Friday, November 1, 2013

በአገራችን ለሙስና መስፋፋትና ለሥነ ምግባር ብልሹነት ተጠያቂው ማን ነው?

January 18, 2013 at 2:30am
በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ላይ አንድ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም፣ አሳዛኝም ዘገባ አነበብኩ። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የግል ት/ቤቶች ውስጥ በአንዱ (ምንአልባትም የእኛ ቋንቋዎች በማይነገሩበትና ልጆች እንግሊዝኛ በመናገራቸው ብቻ የእውቀት ጣሪያ ላይ የደረሱ በሚመስሉበት) የተፈፀመ አስነዋሪ ተግባር።
ሰባት ተማሪዎች (3 ወንድና 4 ሴት) የማጠናከሪያ ትምህርትና ጥናት አለን በማለት ያመሻሉ። ከዛም (ከጥበቃዎች ጋር በመስማማት ይመስላል) ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአንድ ክፍል ውስጥ በቦርሳቸው ደብቀው ያስገቡትን ሁለት ጠርሙስ ውስኪ እየጠጡ ጭፈራ ይጀምራሉ። ይጠጣሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይጮሀሉ… ድምፁ እየተሰማ ተው የሚል አልነበረም። እስከ ምሽቱ 7 ሰዓት አስረሽ ምችው ከጨፈሩ በኋላ ድምፃቸው ይጠፋል።
በማግስቱ ጠዋት ተማሪዎች ወደ ክፍል ሲገቡ የታየው ነገር አስደንጋጭ ነበር። ሴቶችም ወንዶችም እርቃናቸውን በወንበሩም በወለሉም ላይ ተረፍርፈዋል። ክፍሉ በትውኪያና ሽንት ተጥለቅልቋል። ሁለት የውስኪና ሦስት የአምቦ ውሃ ጠርሙሶች በየቦታው ወድቀዋል። የምግብ ፍርፋሪም በክፍሉ ይታያል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በላፕቶፓቸው ሲመለከቱት (ምንአልባት ያንኑ ሲለማመዱት) የነበረው አስፀያፊ የ“ኦንላይን” ልቅ የወሲብ ፊልም አልተዘጋም ነበር። አገር ሰላም ያሉት ቀበጦቹ ተማሪዎች ግን እንቅልፍ ላይ ነበሩ።
እኔን በጣም የገረመኝ ነገር በሌሊት ክፍል ውስጥ ሲጨፈር ድምፁ እየተሰማ ጥበቃዎች ተው አለማለታቸውና ወላጆችም ልጆቻችን የት ቀሩ ብለው አለመጠየቃቸው ነው። ለማንኛውም ይህ በአገራችን በተለይም በመዲናችን እየተፈጠረ ላለው አዲስ የወጣቶች መንፈስ እንደ ማሳያ እንጂ ሌላም እጅግ ብዙ አሳዛኝና ዘግናኝ ነገሮች አሉ። የአባቶች ውብ ባህል ወደ ልጆች እየተሻገረ አይደለም። የሥነ ምግባር መበላሸቱ ብቻ ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር አለማየቱ እየበዛ ነው። ቋንቋችንን መናገር አሳፋሪ ነገር እየሆነ መጥቷል። ገና በሃይስኩል ደረጃ የሚጀመረው ከአገር ወግና ባህል ማፈንገጥ ነው አድጐ ነገ ሀገር የሚያጠፋው። በሥነ-ምግባር ያለታነፀ ትውልድ ለአገር ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም። ጥያቄው ግን ሥነ ምግባርን ማን ያስተምር የሚለው ነው። ወላጆች? ጓደኞች? ትምህርት ቤቶች? ወይስ የምዕራባውያን ፊልሞች? የእያንዳንዳቸው ድርሻስ በምን መልኩ መሆን አለበት?
ሁሉም ድርሻ አላቸው (መጥፎም ጥሩም ለማድረግ)። የአንዱ ግን ከሌላው ይለያል። ትልቁን ድርሻ መውሰድ ያለበት እና ለዚህም ጠንክሮ መስራት ያለበት ግን ትምህርት ሚኒስቴር ነው።  የሥነ ምግባር ትምህርቶች ውጤታማነት መታየት አለበት። ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ የትምህርት ስልት ማስተማር አለባቸው። የተደበላለቀ ዓይነት ትውልድ የሚፈጠረው ወጥ ባልሆነ ሥርዓተ ትምህርት ነው። ዛሬ አገራችንን ደም እያስለቀሰና ታላቅ ዋጋ እያስከፈለ ያለው ሙስና መነሻው ትምህርት ቤት ነው። የሥነ ምግባር አስተምህሮታችን ውጤት ነው ሙስና። ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በአንድ ጀምበር አይፈጠርም። ትምህርት ቤቶች ላይ ብዙ መድከምን ይጠይቃል። ልጆች ሥነ ምግባርን መማር አለባቸው።
እንዲህ የሚባል ተረት አለ። “በእንግሊዝ አገር አንድ ገበሬ ነበር አሉ። ከእርሻ ሥራው ጐን ለጐን ድመቶችን በማሰልጠን የገቢ ማስገኛ ሥራ ይሰራባቸው ነበር። ገበሬው በልደት፣ በሠርግ፣ በምርቃትና በመሳሰሉት ልዩ ልዩ የደስታ ቀናት /በዓላት ላይ ስልጡን ድመቶቹን በመደዳ ያሰልፋቸውና በሁለቱ የኋላ እግሮቻቸው ቆመው በሁለቱ የፊት እግሮቻቸው ደግሞ የተለኮሰ ሻማ ይዘው እንዲታዩ በማድረግ ነበር ገቢ የሚያገኝባቸው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ታዲያ ገበሬው በአንድ ልዑል ሠርግ ተገኝቶ የተለመደውን ትርዒት እንዲያሳይ ይጋበዛል። ከ20 በላይ የሆኑት ድመቶችንም ግራና ቀኝ ተሰልፈው ሻማ እንዲያበሩና ሙሽሮቹ በመካከል እየተጀነኑ እንዲያልፉ በማድረግ ልዩና ዘና የሚያደርገውን ትዕይንት በማሳየት ላይ እያለ አንድ አሳፋሪ ክስተት ተከሰተ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ድመቶቹ በሚያሳዩት ልዩና ቀልብ የሚስብ ትዕይንት ሰው ሁሉ ማጨብጨቡን ትቶ ፈዞ በመመልከት ላይ ነው። የሙሽሮቹ ደስታ እጥፍ ድርብ እየሆነ ነው። ሁሉም ቀልቡ በትርዒቱ ተስቦ በአግራሞትና በአድናቆት ሲከታተል ከየት እንደመጣ ያልታወቀ አንድ የደነበረ ወደል አይጥ በድንገት ዘው ብሎ አዳራሹ ውስጥ ይገባል። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ሆነና የገበሬው ድመቶች ያን ወደል አይጥ ባዩ ጊዜ የተሰጣቸውን በልዑል ሠርግ ፊት እየተደረገ ያለ እጅግ ታላቅ ኃላፊነት ከምንም ሳይቆጥሩ ሻማቸውን እያሽቀነጠሩ በመጣል አይጥ ማባረሩን ተያያዙት። አዳራሹም በቅፅበት በትርምስና በሁከት ተሞላ። ገበሬው ታላቅ ሐፍረት ተሰማው። አንድ ነገር ግን ትዝ አለው። ድመቶቹን ስለ ሻማ አያያዝና አሰላለፍ ለማስተማር ያን ያህል ጊዜ ሲደክም ቢያንስ እንደዚህ ባለ የተከበረ ትርዒት ወቅት አይጥን አይቶ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል አላስተማራቸውም ነበር።” (ምንጭ፤ ምጥን ቅመም ዲ/ን ምትኩ)
ከታሰበበትና ከልብ ከተደከመበት ሰውን አይደለም እንስሳትን አሰልጥኖ ልዩ ተአምር መፍጠር ይቻላል። የሰው ልጅ በባህርይው ባስተማሩትና በደከመበት ልክ የማወቅ ፀጋ አለው። መጥፎ ነገር ላይ ካተኮረ መጥፎን ይማራል። ጥሩን ካዘወተረም ጥሩውን ነገር የህይወቱ አካል ያደርጋል። ያልተማረውን መልካም ነገር ከየትም ሊያመጣው አይችልም። ትውልዳችንን ምን አልባት ፊደል እያስቆጠርነውና ሳይንስን እያስተማርነው ይሆናል። ለዲፕሎማ፣ ለዲግሪ፣ ለዶክትሬት… የሚያበቃውን እውቀትና ክህሎትም ሰጥተነው ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ግን ሥነምግባር ከጐደለው ከንቱ ነው። በትምህርት ውጤት አራት ነጥብ (4.00) ሊኖረን ይችላል። በክህሎትም ምስጉኖች ልንሆንና ሰው ሁሉ የእኛን ጥበብ የሚመኘው ሊሆን ይችላል። ሥነምግባር ከሌለን ግን ይህ ዘላቂ ልማት ላይ ሊተገበር አይችልም።
ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ማስተማር አንድ ነገር ነው። በሥራ ሂደት የሚመጡ መሰናክሎችን ሁሉ አልፎ የሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ እንዴት እንደሚቻል ማሳወቅ ደግሞ ሌላ። ሥራን በልዩ ፍጥነትና ክህሎት እንድንሰራ ብቻ ሳይሆን ለማን እንደምንሰራና ለምን እንደምንሰራ ሁሉ ማወቅ አለብን። ሥራችን እየተደነቀ ባለበትና ልዩ ተስፋ በተጣለብን ወቅት ወፍራም ብር ሲመጣ ቃላችንን የምናጥፈውና ህዝብን ሳይሆን ግለሰብንበ የምናገለግለው እኮ እንዴት መስራት እንዳለብን እንጂ ወፍራም ብርን እንዴት ማለፍ እንዳለብን ስላልተማርን ነው። እነዚያ ድምቶች እኮ ገበሬውን ያዋረዱት አይጥ የማሳደድ ተፈጥሮ ስላላቸው ብቻ አይደለም። አይጥ መቼና የት ማባረር እንዳለባቸው እና መቼ እንደሌለባቸው አልተማሩም። በትርዒት ወቅት አይደለም አንድ አይጥ ሺህ አይጥ ቢመጣ አቋርጦ መሄድ እንደማይቻልና ይህንን የማለፍ ጥበቡና ሥርዓቱ (ምግባሩ) እንዴት እንደሆነ አልተማሩም። ለዚህም ነው ገበሬውን ያዋረዱትና ሠርጉን የረበሹት።
እኛም እኮ ዛሬ ገንዘብ የመውደድ ባህሪይ ስላለን ብቻ አይደለም ሙስና የምንበላው። ገንዘብን ከወደድን እንዴት ሠርተን ማግኘት እንደምንችል፣ ካሰብን እና ከጣርን ማግኘት እንደምንችል እንጂ የህዝብን ተስፋ ገድለን ኪሳችንን ማሳበጥ ፍፁም ቆሻሻና ወራዳ ሥራ እንደሆነ አላወቅንም። እንዲሁ ሰማነው እንጂ አልተዋሃድንም። በወሬ እንጂ በተግባር ያሳየን የለም። የሚያስተምሩንም እራሳቸው ሲዘርፉ እያየን ይሆናል። በልጅ አዕምሮአችን ያልተማርነውን የት እናምጣው። ሙስና ወንጀል ነው ተባልን እንጂ ሙሰኛው ሲወነጀልና ሲቀጣ አላየንም። ሙሰኛው ሲቀጣ በተግባር አሳይቶን የሚያውቅ መምህርም የለም። ታዲያ ሙስና እንደሚያስቀጣ እንዴት እንመን? በተግባር የማያሳየንን ሥነ ምግባር የሚያስተምረንን መምህር እንዴት እኛ በተግባር እናሳየው? የምንማረው ሁሉ እንደሚሆን እንጂ እንዴት እንደሚሆን ካላየን እንዴት እንፈፅም? ይህ ሁሉ በትምህርት ሚኒስቴር ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል።




No comments: