Friday, May 9, 2014

ድፍረት ባይሆንብኝ…


ሰማየ ሰማያት ጽርሐ አርያም ሆይ!
ከልጅሽ አማልጅን ክብርሽን እንድናይ
አስኪ ክብር ባገኝ ልጻፍ ስለክብርሽ
ድፍረት ባይሆንብኝ እኔም ላመስግንሽ
       *  *  *  *  *  *
የአንቺ ግሩም ልደት ለእኔም ነው ልደቴ
የጥምቀት መሥራቹ ልጅሽ ነው አባቴ
ዳግም የተወለድሁ ከውኃና መንፈስ
ባንቺ መወለድ ነው የአዳም ተስፋው ሲደርስ
ሕይወት የሆነልን የልጅሽ ሥጋና ደም
ከአንቺው ነው የነሳው ከላይ አልወረደም
ዝም ማለት ያልቻልኩት ለዚህ ነው ድፍረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው ልደትሽ ልደቴ
      *  *  *  *  *  *
አበው ስለክብርሽ ቃላት አጠራቸው
ስለ ደም ግባትሽ ምሳሌ ጠፋቸው
እኔ ግን ደፋሩ እዘባርቃለሁ
ባልበሰለ ብዕር ቃላት አምጣለሁ
በተንሸዋረረ ዓይን- ክብርሽን አያለሁ
ምልጃሽን እያሰብሁ በተስፋ እኖራለሁ
      *  *  *  *  *  *
የብርሃን እናቱ የፀሐይ ምሥራቁ
የአዳም ሙሉ ተስፋ የሰይጣን መብረቁ
አሳሳች መናፍስት እጅግ የረቀቁ
እኛኑ ለመጣል ክፋት የሰነቁ
ሰው ዳግም እንዳይስት ፈጽመው ይራቁ
ባንቺው መብረቅነት ተመትተው ይውደቁ
      *  *  *  *  *  *
አበው ስለ ጽድቅሽ ጽድቅን ተከተሉ
ስለ ጽኑ ረኃብሽ ሳር ቅጠሉን በሉ
ስለ ውኃ ጥምሽ በጥም ተቃጠሉ
ስለ ስደትሽም ዓለምን ንቀው ዞሩ
ስለ ትህትናሽ ትሁት ሆነው ኖሩ
ስለ ልዩ ፍቅርሽ ሁሉን አፈቀሩ
ስለ ጥልቅ ሀዘንሽ ጥቁር ልብስ ለበሱ
ስለ በዛ እንባሽ ዘወትር አለቀሱ
ሰለ አዋቂነትሽ ጥበብን አፈቀሩ
ስለ ዝምታሽም በዝምታ ኖሩ
ስለ አስተውሎሽ በጥልቅ መረመሩ
ስለ ሙሉ ጸጋሽ በጸጋ ከበሩ………
እኔ ግን ባተሌው ይሄው እደክማለሁ
ዓለምን አፍቅሬ ክብርሽን እሻለሁ
ከሕይወት ርቄ በቃል እኖራለሁ
ለክብርሽ በድፍረት ልጽፍ እዳዳለሁ
      *  *  *  *  *  *
ጻድቃን ሰማዕታት ስምሽን ሲጠሩ
ጥዑም ዜማ ደርሰው ሁሌ ሲዘምሩ
ስለጣፈጣቸው ከወተት ከማሩ
አልበቃ ብሏቸው ምሥጋናና ዜማ
በስደት ሀዘንሽ ነፍሳቸው ቆዝማ
ፈልገዋልና ከከክብርሽ ሊወስዱ
እውነት ለመመስከር ፍርሃት አስወገዱ
በሰይፍ ታረዱ በእሳት ነደዱ………
እኔ ምስኪን ልጅሽ ደኃ ነኝ በመንፈስ
ከቶ ያልታደልኩኝ የእነርሱን ክብር ልወርስ
ሁሉን ልተውና ባንቺ ተስፋ ልጽና
በልጅ አይገፋም የእናት ልመና!
     *  *  *  *  *  *
ጻድቃን ሰማዕታት መላእክት በሙሉ
በአጸደ ሥጋና በአጸደ ነፍስ ያሉ
ስለ ልዩ ክብርሽ ይጠነቀቃሉ
ሊቃነ መላእክት ሲቆሙ ከፊትሽ
በጥንቃቄ ነው ስለ ልዩ ክብርሽ
የአንቺንማ ክብር ገብርኤል ይናገረው
ከዘካርያስ ጽድቅ ምን እንዳከበረው
ስለድምጽሽ ጣዕም ኤልሳቤት ትመስክር
የማህፀኗ ጽንስ ዘሏል ላንቺ ክብር
ያሬድ በማሕሌት ሕርያቆስ በቅዳሴ
ጊዮርጊስ በአርጋኖን ኤፍሬም በውዳሴ
ዳዊት በበገና ኢሳይያስ በትንቢት
ክብርሽን ይንገሩን የኖሩት በሕይወት
አበው ነቢያቱ ሐዋርያት  ይጠሩ
ሊቃውንትም ይምጡ ምሥጢር ያመሥጥሩ
በአንቺ የልደት ቀን ክብርሽን ይንገሩ……
እኔ ግን በድፍረት ከሰማሁት ልጻፍ
ለምልጃሽ ወድቄ ከመቅደስሽ ደጃፍ
     *  *  *  *  *  *
ሰማይና ምድር ልደትሽን ሲያከብሩ
ሊቃውንት ሲቀኙ መላእክት ሲዘምሩ
ክብርሽን ተማምነው በምልጃሽ ያደሩ
በምህረት ቃል ኪዳን ለክብር ሲጠሩ
እንደልጅነቴ ለእኔም እንዲደርሰኝ
እንባሽን አስታውሶ ልጅሽ እንዲምረኝ
ዝም ማለት ያልቻልኩት ለዚህ ነው ድፍረቴ
የአንቺ መወለድ ነው የጽድቅ መሠረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው ልደትሽ ልደቴ
       *  *  *  *  *  *
   (መላኩ አ.- ግንቦት 1/2006-አ.አ- https://www.facebook.com/melakualamrew?ref=hl

melakua.blogspot.com)

No comments: