አንዳንዱ የዓለም ልጅ- ከዓለም ተወልዶ- ለዓለም የኖረ
የመንፈሱን ዕውቀት- ሥጋ በተባለ- ጉድጓድ የቀበረ
በሥጋ መነፀር- የዓለምን ጉዳይ- አጉልቶና አስፍቶ
ሳይሞት የበደነ- ዓይነ ህሌናውን- ከምድር ሰክቶ
በሥጋ ፍላጎት- ለሥጋ እየኖረ- መንፈሱን ረስቶ
እርሱ መኖር ሲያቅተው- ከዓለም ባሻገር- ከህሌና በላይ
ለሰማይ ተፈጥሮ- ሰማይ ተጋርዶበት- ምድር ምድር የሚያይ
ከሞቱ በኋላ- ሕይወት አይታየው- ሞቱ መጨረሻው
ኑሮው በዓለም ብቻ- ለጽድቅ አይጨነቅ- ጽድቅ አያስፈልገው
አምላኩን አያውቀው- ጻድቃን አይራዱት- መልአክ አይጠብቀው
ከማመን የራቀ- ጠበል አያድነው- እምነት አይፈውሰው
…………………………
ምድራዊ አዕምሮው- በምድር ተወስኖ- ሀሳቡ ሲያልቅበት
ብዕሩን ያሾላል- አፉን ያላቅቃል- አድጎ ባልኖረበት
እውነት አልቦ ልቡ- እውነትን ተቃውሞ- ለማስመሰል ሀሰት
መሆኑ ያልገባው- እውነትና ሀሰት- የሰማይ የምድር
ተገድቦ እንዲኖር- ሀሰት በመቃብር- ከእውነት ጋር ላይኖር!!!!
(በመላኩ. ጥር 17/2004- መንፈስን ለሚቃወሙ ምድራውያን “ምሁራን” ነን ባዮች)