Monday, May 19, 2014

እወዳችኋለሁ! ምን ታመጣላችሁ?


(መላኩ አላምረው)
* * * * *
የኢትዮጵያ ልጆች እናንተ ሁላችሁ
ባገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ያላችሁ
ከውስጤ፣ ከልቤ ውድድድ…ባደርጋችሁ
ከመወደድ ሌላ ምን ታመጣላችሁ!
 * * * * *
ሃይማኖቴን ተውት
ብሔሬንም ተውት
ቀለሜንም ተውት
እውቀቴምን ተውት ይህ የእኔ ጉዳይ ነው
ፍቅሬ ያለላችሁ “ሰውነቴ” ላይ ነው
እዩት እኔነቴን እንደናንተው ሰው ነኝ
ፍቅርን በመስጠት ፍቅርን የማገኝ
የሰውነት ክብሬን ብቻ ተመልከቱ
ወደ ፍቅር ግቡ ከእስራት ተፈቱ
እኔ ግን እመኑኝ ሰው ስለሆናችሁ
ሰው በመሆኔ ነው ከልብ ምወዳችሁ
ስላፈቀርኋችሁ ምን ታመጣላችሁ?
* * * * *
እውነት እውነት እውነት
በማይዋሽ አንደበት
ከእናንተ በስተቀር ለኔ ምን ሀብት አለኝ?
ከፍቅራችሁ በቀር ለኔ ምን ጸጋ አለኝ?
ሀገሬም ወገኔም ያው እናነተው ናችሁ
ፈጽሞ አንለያይ ስሙኝ እባካችሁ
በምድር እስከኖርን በሰውነት ክብር
ሰው ሰውን ለመውደድ ሌላ ሰበብ ይቅር
በሰውነት መስፈርት ከልብ እንፋቀር
እንደኔው ሰው ናችሁ! እወዳችኋለሁ!
ምን ታመጣላችሁ? አፈቅራችኋለሁ!
* * * * *
ከየትም ብሔር ኑ
በምንም ስም ተጠሩ
የትም ቦታ ኑሩ
ከቶ ቢኖራችሁ ምንም ዓይነት ቀለም
አትጠራጠሩ አንድ ነው የእኛ ደም
የሁሉም ሰው ደሙ ቀይ ብቻ እኮ ነው
የዘር መለያየት መንስኤው ምንድነው?
የአንድን እናት አባት ልጆች እስኪ እዩአቸው
ፍጹም ተመሳሳይ አንድ ነገር አላቸው?
አንዷ ጠይም ስትሆን ሌላኛው ይጠቁራል
አንዷ ረጅም ስትሆን ሌላው ደግሞ ያጥራል
በእምነትም ቢሆን በአመለካከታቸው
አንድ ሊሆኑ አይችሉም ልዩነት አላቸው
ግን ከአንድ ቤተሰብ ተፈጥረው ሲኖሩ
የት መጣ አንድነቱ ከየት መጣ ፍቅሩ?
አይመስላችሁም ወይ ዘር ስለማይቆጥሩ
በአንድ አገር ጥላ ሥር ምንኖር ተጠልለን
ተፈጥሮ ነውና- በብዙ መንገዶች እንለያያለን
ግን ምን ያግደናል? ከልብ ለመዋደድ ከልብ ለመፋቀር
በአንዲት አገር ጥላ- ንፍቅፍቅ እያሉ- ባንድ አብሮ ለመኖር
የራሳችሁ ጉዳይ! ካልወደዳችሁኝ- ያው ቀረሁባችሁ
እኔ ግን ከልቤ- እኔም ሰው ነኝና ሰው በመሆናችሁ
እወዳችኋለሁ! አፈቅራችኋለሁ! ምን ታመጣላችሁ?
        (Melaku A.- ግንቦት 11/2006)

No comments: