Monday, April 27, 2015

እንግድነቱን ያልተረዳ ሕዝብና ጉዞው….


(መላኩ አላምረው)
...
የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሰው በዚህች ዓለም ላይ ሲኖር በፍጹም የተረጋጋ ሰላም/ሕይወት ውስጥ ይኖር ዘንድ እንዳልተፈጠረ ነው፡፡ ምን አልባትም ይህች ዓለም ለሰዎች ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ መኖሪያ ስላይደለች ይሆናል፡፡ አዎ! ሰው በእንግድነት በሚኖርበት ዓለም ሁሉም ይሟላልኝ የማለት መብት የለውም፡፡ እስኪ አስቡት…. እንግዳ ሆናችሁ ከሄዳችሁበት ቤት የፈላግችሁትን ሁሉ የማዘዝ መብት/ሞራል አላችሁ? አይመስለኝም:: የሰጧችሁን በልታችሁ ባገኛችሁት ተኝታችሁ ትመለሳላችሁ እንጂ እንደ ቤታችሁ “ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ”… የፈለግሁት ይምጣልኝ ያልፈለግሁት ይሂድልኝ አትሉም፡፡
ሰፋ አድርገን ብናየው በዚህች ዓለም ያለው ኑሯችንም ይሄው ነው፡፡ ማን የፈለገውን ሁሉ አሟላ? (ፍላጎት ገደብ ባይኖረውም ቅሉ)፡፡ ነጻነታችንን በሙሉ የምጠቀምባት ምድር/ሀገር አለች? ፍጹም የሆነ ሰላም የሰፈነባት፣ ክፉ ነገር የሌለባት ብቻ ሳትሆን የማይወራባት፣ ምንም መከልከል የሌለባት፣ ሁሉም እኩል ተናግሮ፣ እኩል ሠርቶ፣ እኩል አግኝቶ… የሚኖርባት ሀገር አለች? የትም!!!! ሁሉም እንግዳ ስለሆነ ተሸማቆ፣ ተሳቆ፣ ተጨንቆ ነው የሚኖረው፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ፍርሃት አለበት፤ ሁሉም ችግር አለበት፤ ሁሉም ህመም አለበት፤ ሁሉም ክልከላ አለበት፤ ሁሉም ስለነገ እርግጠኛ አይደለም፤ …. እንግዳ ነዋ፡፡ የሚኖረው በራሱ ሀገር አይደለማ፡፡
እስኪ አሁን በዚህ ሰዓት በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን አስቡት፡፡ ስደት፣ ጦርነት፣ ረኃብ፣ ሱናሜ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ አመጽ፣ ሽብር፣ ግጭት፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ሙስና/ስርቆት፣ … የማያስጨንቃት ሀገር አለች? መጠኑ ቢለያይም በዚህ የማይሳቀቁ ሕዝቦች አሉ? ዛሬ ባይሳቀቁ ነገ ይጨነቃሉ፡፡ ዛሬ የሚስቁ ነገ ያለቅሳሉ፡፡ ዛሬ በሰላም የሚኖሩ ነገ ይረበሻሉ፡፡ ዛሬ የሚገሉ ነገ ሲሞቱ ይታያሉ፡፡ ዓለም እና ‘ገዥዋ’ እየተመካከሩ የፈለጉትን ሁሉ ያፈራርቃሉ፡፡ በቃ ሁሉም የእንግድነት ዓለሙ ላይ ስለሚኖር የማይሸከመው ሸክም የለም፡፡ ሁሉም ሲደርስበት ይቀበላል፡፡ እምቢ ቢልም ከመፍጨርጨር ያለፈ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ ምን አልባት ከአንዱ ችግር ወደ ሌላው ስቃይ ይሄዳል እንጂ ዓለምን ከችግር ሊያጸዳት አይችም፡፡ የእርሱ አይደለችማ፡፡ በሰው ዓለም ላይ መወሰን ብሎ ነገር የለም፡፡
ለዓለም ሰላምን እናመጣለን የሚሉትን ሀገራትም አየናቸው፡፡ የባሰ ጦርነትና ሰቆቃ እንጂ መፍትሄ ሲያመጡ አልታዩም፡፡ በአሜሪካ የሚመሩት ምዕራባውያኑ አምባገነኖችን አስወገድንላቸው ያሏቸው ሀገራት ዛሬ የአሸባሪ (የሰወ-በላ) ድርጅቶች መፈልፈያና መፈንጫ ሆነው ችግሩንና ሰቆቃውን እያባዙት ይገኛሉ፡፡ ኢራቅንና ሊቢያን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ ዓለም ባልገባው/በማያውቀው ጉዳይ ነው ገብቶ የሚዳክረው፡፡ የሰው ልጅ ማንነቱን/ምንነቱን እስከሚረዳና ወደ ሕሌናው እስኪመለስም ሁሉም ችግሮች እየተባዙ ይቀጥላሉ፡፡ በሰዎች ስሌት የሚመጣ መፍትሄ የለም፡፡ የራሳቸው ባልሆነ ዓለም ላይ ለምን እንደመጡ እንኳን በውል ሳይረዱ ማን የመፍትሄ አካል አደረጋቸው? ስህተቱ በእንግድነት ባረፉበት ዓለም ላይ የመቆጣጠር ምኞትንና ሙከራን ያውም በጉልበት ማምጣቱ ላይ ነው፡፡ በቃ እንደ እንግድነታችን ዓለም የምትሰጠንን ተቀብለን አመስግነን መሄድ እንጂ…. ሌላ ምኞት ስናመጣ ሌላ ጣጣ እያመጣን ነው፡፡
እንግድነቱን ያልተረዳ የዓለም ሕዝብ ዓለምን የሰቆቃ መናኸሪያ እያደረጋት ነው፤ እንዳደረጋትም ይቀጥላል፡፡ እንግዳ በሰው ቤት ላዝዝ ሲል የሚፈጠረው ጠብ ብቻ ነው፡፡ የሰውን ቤት ለእኔ ይገባኛል የሚልም ሰው ኑሮው ሰላም-አልባ ይሆናል፡፡ ባለቤቱን አስወግዶ/ገድሎ ቢኖርበት እንኳን እርሱ ያልሰራውን ቤት መውጫና መግቢያ፣ የቤተሰቡን ባሕርይ፣ የጎረቤቱን ጸባይ… ጠንቅቆ ሊያውቅ አይችልም፡፡ ራሱ አልሰራውምና ፍጹም ነጻነትን አይሰጠውም፡፡ ሁሌም በመጨነቅና በመሳቀቅ ውስጥ ይኖራል፡፡ እንግዶች ሚያምርባቸው ባለቤቱ እንደወደደና እንደፈቀደ ብቻ ተስተናግደው ሲሄዱ ነው፡፡
የሰው ልጅ ለምን ወደ ዓለም መጣ? ሊገዳደል? አንዱ አንዱን ሊገዛ? ዓለምን ሊወርስ?.... ሁሉም የሰው ልጆች ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ እስከሚኖረራቸውና በተግባርም እስከሚተረጉሟቸው ድረስ ዓለም በእብደቷ ትቀጥላለች፡፡ የሰው ልጆችም ለመጡበት ዓላማ ሳይኖሩ እንዲሁ እንደባዘኑ፣ እንደተሰደዱ፣ እንደተቀዋወሙ፣ እንደተሰዳደቡ፣ እንድተገዳደሉ ያልፋሉ፡፡
ስደት መፍትሄ የሚሆነው ይመስል ሰው ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ይሄዳል፡፡ ግን በዚያም የተሻለ ነገር አያገኝም፡፡ ምን አልባት ችግሮቹ መልካቸውን ቀይረው ይጠብቁታል፡፡ ተረቦ የተሰደደው እንጀራ ያገኝና ነጻነቱን ምን አልባትም ሕይወቱን ያጣል፡፡ ከምግብ ሲጠግብ ከፍቅር ይራባል፡፡ ፖለቲካ አስመርሮት የሄደው ከጠላቸው/ከጠሉት ፖለቲከኞች በመራቁ ሰላም ያገኘሁ ሲመስለው ሌላ የመረረ ዘረኝነት ይጠብቀዋል፡፡ ከዚህ በአመለካከቱ ከጠሉት/ከተጸየፋቸው ሲርቅ በቆዳ ቀለሙ የሚጠሉት ይጠብቁታል፡፡ በቃ ይሄው ነው የዓለም እውነት፡፡
ሁሉም ዓለም ላይ ያሉት መኖሪያዎች የእንግድነት ቤት ስለሆኑ አንዱ ሲሞላ ሌላው ይጎድላቸዋል፡፡ እናም ምንም ይሁን ምን ባላወቅነው እና ባልመረጥነው መንገድ ተፈጥረን ወደዚህች ዓለም በመጣንባት ቀዬ በዚህችው መኖር ሳይሻል አይቀርም፡፡

·         ሚያዝያ 19/2007 ዓ.ም - አዲስ አበባ

No comments: