማንም አያዳምጥም። መልስም የሚሰጣቸው የለም። “ሕግ ሆይ! ወዴት ተሰደድሽ?. .
.” ሴትየዋ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መጮሃቸው ቀጠሉ። በዙሪያቸው ያለው ሰው በመደናገጥም በመገረምም ዓይኑን ወደርሳቸው
አዞረ። የሚናገሩት ኃይለ ቃል ውስጤን ነካው። ‘ክላስ’ በሰዓቱ እንደማልደርስ ሲገባኝ ተስፋ ቆረጥሁ። እንዴት አልፌ? በሴትዮዋ
ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሴትየዋ ንግግር ዙሪያ የተለያየ አስተያየት መስጠት ጀመሩ። አንዳንዱ “ልክ ናቸው ሴትዮዋ። ምን ህግና
ሥርዓት አለ? ህግ ቢኖር እንዲህ የቤተ ክርስቲያን መሳለሚያ እናጣ ነበር?” ይላል። ሌላው ደግሞ “ቢጨንቃቸው እኮ ነው። ዝም
ብለው ቢጋፉና ቢያልፉ ይሻላል። ማን ይሰማኝ ብለው ነው አሁን እንዲህ የሚጮኹት . . .ሆ!ሆ!” እያለ ያሽሟጥታል። አንዳንዱ
የባሰበትም “እባክዎትን እርስዎም ብሰው አያድርቁን። ሄደው ፖሊስ ጣቢያ አይጮሁም ከፈለጉ?” በማለት የበለጠ ሆድ ያሰብሳቸዋል።
እንደምንም ተጋፍቼ ወደ እርሳቸው ተጠጋሁና “አይዞዎት
ማዘር እንደምንም ተጋፍተን እንለፈው” አልኳቸው። “አይ ልጄ.. . የመጣብን ጉድ ተጋፍተን የምናልፈውም አይመስልም። አቅም
ካላችሁ ሞክሩ” አሉኝ። በንግግራቸው ትንሽ ግራ ተጋባሁና “ንግግርዎት በደንብ ግልፅ አልሆነልኝም” አልኋቸው። “ነገርኩህ ልጄ።
እኛ ይሄን ችግር የመጋፋት አቅም ያለን አይመስለኝም። ጩኸታችንን የሚሰማም የለም። ቤተ ክርስቲያን ዝም። መንግስትም ዝም።
ሥርዓት ጠፋ። አሁን ይሄ ለማን አቤት ይባላል? ሰላማችን እኮ ጠፋ። ሰው ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ፣ መንፈሱን አድርሶና ሰላም
አግኝቶ ለመመለስ ነው የሚመጣው። ግን ሰላም የት አለ? ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከሚመጣው እኮ ለገበያ የሚመጣው በዛ። ቅዳሴ
ከሚያስቀድሰው እኮ የጎዳና ላይ የሞንታርቦ መዝሙር የሚያዳምጠው በዛ። አሁን የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ነበር?” ብለው
እኔን አፍጠው ተመለከቱኝ።
ከእኔ መልስ የሚሹ ስለመሰለኝ ደንገጥም ፈራም አልሁና
“ኧረ ልክ ነዎት. . .ኧ. . .” ብዬ ያሰብኩትን ሳልናገር “ተመልከት” አሉኝ አንድ ባህታዊ ነኝ ባይን ከበው ወደ ቆሙ
ሰዎች እየጠቆሙኝ። “ተመልከት እንግዲህ። ሥርዓተ ቅዳሴው በቤተመቅደስ እየተካሄደ ምዕመኑ በሥርዓቱ መሰረት ከካህናቱ ተሰጥኦ
እየተቀበለ ማስቀደስ ሲገባው አንድ አወናባጅ መነኩሴ ነኝ ባይ ከቦ ቆሞልሃል ደግሞ እኮ እነዚህ የሀሰት ባህታውያን ሰላምን
የሚሰብኩ እንዳይመስልህ፤- ጠብን እንጅ። “እስኪ ና ቀረብ ብለህ ስማ” አሉኝና አብረን ጠጋ አልን። ‘ባህታዊው’ አነስተኛ
የድምፅ ማጉያን በመጠቀም እንዲህ ሲል ሰማሁና ደነገጥሁ። “ምዕመናን፣ በአሁኑ ሰዓት ካህን ያለ እንዳይመስላችሁ። ሌባ ብቻ
ነው። መንግሥትም ሌባ ነው።
ጳጳሳትም ፖለቲከኞች ናቸው። መንግሥት ጳጳሳትን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው. . . የመጨረሻው ዘመን ስለሆነ በሽታው፣
ጦርነቱ፣ መቅሰፍቱ በዝቷል.. …. ‘ምዕመናን እጅግ ፈዋሽ የሆነ ከኢየሩሳሌም የመጣ ቅብዓ ቅዱስ ስላለ እየገዛችሁ’. .
.ከሁሉም በሽታ ትፈወሳላችሁ . . . እናም ካህናትን አትመኗቸው...” ገረመኝ። እውነትም ሴትዮዋ ልክ ናቸው። እንዴት ነው
ነገሩ?
እውነትም የህግ ያለህ ማለት ይሄኔ ነው። ይህ ጉዳይ እኮ
እንደቀላል መታየት የለበትም። ጋዜጦች ብዙ ፃፉ - ዝም። ሕዝብ በየጎዳናው ምሬቱን ያሰማል - ዝም። በእንደዚህ ዓይነት
ግርግሮች በርካታ ሰዎች ሞባይልና ሌላ እቃ እየተሰረቁ ያለቅሳሉ - ዝም። ለመሆኑ እነዚህን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዙሪያ
የሚካሄዱ ንግዶችንና ከስርዓት ውጪ የሆኑ የመዝሙርና የ‘ባህታውያን’ ጩኸቶችን የማስቆም ኃለፊነቱ የማነው? የቤተክርስቲያን
ወይስ የመንግሥት? እስከመቼስ በዚህ መልኩ ይቀጥላል? እስመቼስ ዝም ይባላል? ለመሆኑ ማን ፈቅዶላቸው ነው ወርሃዊ በዓላትን
እየጠበቁ ሸቀጥ የሚዘረጉ ‘ነጋዴዎች’ የዋህ ምዕመናንን የሚረብሹት? በየትኛው ሥርዓትስ ነው መዝሙር ሻጭ ነን ባዮች በሞንታርቦ
ድምፅ በሥርዓት እያስቀደሱ ያሉ ምዕመናንን የሚረብሹት? ምንም ፈቃድ ሳይኖራቸው በየመንገዱ እየቆሙ በህዝቡ ዘንድ መለያየትንና
ጥላቻን የሚሰብኩ ባህታውያን ነን ባዮችስ ጉዳይ ማንነው የሚመለከተው?ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ማን ሥርዓት ያስይዝ?
ቤተክርስቲያንና መንግሥት ሆይ! እባካችሁ በዚህ ጉዳይ
ላይ የየድርሻችሁን ተወጡ። ለህዝቡ ሰላም አይገዳችሁምን? ቤተ አምልኮና የንግድ ቦታ መለያየት የለበትምን? ፈቃድ የሌላቸው
አወናባጆችስ በየጎዳናው የጥላቻና የመከፋፈል ስብከትን ለህዝቡ ያዳርሱ ዘንድ ተፈቅዷልን? ቤተክርስቲንና መንግሥት ድርሻችሁን
ለይታችሁ አውቃችኋልን? እውነት ይሄ ጉዳይ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ታስቦበታልን?
መንግሥት ያላት ሀገር ሕግ ማስከበር ካቃታትና ሲኖዶስ
ያላት ቤተክርስቲያን ሰባኪዎቿንና ዘማሪዎቿን በሥርዓት ካላሰማራች ማን መጥቶ ህግና ሥርዓት ያስከብር? ይከብዳልም፤ ይገርማልም።
የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሆይ! የመዝሙር አገልግሎት ‘ቢዝነስ’ ነወይ? ያውም ከሸቀጣሸቀጦች ጋር አብሮ ተሰልፎ ግዙኝ ብሎ
በመለፈፍ? ኧረ ይሄ ነገር ያሳፍራል እኮ። መንፈሳዊ አገልግሎትን ለሀብት መፍጠሪያ ለማዋል ሲባል ሥርዓተ ቅዳሴውን በመረበሽ.
. . ጉድ እኮ ነው። ማስተዋል ይገባናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና መንግሥት ይህን ጉዳይ ሥርዓት
ለማስያዝ ብትተባበሩ መልካም ነው እላለሁ።