Friday, August 12, 2016

ለሕዝቡ ‹‹እናውቅልሃለን›› ካልን በቀልን ሳይሆን ይቅርታን እናሳየው!

(መላኩ አላምረው)
-----//-----
በየቀኑ... በትጋት... በተደጋጋሚ... ‹‹የእገሌ ብሔር በእነ እገሌ ንበረቱ እየወደመ ነው ፣ እየተገደለም ነው... ወዘተረፈ›› እያልን የዘር-ተኮር ብጥብጥ ቀስቃሾች የሆን ‹‹አዋቂ ነን - ጸሐፊ ነን›› ባዮች ግን ትንሽ ማስተዋል የሚባል ነገር አልፈጠረብንም ? ደግሞ እኮ የምንለጥፈው ነገር እራሱ ምንም ያልተጨበጠና እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡ አንዴ ሕዝቡ ጨዋ ነው አንዴ ገዳይ ነው... አንዴ ለሕዝቡ ስንሠራ ስለኖርን ሕዝቡ ይወደናል ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘር ለይቶ እያጠቃን ነው... ዝብርቅርቅ ያለ መልእክት፡፡
ዓላማችንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በዘር እየተጠቃ ነው ለምንለው ወገን አስበን ነው እንዳልል... በተዛባና ባልተረጋገጠ መረጃ እያወናበድንና ተረጋግተው የሚኖሩትን የበለጠ እየረበሽን ‹‹ለሕዝብ ማሰብ›› ብሎ ነገር አይገባኝም፡፡ በተለይም ይህ በሆነ ባልሆነው የምናራግበው ዘር-ተኮር መጠቃቃት ሌላ በቀልና ሌላ ጥቃት እንደሚያስከትልም የገባን አይመስለኝም፡፡
ደግነቱ ሕዝቡ ከእኛ የተሻለ ያስባል፡፡ በስሜት የበደለ ካለ ይክሳል፡፡ በስህተት የተበደለ ካለም ይቅር ይላል.. ይታረቃል፡፡ ሕዝቡ በክስተቶች (ራሱ ሳይሆን ሌሎች በራሳቸው ዓላማ በሚፈጥሩበት ችግር) ቢገዳደልም እንኳን በደም ካሳ ታርቆ የመኖር ባህሉም የአዕምሮ ልዕልናውም አለው፡፡ አሁን ‹‹በዘር ተጠቃህ›› የምንለው ሕዝብ በእርግጠኝነት ነገ (በስሜትም ሆነ በስህተት ጉዳት ያደረሰበት ካለም) ይቅርታ አድርጎለት አብሮ ይኖራል፡፡ ሕዝቡ የመኖር ምሥጢር ማለት ‹‹ይቅርታ ማድረግ - የበደለ ክሶ የተደበደ ተክሶ›› መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ አላዋቂዎች እናውቅልሃለን በማለት፣ ከወንድምና እህቶቹ ጋር ልናገዳድለው ብዙ ብንደክምም ይህንን እኩይ ዘር-ተኮር ጠብ አጫሪነት የመስሚያ ጆሮ የለውም፡፡
እኛ በአላዋቂነታችን መጠን ብዙ እንለፈልፋለን፡፡ ሕዝቡ ግን ‹‹አብሮ በመኖር ግጭት፣ በግጭትም እስከመገዳደል የሚደርስ ችግር ሊመጣ ቢችልም... ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በይቅርታ አብሮ መኖር›› እንደነበረ፣ እንዳለና እንደሚቀጥል ያውቃል፡፡ ይህንን አላውቅ ብለን ለመኖር የተቸገርነው እኛ ‹‹ተማርሁና አወቅሁ›› ያልን ዘረኞች ነን፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር የበቀል ጦርነት የምናውጀው እኛው ነን፡፡ ግራ በተጋባ አዕምሯችን ትልቅ አብሮ የመኖር እሴትና የይቅርታ ባህል ያለውን ሕዝብ ሌላ አዲስ እኩይ ትምህርት ልንሰብከው የሚዳዳን እኛው ነን፡፡ አንዳንዴማ እንፈር እንጅ፡፡
ለሕዝቡ በጎውን እንጅ ክፉውን እንድናወርሰው ከሆነ ድካማችን ወላጆቻችንን ‹‹የወላድ-መካን›› እያደረግናቸው ነው፡፡ ሌላ ወልደው እንዳይተኩም ዘር አጥፊ መንገድን እያሳየናቸው ነው፡፡ የምንናገረውን የማናውቅ ከሆነ ዝም ብንል አዋቂዎች ይናገሩና መፍትሔ ይመጣ ነበር፡፡ ግን በድፍረት ብቻ ቦታውን ይዘን ነገር እያበላሸን ነው፡፡ ምን ተሸለን ? ‹‹ድፍረት ብሔራዊ ቋንቋ እየሆነባት ያለች ሀገር›› አለ እያዩ ፈንገስ........
እባካችሁ... ፖለቲከኞችን ተዋቸው። ሁሉም በየራሳቸው ዓላማ ሊቃዡም ሊያልሙም ይችላሉ፡፡ ለእኛ ከተመቹን ብቻ ይመሩናል፡፡ ካልተመቹንና እኛን ካልሰሙን ይወገዳሉ፡፡ ሕዝብን የማያመችም ሆነ የማይሰማ ፖለቲከኛ በሕዝቡ ከመወገድ የሚያድነው ምንም እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከሕዝቡ ውጭ ሆነው መኖር እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የእነርሱ ጉዳይ ሳይሆን የሕዝብ አንድነት ጉዳይ ነው ሊያሳስበን የሚገባው፡፡ እኛ ‹‹አዋቂ ነን - ጸሐፊ ነን›› ባዮች እንደ ሕዝቡ አካል ሕዝቡን እንምሰል፡፡ አብሮ የመኖር ዋስትናችን የተመሰረተው ‹‹ነፃ አውጥቸሃለሁም ነፃ አወጣሃለሁም›› በሚሉን ፖለቲከኞች ላይ ሳይሆን በእኛው (በአባቶቻችን) ‹‹የኖረና ያኖረን የሚያኖረንም›› የዳበረ የአብሮነት ባህልና ፍቅር ነው። እንደሕዝብ አንድ እንሁን። እኛ አንድ ስንሆን ፖለቲከኞች ልብ ይገዛሉ። ከሕዝብ ልብ የሌለውን አጀንዳቸውንም ይተውታል። ሕዝብ ለሕዝብ ምንም ቂም በቀል የለንም። ተዋደን፣ ተጋብተን፣ ተዋልደን፣ ተዋሕደን... እየኖርን ነው ፣ ገናም እንኖራለን። የሃይማኖትም፣ የቀለምም፣ የባህልም፣ የቋንቋም ልዩነታችን ውበታችን እንጅ መከፋፈያችን አይደለም። ሺህ ዓመታትን እንደኖርን በፍቅርና በአንድነት እንቀጥላለን።
ማስተዋሉን ያድለን፡፡
-----//-----

No comments: