(መላኩ አላምረው)
...
ጎበዝ !... የፍቅርን ሕይወት በትክክል መኖር ባንችል እንኳን ትርጉሙን አዛብተን በመረዳት ለትውልዱም የተሳሳተ ግንዛቤ ለመስጠት ባንደክም አይሻልም ? "ፍቅር" እንኳን
ሳይተያዩ ተያይቶና ተጠናንቶም በሥጋ ስለተዋደዱ ብቻ ዘው ብለው የሚገቡበት ሕይወት አይደለም። የሰው ልጅን ሦስት ባሕርያት መግባባትና መዋሐድ ከሚጥይቁ ነገሮች አንዱና ዋናው ፆታዊ ፍቅር ነው። የስሜት (በአጠቃላይ የስሜት ህዋሳት) ፣ የአዕምሮ እና የመንፈስ። በእነዚህ ነገሮች ለመግባባት ደግሞ ምን ያህል
ጊዜና ትኩረት ሊጠይቁ እንደሚችሉ ለመገመት አያዳግትም፡፡
……………….
የሰሞኑን የebs "የፍቅር ምርጫዬ" ፕሮግራም አስተያየት ተከታትላችሁ ከሆነ... ቴሌቪዥን ጣቢያው ምን መልእክት ማስተላለፍ እንደፈለገ ግልጽ ነው። "ምንም
በሉ ምን እንቀጥላለን" አይነት ነው። ምክንያቱም የመጨረሻው አስተያየት "በርቱ" የሚል ነውና። ይህንን በማለት ፕሮግራሙን መቀጠል መብታቸው ነው። እኔም ትዝብቴን እየጻፍሑ መቀጠል መብቴ ነው።
({J> በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጽፌው ከነበረው የግል አስተያየት ጋር በተያያዘ ለምን ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› ፕሮግራምን
እንደምቃወም ከebs ቴሌቪዥን ጋር ረዘም ያለና የተላዘበ ቃለ መጠይቅ አድርጌ ነበር። ነገር ግን የተቆራረጡ ደጋፊ አይነት ሃሳቦች ተመርጠው ነው የቀረቡት። ወይ ሚዲያዎቻችን... ግርምምም ይሉኛል:J))
ቃለ መጠይቁ ላይ የቆርጦ መቀጠል ሥራው (Editing) በተቃውሞ
ጎራ የተሰለፍን ተጠያቂዎችን መልእክት ጭብጡን እንዳሳጣው ከእኔ በላይ ምሥክር የለም። ለአንድ ሀሳብ መነሻ ሳይኖረው መደምደሚያ የለውም፡፡
አንድ አካል የአንተን መነሻ አመክንዮ ቆርጦ መደምደሚያህን ወይም መድረሻ ሃሳብህን ትቶ መነሻ ምሳሌዎችህን ካቀረበው ምን ያህል መልእክትህ እንደሚዛባ
ደርሶብህ እየው፡J)
………
›) ለማንኛውም ለማኅበራዊ ድረ-ገጽ አንባብያን በፕሮግራሙ ዙሪያ በአመክንዮ የተመሠረተ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ለማድረግ ግልጽ ውይይት ማድረግ ግድ ነውና በዚያው በቃለ መጠይቁ አንስቻቸው
የ‹ኤዲተሩን› መቀስ ማለፍ ስላልቻሉ ያልተሰተናገዱ እና እንዲሁ ብንወያይባቸው ይጠቅማሉ የምላቸውን አንዳንድ ተጨማሪ ነጥቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁ። (ቴሌቪዥኑ ቢቆራርጠውም ማንም የማይቆርጥብኝ በእጄ ያለ መድረክ ላይ ነኝና)።
1ኛ. ስለ ፕሮግራሙ ርዕስ እና ይዘት...
ለእነርሱም በግልጽ እንደነገርኋቸው... በእኔ እምነት "ፕሮግራሙ የማይመጥነውና የማይስማማው" ርዕስ ነው የያዘው። "የፍቅር ምርጫዬ" ብሎ ሳይተያዩ (በደንብ ሳይተዋወቁ) መመራረጥ የለም። ቢኖርም ስህተት ነው። እርግጥ ነው በሥጋ ዓይን የማያዩ ሰዎችም የፍቅር አጋራቸውን ይመርጣሉ። ነገር ግን በሕሊናቸው ዓይተውና በሚያዩ ሰዎችም አሳይተው እንጅ እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። "ባዶ እጄን ከምሄድ፣ ብቻዬን ከምኖር..." ብለውም አይደለም። የሀገራችን የጋብቻ ባህል ከቦታ ቦታና የሚለያይበት ነገር ቢኖረውም… "ልጆች ሳይተዋወቁ ነው የሚጋቡት" ከምንላቸው ጋብቻዎች ጀርባ ትልቅ የሆነ የወላጅና የማህበረሰብ ትውውቅና ለልጅ አሳቢነት የሚታይበት በጥንቃቄ የተሞላ አመራረጥ ነው ያለው። ዝም ብለን በኋላ ቀርነት የምንነቅፈውና ልናርመው የምንሮጥ ባህል የለንም። ማረም ያለብን ይልቅ ከየትም ሀገር ያየነውን ኮርጀንና ከሀገራችን ባህልና ወግ ጋር መሄድ አለመሄዱን ሳናስተውል ለሚዲያ የምናበቃውን ነገር ነው። እናም ፕሮግራሙ የግድ እቀጥላለሁ ካለ ወይ ስሙን ወይ ይዘቱን ይቀይር። እኔ በግል ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› የሚል ስም
የያዘ ፕሮግራም አይኑር አልልም፡፡ አሁን በሚቀርብበት መልኩ ግን ላየው አልፈልግም፡፡
2ኛ. የሕዝባችን አዲስ ነገርን የመቀበል ጉዳይ...
ስለ ፕሮግራሙ ያለው አንዱ የአዘጋጆች እይታ ይህ ነው። "ሕዝቡ አዲስ ነገርን የመቀበል ልምዱ ደካማ በመሆኑ ነው የሚቃወመን" የሚል። ለዚህም በትላንቱ የአስተያየት ፕሮግራም "ለቴክኖሎጅ" የተጠቀሰውን ሀገርኛ ምሳሌ... ምንም አዲስ ላልሆነው ለዚህ የማስተዋወቅ (በዘመንኛ አጠራር ለማጣበስ) ፕሮግራም በመጥቀስ "ሕዝቡ አዲስ ነገርን መቃወሙ አዲስ ነገር አይደለም" የሚል ድምዳሜ እንዲያዝ ለማድረግ ተሞክሯል። ያው ምንም ይባል ፕሮግራሙ ይቀጥላል አይነት መልእክት ለማስተላለፍ ነው። እኔ (ለቃለ መጠይቅ አድራጊውም በግልጽ የነገርሁት) ይህ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ለሀገራችን አዲስ አይደለም። አዲስ ነገር አመጣን ብለን "ሕዝቡ አዲስ ነገርን የመቃወም ልማድ ስላለው ነው የሚቃወመን" የሚል ራስን መደለያ ሃሳብ መያዝም መሳሳት ነው። ሕዝቡ ሲቃወማቸውና የሰይጣን ሥራዎች ናቸው ሲላቸው የነበሩ (ለምሳሌ የሚኒልክ ዘመን ወፍጮ፣ የቧንቧ ውሃ፣ ስልክ፣ መኪና...) ለሀገሩ እንግዳ ለሕዝቡ ባዳ የነበሩ አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች ናቸው። እነርሱንም ቢሆን ጥቅማቸው ሲገባው ተላመዳቸው... እንዲያውም አብዝቶ ፈለጋቸው እንጅ ተቃውሟቸው አልቀረም።
እርግጥ
የእኛ ባህልና ሃይማኖት አዳዲስ ነገሮችን እንዳንቀበል ተጽእኖ ያደርጉ እንደነበረ ታሪክ ምሥክር ነው፡፡ አሁንም ድረስ
የሚስተዋል ሀቅ ነው፡፡ ይህ "የፍቅር ምርጫዬ" ብሎ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ግን ለሀገራችን አዲስ አይደለም። (አዲስ ሆኖ ነገር ግን ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ከሆነ ማንም ሊያስቆመው
አይችልም)፡፡
ግን አይደለም፡፡ ወላጅ ለልጅ አጭቶ በሚያጋባበት ማህበረሰብ ዘንድም እንኳን አባቶቻችን "ማስተዋወቅ" የሚለውን በመረዳት በኩል የተሻሉ ነበሩ። ልጃቻቸው ከማግባተቸው በፊት (በድብቅም ቢሆን) እንዲተያዩ ያደርጋሉ። ልጆች ባይተዋወቁም ወላጆች በደንብ ያውቋቸዋል። ወላጅ ለልጁ የሚበጀውን ለመምረጥ ብዙ ይደክማል።
ይህ ፕሮግራም ግን "ባለመተያየት ነገር ግን አዘጋጆች በሚያወጧቸው ውስን የጥያቄ መልሶች ለፍቅር አጋር መምረጥ" የሚልና "ሰውን ከሸቀጥም በታች ማድረግ" ነው። ሸቀጥን እንኳን ስንመርጥ በደንብ አይተን ወደን እንጅ በሰማነው ብቻ አይደለምና። ይህ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራ
ካለበት በጋብቻ አማካሪዎች በኩል ቢሠራ፡፡ እንጅ በሚዲያ ያውም በቴሌቪዥን ለመቅረብ ሀገሩ ኢትዮጵያ አይደለችም፡፡
የሚቀርብበትን ሀገር ይፈልግ፡፡ አይ እምቢ ካለ ግን መብቱ ነው፡፡ ነጻነት እንደዚህም ነውና፡፡
3ኛ.
ስለ ባህል መሻሻል/ማደግ/መጥፋት…
አንደኛው
የፕሮግራሙ ደጋፊዎች እይታ ይህ ነው፡፡ ባህላችን ለዚህ ፕሮግራም ባይመችም ባህል በራሱ የሚሻሻል/የሚያድግ ነገር በመሆኑ ቆመን
ለመቅረት አንከራከር የሚል፡፡ ይህኔ ነው ማፈር ! ገና ለገና ባህል ሊያድግ/ሊለወጥ/ሊጠፋ/ሊሸጋገር የሚችል ነገር ነው ተብሎ
እንዲህ ይባላል ? ዛሬ ላይ መነጋገር ያለብን እኮ ስለ ዛሬ/አሁን ነው፡፡ ነገን ማንም አያውቃትምና፡፡ ይህ ፕሮግራም ከአሁኑ
ባህላችን አፈንግጧል ካልን በቃ ፍርጃው አሁን ነው፡፡ አይ ችግር የለበትም ካልንም ከአሁኑ የሀገራችን ነባራዊ የባህልና ወግ
ሁኔታ አንጻር አይተንና አሳይተን ነው፡፡ ይህ የአሁኑ ባህላችን ነገ መቀየሩ ስለማይቀር አስቀድመን የፈለግነውን ሁሉ ለማድረግ
አይከለክለንም ካልን በእውነት ተሳስተናል፡፡ ደግሞም ቆመው መቅረት (አለመለወጥ አለመሻሻል) ያለባቸው ጠቃሚ ባህሎች ካሉ በሙሉ
ህልውናቸው ቆመው መኖር አለባቸው፡፡ የእኛን ጠቃሚ ባህል እየጣልን የሌላን ስናሳድድ ነው ራሳችንን ሳንሆን የምናልፈው፡፡
ከዚሁ
ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ሁኔታ ከሀገራችን የከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተቀይሯል፤ እናም ለ‹‹ፍቅር ምርጫዬ›› ዓይነት
ፕሮግራሞች ምቹ ሁኔታዎች አሉ እያልን ከሆነ እንግዲህ የባህሉ ባለቤት ሕዝቡ ይፍረድ፡፡
እኔ
በግል ከፕሮግራሙም ሆነ ከአዘጋጆቹ ጠብ የለኝም/አንተዋወቅምም፡፡ የሕዝቡ አካል እንደመሆኔ ግን ሕዝቡ የሚቀበለውንና
የማይቀበለውን (አማራጭ አጥቶ ዝም ስላለ ተቀበለ ማለት አይደለም) አውቃለሁና ተቃውሞውን በአቅሜ አሰማለሁ፡፡ ይህንን ለማወቅ
የተለዬ ጥናት አይጠይቅም፡፡ ‹‹ደጋፊም አለን›› ካላችሁ አዎ ይኖራል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፍ ሰው ከማየት በላይ ደጋፊ
እንዳለ ማረጋገጫ አይኖርምና የለም አልልም፡፡ ግን ጥቂት ደጋፊ ያለው ነገር ሁሉ ለሕዝቡ የሚቀርብበት ምክንያት አይገባኝም፡፡
ማየት ያለብን አብዛኛውን ሕዝብና ሕጻናትን ወይስ እነዚህን ‹‹እንደ አማራጭ እየወሰድነው ነው›› የሚሉትን ?
4ኛ.
ግልጽነት/የእኩልነት መብት…
ፕሮግራሙን
የሴቶችን መብት የማስጠበቅና ግልጽ የመነጋገር አማራጭ አድርጎ ማይት ለእኔ አይገባኝም፡፡ ግልጽ መነጋገርን በዚህ መልኩ ከሆነ
የምንረዳው ማለቴ ለሕጻናት መጥፎ ትምህርት የሚሰጡ የአልጋ ላይ ንግግሮችን ወደ አደባባይ በማውጣት ከሆነ በእውነት
ተሳስተናል፡፡ መናናቅንና መነቃቀፍን በግልጽ ለሚዲያ ማቅረቡን ግልጽነት ካልነው ግልጽነት በራሱ ግልጽ አልሆነልንም፡፡
የሴቶች
መብትስ የሚጠበቀው በዚህ መልኩ ሳይተያዩ በመምረጥና በመመረጥ ነው እንዴ ? የሀገራችን ባህል ለሴቶች ያሳጣቸው መብት ፍቅርን
በግልጽ የመናገር (ለምሳሌ የወደዱትን መርጦ የመጠየቅ) ከሆነ ይህ ፕሮግራም በምን መልኩ ነው መብታቸውን ያስከበረላቸው ?
እውን የወደዱትን ነው እየመረጡና እየጠየቁ ያሉት ? ብቻ ግራ የገባው መረዳት የያዝን ይመስለኛል፡፡
……
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተላለፉ የሚዲያ ፕሮግራሞች ሀገራችን የሃይማኖትና የባህል ሀገር መሆኗን መርሳት የለባቸውም። ባህልንና ሃይማኖትን አክብረው... ሲሆን ማኅበረሰቡን ወደተሻለ የአስተሳሰብ ከፍታ ለማምጣት ቢጥሩ ፣ ባይቻል ደግሞ ያለውን መልካም እሴት እንዲጠብቅ ቢያደርጉ ጥሩ ነው። በተለይ ግን ያለውን ጥሩ ነገር እያጠፉ የባዕድን ልቅነትና ሥርዓት አልባነት ለትውልዱ የሚያለማምዱ "የምንአለበት" ፕሮግሞች ከሚኖሩ ይልቅ ባይኖሩ እመርጣለሁ። አዘጋጆቻቸውም ሕዝቡ ቀድሟቸው ወደተሻለው ከፍታ ሄዷልና ለማውረድ ከሚጥሩ ይልቅ ከሕዝቡ ቢማሩ ይጠቀማሉ።
.......
No comments:
Post a Comment