የጉዞ ማስታወሻ

የዓለም ቱሪዝም ቀን አምናና ዘንድሮ - ከአፍሪካ ጣሪያ ወደ ዓለም መሠረት!

v  በመላኩ አላምረው

እንደ መንደርደሪያ፡-
ጣሪያና መሠረት የሚሉ ቃላት ከቤት አሠራር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ጣሪያና መሠረት ባንድ ላይ የሌለው ቤት በራሱ ቤት ተብሎ ሊጠራ አይገባውም፡፡ መሠረት ከሌለው ጣሪያው አይቆምም፡፡ ጣሪያ ከሌለው ደግሞ የመሠረቱ መኖር ትርጉም የለውም፡፡ ከፀሐይም ሆነ ከዝናብ አያስጥልም፡፡ ማንም ሊኖርበት አይመኘውም- አማራጭ ከሌለው በስተቀር፡፡ አገርም እንደ ቤት ናት፡፡ ሁሉንም ልጆቿን ሰብስባ የምታኖር ታላቅ ቤት፡፡
የእኛ ኢትዮጵያም ታላቅ ቤታችን ናት፡፡ ሲከፋንም ሆነ ስንደሰት የምንጠለልባት የፍቅር ቤታችን፡፡ ይህች አገር መሠረትና ጣሪያ አላት፡፡ መሠረትና ጣሪያ ባይኖራትማ ኖሮ እንደዚህ በክብርና በፍቅር አንኖርባትም/አታስኖረንም ነበር፡፡ ጽኑ መሠረትና ጠንካራ ጣሪያ ስላላት አባቶቻችን ኖሩባት፤ እኛም እየኖርንባት ነው፤ ልጆቻችንም ይኖሩባታል፡፡ ልጆቻችን ይኖሩባት ዘንድ ደግሞ መሠረቷንና ጣሪያዋን የበለጠ ማጽናትና ማጠናከር ከእኛ ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል፡፡ የአገር መሠረትነትና ጣሪያነት ትርጉሙ ጠለቅ ያለና ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ስለሆነ እይታችንን ወደ አንድ አቅጣጫ እናድርገው፡፡ ወደ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና ወደ ሰው ዘር መነሻነት…..
ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረትና ጣሪያ ያላት ቤት ብቻ አይደለችም፡፡ ለዓለምም መሠረትነት አላት፡፡ ለዓለም መሠረትነቷ ምንድነው? ይህች አገር ጣሪያ ያላት ቤት ብቻም አይደለችም፡፡ ለዓለም በተለይም ለአፍሪካ ጣሪያነት ያላት ድንቅ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጣሪያነቷ ከምን አንፃር ይሆን? ይህንንስ ከቱሪዝም በተለይም ከዓለም ቱሪዝም ቀን ጋር ምን ያገናኘዋል? ይህ ጽሑፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡ ሌሎችንም ከአምናና ዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀናት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል የተባበሩት መንግስታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ለተመሠረተበት ቀን (መስከረም 17/September 27 እኤአ 1970) መታሰቢያነት በየተራ በሚመረጥ አገርና ወቅቱን ባገናዘበ ልዩ መልእክት ታጅቦ በሁሉም አባል አገራት ዘንድ እኤአ ከ1980 ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ ለዚህ በዓል የተመረጠው መሪ መልእክት በዕለቱ ብቻ እንደ መፈክር ተነግሮና ተደምጦ የሚታለፍ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር ተጣጥሞ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን በየዓመቱ በድምቀትና በልዩ ትኩረት የመከበሩ ዋና ዓላማም ቱሪዝም ለዓለም አቀፍ ማህበረስብ የሚያበረክተውን ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የአካባቢ ጥበቃ/እንክብካቤ እና ፓለቲካዊ ፋይዳዎች በአጽንኦት በማሳየት ለዓለም ማኅበረሰብ ሁሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ለዚህ በዓል ሲባል የሚመረጠው መሪ ቃልም ሆነ የሚተላለፈው መልእክት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሌኒየም ግቦች (MDGs) ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ነው፡፡ ይህ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓልም በዋናነት የመንግሥታቱን ድርጅት የሚሌኒየም ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ርብርቦሽ ውስጥ ለሚያጋጥሙ መሰናክሎችና ፈታኝ ሁኔታዎች እንደ መፍትሄ ጠቋሚ ብቻ ሳይሆን ዋናው የመፍትሄ አካል ተደርጎም ይወሰዳል፡፡  
ኢትዮጵያ እንደ አባል አገር የዓለም ቱሪዝም ቀንን ማክበር ከጀመረች እነሆ አሁን ለ27ኛ ጊዜ ሲሆን በየክልሉ በመዘዋወር በጋራ ሲከበር ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ ነው፡፡ የመጀመሪያውን አገራዊ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል በክልል ደረጃ ያከበርነው በ2001 ዓ.ም. በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልል የጋራ አዘጋጅነት ነበር፡፡ ሁለተኛውን በ2002 ዓ.ም. በሀረሪ ክልልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ሦስተኛውን በ2003 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ አራተኛውን በ2004 ዓ.ም. በትግራይ ክልል፣ አምስተኛውን በ2005 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስናከበር በ2006 ዓ.ም.ማለትም የአምናውን የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል ደግሞ በአማራ ክልል አክብረናል፡፡
በሁሉም ክልሎች የተከበሩት በዓላት የየክልሉን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች በስፋት በመጎብኘትና ለኅብረተሰቡ ስለ ቱሪዝም ምንነት የሚፈጥሩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማከናወን ነበር፡፡ የቱሪዝም ባለድርሻ አካላትም ሆኑ የመስህቦች ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ በቀጥታ የተሳተፈባቸው እነዚህ የዓለም ቱሪዝም ቀናት በየክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሳደሩት አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በየዓመቱ በሚዘጋጁት የቱሪዝም ሲምፖዚየሞች ላይ በአራዊም ሆነ በየክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ተጠንተው የቀረቡና ውይይት የተደረገባቸው የጥናትና ምርምር ጽሑፎችም በርካታ ተሞክሮዎችን የተለዋወጥንባቸው፣ ችግሮችን ያሳዩና መፍትሔዎችንም የጠቆሙ ስለነበሩ ለዘርፉ ለውጥ መነቃቃት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡
በአንዳንድ ክልሎችም የዓለም ቱሪዝም ቀንን መከበር ምክንያት በማድረግ በተደረጉ ውይይቶችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ በተለይም የየክልሉን ፕሬዝዳንቶችና ወሳኝ አካላትን ባካተተ መልኩ በተደረጉ መግባባቶች በዘርፉ በነበሩ የአደረጃጀት ክፍተቶች ላይ ማስተካከያዎችን እስከማድረግ ድረስ ተችሏል፡፡ በየዓመቱ በበዓሉ ላይ በሚሳተፉ የመንግሥትም ሆነ የግል ብዙኃን መገናኛዎች አማካኝነትም የየክልሉን ቱባ ባህልና እምቅ የቱሪዝም ሀብት በስፋት ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ በየዓመቱ በተለይም መስከረም ወር ላይ የአገራችን ኅብረተሰብ ከዳር እስከ ዳር ስለቱሪዝም እንዲያወራና እንዲወያይ ለማደረግ ሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ ወቅት በየደረጃው ቀኑን በደማቅ ዝግጅት እያከበሩት ይገኛሉ፡፡ ከዋናው በዓል ቀጥሎ በሚከናወኑ የብዙኃን መገናኛዎች ዘገባና ሌሎች ተከታታይ ሥራዎች አማካኝነት ቱሪዝም ዓመታዊ አጀንዳ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ በየክልሉ በመዘዋወር የሚከበረው ይህ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል እጅግ ደማቅ፣ የሁሉንም ቀልብ የሚስብና ለዘርፉ ለውጥ የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ተወዳጅ ዝግጅት እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ዓይነተኛ መንገድ እየሆነ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመትም ከአገራችን ክልሎች ብቻ ሳይሆን ከዓለምም ጭምር እጅግ ዝቅተኛው ቦታ (Danakel Depression) መገኛ ወደሆነውና የዓለምን ቱሪስቶች ቀልብ እየሳበ የሚገኘው የኤርታ-አሌ የማያቋርጥ እሳተ ገሞራ (Arta-Alle Active Volcano) ወደሚገኝበት የአፋር ክልል በመጓዝ ዝግጅቱን በድምቀት እናከብራለን፡፡ በዚህ ልዩ ዕትማችንም የክልሉን መስህቦች ባጭሩ እናስቃኛችኋለን፡፡ ስለ አምናው የዓለም ቱሪዝም ቀን ትውስታ እንዲኖራችሁም በተወሰነ መልኩም ቢሆን  ወደ ኋላ ሄደን ከዚህ ዓመቱ በዓል ጋር በማስተሳሰር ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡
የየበዓላቱን መሪ መልእክታትና የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ፣ በዓላቱ የተከበሩበት/ የሚከበሩበት ክልልና የመሪ ቃላቱ ልዩ አጋጣሚያዊ ትስስር፣ የነበሩ/የሚኖሩ ልዩ ገጽታዎችና ሌሎችም ጉዳዮች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ፡፡ ዓባይ በሕዳሴ ግድብነት ከትሞ የአገራችንን ታላቅነት ለማሳየት ወደ ጉባ (ቤኒሻንጉል) ለመጓዝ ከተፀነሰባቸውና ረጃጅም እግሮቹን ከዘረጋባቸው የጎጃምና የጎንደር ተራራዎች ተነስተን የሚወለድበትን ጣናንና የልደት አጃቢዋን/አድማቂዋን ውቢቷ ባህር ዳርን ቃኝተን እጅግ በፈጠነ ጉዞ ወደ አፋር እንወረወራለን፡፡
በፈጣኑ የወፍ በረር ጉዟችንም አፋርንና ድንቃድቆቿን እየጎበኘን በአማራዎቹ የሰሜን ተራራ በረዶና በዓባይና ጣና ውኃ ቅዝቃዜና ብርድ ሲሰማን ከአፋሩ ኤርታ-አሌ እሳት እንሞቃለን፡፡ በአፋር በረኃና በኤርታ-አሌ እሳት ሙቀት ሲሰማን ደግሞ ወደ ሰሜን ተራራ በረዶና ወደ ጣና ሐይቅ በትዝታ መለስ ብለን ቀዝቀዝ እንላለን፡፡ ሁሉም በቤታችን አለ፡፡ ሜዳው፣ ተራራው፣ ሙቀቱ፣ ቅዝቃዜው፣ ሐይቁ፣ አሸዋው፣ ጫካው፣ ብርቅዬ አዕዋፍና የዱር እንስሳት….. የፈለግነው ሁሉ አለ፡፡ ምክንያቱም ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ዓይናችን የሚራበውም ሆነ በማየት የሚሰለቸው ነገር አይኖርም፡፡ ለዓይናችን፡- እነሆ የመስህብ በየዓይነቱ!….. ጉዟችን ከጣሪያ ወደ መሠረት- ከበረዶ ወደ እሳት ነው፡፡ መልካም ጉዞ!....to be continued...

No comments: