Thursday, October 30, 2014

ይህ ግን ማንን ነው የሚመለከተው? መንግሥትን ወይስ ቤተክርስቲያንን?



[መላኩ አላምረው]

ዕለተ ሚካኤል ጠዋት ነው፡፡ ሰዓት ሳይረፍድብኝ ለትምህርት ለመድረስ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍጥነት በመጓዝ ላይ ነበርሁ። ዕለቱ የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል በመሆኑ በቅ/ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ምዕመናን እንደሚበዙ ብገምትም ከ6 ኪሎ ሰማዕታት ሃውልት ጀምሮ መንገዱ ይዘጋጋል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበርና ወደ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ ለመግባት አምስተኛ በርን ምርጫዬ አደረግሁ። ልክ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልቱን እንዳፍኩ ጀምሮ ግን አይደለም በፍጥነት ተጉዤ በሰዓቱ ክፍል መግባት ቀርቶ ለመንቀሳቀስም ተቸግርሁ። ከአስፓልቱ የቀኝ ጠርዝ እስከ ዩኒቨርስቲው አጥር ድረስ የጤፍ መጣያ እስኪጠፋ ድረስ በሸቀጣሸቀጦችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም በሰዎች ተሞልቷል።

ሰው ማለፊያ ሲያጣ ወደ አስፓልቱ እየገባ፣ መኪኖቹንም ግራ እያጋባቸው፣ ሾፌሮችም እየተቆጡና ክላክስ እየነፉ. . . ይህ ሁሉ ደግሞ ከሸቀጣሸቀጥ ግዙን ባዮች ልፈፋ፣ በሞንታርቦ ከተለቀቁ መዝሙሮች “ጩኸት”፣ ከ “ባህታውያን” ነን ባዮች “ስብከት” ጋር ተደማምሮ ለአካባቢው ልዩ ትዕይንትን ፈጥሯል። አንዳንዴ መርካቶን፣ አንዳንዴ መዝሙር ቤቶችን፣ አንዳንዴ ደግሞ የሀብታም ሰርግን (የታክሲዎችን ክላክስ) ያስታውሳል። ውስጤን ሁለት ሀሳቦች ወጠሩት፡ አንደኛው የትምህርት ሰዓቴ መርፈድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስመቼ እንዲህ ይደረጋል? ለምን እንዲህ ይሆናል? ይህን የማስቆም ኃላፊነቱስ የማነው? የሚለው የብስጭት ሀሳብ። ወርሃዊ በዓላት በመጡ ቁጥር አብያተ ክርስቲያናት ወደ ገበያ ማዕከልነት ይለወጡ የሚል ህግ ወጣ እንዴ?(ብዙ ህጎች ደርሰው ስለሚወጡ)፣ ወይስ እኔ ያልሰማሁት ልዩ ዐውደ ርዕይ ይኖር ይሆን? የዛሬው ደግሞ ልዩ ነው። እንዲህ ሰው መንቀሳቀሻ እስከሚያጣ ድረስ. . . ግሩም ነው መቼም። እሺ ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም የሚፈልጉ እንዴት ይለፉ?

በርካታ ሀሳቦችን በአዕምሮዬ ሳውጠነጥን ከጫጫታው መሀል የአንዲት እናት ድምፅ ጎልቶ ተሰማኝ። “የህግ ያለህ! ኧረ የዛሬውስ የጉድ ነው ወገኖቼ. . . ሰው ለማን አቤት ይላል?ኧረ እባካችሁ አሳልፉኝ ስለት አለብኝ. . .” እጅግ በጣም ያመረሩ ይመስላል ሴትየዋ። ሲናገሩ ጉሮሯቸውን ሲቃ ይተናነቀዋል። ዓይኖቻቸውም እምባ አዝለዋል። ጩኸታቸውን ግን ማንም አያዳምጥም። መልስም የሚሰጣቸው የለም። “ሕግ ሆይ! ወዴት ተሰደድሽ?. . .” ሴትየዋ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መጮሃቸው ቀጠሉ። በዙሪያቸው ያለው ሰው በመደናገጥም በመገረምም ዓይኑን ወደርሳቸው አዞረ። የሚናገሩት ኃይለ ቃል ውስጤን ነካው። ‘ክላስ’ በሰዓቱ እንደማልደርስ ሲገባኝ ተስፋ ቆረጥሁ። እንዴት አልፌ? በሴትዮዋ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሴትየዋ ንግግር ዙሪያ የተለያየ አስተያየት መስጠት ጀመሩ። አንዳንዱ “ልክ ናቸው ሴትዮዋ። ምን ህግና ሥርዓት አለ? ህግ ቢኖር እንዲህ የቤተ ክርስቲያን መሳለሚያ እናጣ ነበር?” ይላል። ሌላው ደግሞ “ቢጨንቃቸው እኮ ነው። ዝም ብለው ቢጋፉና ቢያልፉ ይሻላል። ማን ይሰማኝ ብለው ነው አሁን እንዲህ የሚጮኹት . . .ሆ!ሆ!” እያለ ያሽሟጥታል። አንዳንዱ የባሰበትም “እባክዎትን እርስዎም ብሰው አያድርቁን። ሄደው ፖሊስ ጣቢያ አይጮሁም ከፈለጉ?” በማለት የበለጠ ሆድ ያሰብሳቸዋል።

እንደምንም ተጋፍቼ ወደ እርሳቸው ተጠጋሁና “አይዞዎት ማዘር እንደምንም ተጋፍተን እንለፈው” አልኳቸው። “አይ ልጄ.. . የመጣብን ጉድ ተጋፍተን የምናልፈውም አይመስልም። አቅም ካላችሁ ሞክሩ” አሉኝ። በንግግራቸው ትንሽ ግራ ተጋባሁና “ንግግርዎት በደንብ ግልፅ አልሆነልኝም” አልኋቸው። “ነገርኩህ ልጄ። እኛ ይሄን ችግር የመጋፋት አቅም ያለን አይመስለኝም። ጩኸታችንን የሚሰማም የለም። ቤተ ክርስቲያን ዝም። መንግስትም ዝም። ሥርዓት ጠፋ። አሁን ይሄ ለማን አቤት ይባላል? ሰላማችን እኮ ጠፋ። ሰው ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ፣ መንፈሱን አድርሶና ሰላም አግኝቶ ለመመለስ ነው የሚመጣው። ግን ሰላም የት አለ? ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከሚመጣው እኮ ለገበያ የሚመጣው በዛ። ቅዳሴ ከሚያስቀድሰው እኮ የጎዳና ላይ የሞንታርቦ መዝሙር የሚያዳምጠው በዛ። አሁን የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ነበር?” ብለው እኔን አፍጠው ተመለከቱኝ።
ከእኔ መልስ የሚሹ ስለመሰለኝ ደንገጥም ፈራም አልሁና “ኧረ ልክ ነዎት. . .ኧ. . .” ብዬ ያሰብኩትን ሳልናገር “ተመልከት” አሉኝ አንድ ባህታዊ ነኝ ባይን ከበው ወደ ቆሙ ሰዎች እየጠቆሙኝ። “ተመልከት እንግዲህ። ሥርዓተ ቅዳሴው በቤተመቅደስ እየተካሄደ ምዕመኑ በሥርዓቱ መሰረት ከካህናቱ ተሰጥኦ እየተቀበለ ማስቀደስ ሲገባው አንድ አወናባጅ መነኩሴ ነኝ ባይ ከቦ ቆሞልሃል ደግሞ እኮ እነዚህ የሀሰት ባህታውያን ሰላምን የሚሰብኩ እንዳይመስልህ፤- ጠብን እንጅ። “እስኪ ና ቀረብ ብለህ ስማ” አሉኝና አብረን ጠጋ አልን። ‘ባህታዊው’ አነስተኛ የድምፅ ማጉያን በመጠቀም እንዲህ ሲል ሰማሁና ደነገጥሁ። “ምዕመናን፣ በአሁኑ ሰዓት ካህን ያለ እንዳይመስላችሁ። ሌባ ብቻ ነው።  መንግሥትም ሌባ ነው። ጳጳሳትም ፖለቲከኞች ናቸው። መንግሥት ጳጳሳትን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው. . . የመጨረሻው ዘመን ስለሆነ በሽታው፣ ጦርነቱ፣ መቅሰፍቱ በዝቷል.. …. ‘ምዕመናን እጅግ ፈዋሽ የሆነ ከኢየሩሳሌም የመጣ ቅብዓ ቅዱስ ስላለ እየገዛችሁ’. . .ከሁሉም በሽታ ትፈወሳላችሁ . . . እናም ካህናትን አትመኗቸው...” ገረመኝ። እውነትም ሴትዮዋ ልክ ናቸው። እንዴት ነው ነገሩ?
እውነትም የህግ ያለህ ማለት ይሄኔ ነው። ይህ ጉዳይ እኮ እንደቀላል መታየት የለበትም። ጋዜጦች ብዙ ፃፉ - ዝም። ሕዝብ በየጎዳናው ምሬቱን ያሰማል - ዝም። በእንደዚህ ዓይነት ግርግሮች በርካታ ሰዎች ሞባይልና ሌላ እቃ እየተሰረቁ ያለቅሳሉ - ዝም። ለመሆኑ እነዚህን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዙሪያ የሚካሄዱ ንግዶችንና ከስርዓት ውጪ የሆኑ የመዝሙርና የ‘ባህታውያን’ ጩኸቶችን የማስቆም ኃለፊነቱ የማነው? የቤተክርስቲያን ወይስ የመንግሥት? እስከመቼስ በዚህ መልኩ ይቀጥላል? እስመቼስ ዝም ይባላል? ለመሆኑ ማን ፈቅዶላቸው ነው ወርሃዊ በዓላትን እየጠበቁ ሸቀጥ የሚዘረጉ ‘ነጋዴዎች’ የዋህ ምዕመናንን የሚረብሹት? በየትኛው ሥርዓትስ ነው መዝሙር ሻጭ ነን ባዮች በሞንታርቦ ድምፅ በሥርዓት እያስቀደሱ ያሉ ምዕመናንን የሚረብሹት? ምንም ፈቃድ ሳይኖራቸው በየመንገዱ እየቆሙ በህዝቡ ዘንድ መለያየትንና ጥላቻን የሚሰብኩ ባህታውያን ነን ባዮችስ ጉዳይ ማንነው የሚመለከተው?ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ማን ሥርዓት ያስይዝ?
ቤተክርስቲያንና መንግሥት ሆይ! እባካችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ የየድርሻችሁን ተወጡ። ለህዝቡ ሰላም አይገዳችሁምን? ቤተ አምልኮና የንግድ ቦታ መለያየት የለበትምን? ፈቃድ የሌላቸው አወናባጆችስ በየጎዳናው የጥላቻና የመከፋፈል ስብከትን ለህዝቡ ያዳርሱ ዘንድ ተፈቅዷልን? ቤተክርስቲንና መንግሥት ድርሻችሁን ለይታችሁ አውቃችኋልን? እውነት ይሄ ጉዳይ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ታስቦበታልን?
መንግሥት ያላት ሀገር ሕግ ማስከበር ካቃታትና ሲኖዶስ ያላት ቤተክርስቲያን ሰባኪዎቿንና ዘማሪዎቿን በሥርዓት ካላሰማራች ማን መጥቶ ህግና ሥርዓት ያስከብር? ይከብዳልም፤ ይገርማልም። የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሆይ! የመዝሙር አገልግሎት ‘ቢዝነስ’ ነወይ? ያውም ከሸቀጣሸቀጦች ጋር አብሮ ተሰልፎ ግዙኝ ብሎ በመለፈፍ? ኧረ ይሄ ነገር ያሳፍራል እኮ። መንፈሳዊ አገልግሎትን ለሀብት መፍጠሪያ ለማዋል ሲባል ሥርዓተ ቅዳሴውን በመረበሽ. . . ጉድ እኮ ነው። ማስተዋል ይገባናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና መንግሥት ይህን ጉዳይ ሥርዓት ለማስያዝ ብትተባበሩ መልካም ነው እላለሁ።

Thursday, October 16, 2014

የዓለም ቱሪዝም ቀን አምናና ዘንድሮ - ከአፍሪካ ጣሪያ ወደ ዓለም መሠረት!


v  በመላኩ አላምረው

እንደ መንደርደሪያ፡-
ጣሪያና መሠረት የሚሉ ቃላት ከቤት አሠራር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ጣሪያና መሠረት ባንድ ላይ የሌለው ቤት በራሱ ቤት ተብሎ ሊጠራ አይገባውም፡፡ መሠረት ከሌለው ጣሪያው አይቆምም፡፡ ጣሪያ ከሌለው ደግሞ የመሠረቱ መኖር ትርጉም የለውም፡፡ ከፀሐይም ሆነ ከዝናብ አያስጥልም፡፡ ማንም ሊኖርበት አይመኘውም- አማራጭ ከሌለው በስተቀር፡፡ አገርም እንደ ቤት ናት፡፡ ሁሉንም ልጆቿን ሰብስባ የምታኖር ታላቅ ቤት፡፡
የእኛ ኢትዮጵያም ታላቅ ቤታችን ናት፡፡ ሲከፋንም ሆነ ስንደሰት የምንጠለልባት የፍቅር ቤታችን፡፡ ይህች አገር መሠረትና ጣሪያ አላት፡፡ መሠረትና ጣሪያ ባይኖራትማ ኖሮ እንደዚህ በክብርና በፍቅር አንኖርባትም/አታስኖረንም ነበር፡፡ ጽኑ መሠረትና ጠንካራ ጣሪያ ስላላት አባቶቻችን ኖሩባት፤ እኛም እየኖርንባት ነው፤ ልጆቻችንም ይኖሩባታል፡፡ ልጆቻችን ይኖሩባት ዘንድ ደግሞ መሠረቷንና ጣሪያዋን የበለጠ ማጽናትና ማጠናከር ከእኛ ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል፡፡ የአገር መሠረትነትና ጣሪያነት ትርጉሙ ጠለቅ ያለና ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ስለሆነ እይታችንን ወደ አንድ አቅጣጫ እናድርገው፡፡ ወደ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና ወደ ሰው ዘር መነሻነት…..
ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረትና ጣሪያ ያላት ቤት ብቻ አይደለችም፡፡ ለዓለምም መሠረትነት አላት፡፡ ለዓለም መሠረትነቷ ምንድነው? ይህች አገር ጣሪያ ያላት ቤት ብቻም አይደለችም፡፡ ለዓለም በተለይም ለአፍሪካ ጣሪያነት ያላት ድንቅ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጣሪያነቷ ከምን አንፃር ይሆን? ይህንንስ ከቱሪዝም በተለይም ከዓለም ቱሪዝም ቀን ጋር ምን ያገናኘዋል? ይህ ጽሑፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡ ሌሎችንም ከአምናና ዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀናት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል የተባበሩት መንግስታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ለተመሠረተበት ቀን (መስከረም 17/September 27 እኤአ 1970) መታሰቢያነት በየተራ በሚመረጥ አገርና ወቅቱን ባገናዘበ ልዩ መልእክት ታጅቦ በሁሉም አባል አገራት ዘንድ እኤአ ከ1980 ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ ለዚህ በዓል የተመረጠው መሪ መልእክት በዕለቱ ብቻ እንደ መፈክር ተነግሮና ተደምጦ የሚታለፍ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር ተጣጥሞ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን በየዓመቱ በድምቀትና በልዩ ትኩረት የመከበሩ ዋና ዓላማም ቱሪዝም ለዓለም አቀፍ ማህበረስብ የሚያበረክተውን ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የአካባቢ ጥበቃ/እንክብካቤ እና ፓለቲካዊ ፋይዳዎች በአጽንኦት በማሳየት ለዓለም ማኅበረሰብ ሁሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ለዚህ በዓል ሲባል የሚመረጠው መሪ ቃልም ሆነ የሚተላለፈው መልእክት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሌኒየም ግቦች (MDGs) ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ነው፡፡ ይህ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓልም በዋናነት የመንግሥታቱን ድርጅት የሚሌኒየም ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ርብርቦሽ ውስጥ ለሚያጋጥሙ መሰናክሎችና ፈታኝ ሁኔታዎች እንደ መፍትሄ ጠቋሚ ብቻ ሳይሆን ዋናው የመፍትሄ አካል ተደርጎም ይወሰዳል፡፡  
ኢትዮጵያ እንደ አባል አገር የዓለም ቱሪዝም ቀንን ማክበር ከጀመረች እነሆ አሁን ለ27ኛ ጊዜ ሲሆን በየክልሉ በመዘዋወር በጋራ ሲከበር ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ ነው፡፡ የመጀመሪያውን አገራዊ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል በክልል ደረጃ ያከበርነው በ2001 ዓ.ም. በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልል የጋራ አዘጋጅነት ነበር፡፡ ሁለተኛውን በ2002 ዓ.ም. በሀረሪ ክልልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ሦስተኛውን በ2003 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ አራተኛውን በ2004 ዓ.ም. በትግራይ ክልል፣ አምስተኛውን በ2005 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስናከበር በ2006 ዓ.ም.ማለትም የአምናውን የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል ደግሞ በአማራ ክልል አክብረናል፡፡
በሁሉም ክልሎች የተከበሩት በዓላት የየክልሉን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች በስፋት በመጎብኘትና ለኅብረተሰቡ ስለ ቱሪዝም ምንነት የሚፈጥሩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማከናወን ነበር፡፡ የቱሪዝም ባለድርሻ አካላትም ሆኑ የመስህቦች ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ በቀጥታ የተሳተፈባቸው እነዚህ የዓለም ቱሪዝም ቀናት በየክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሳደሩት አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በየዓመቱ በሚዘጋጁት የቱሪዝም ሲምፖዚየሞች ላይ በአራዊም ሆነ በየክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ተጠንተው የቀረቡና ውይይት የተደረገባቸው የጥናትና ምርምር ጽሑፎችም በርካታ ተሞክሮዎችን የተለዋወጥንባቸው፣ ችግሮችን ያሳዩና መፍትሔዎችንም የጠቆሙ ስለነበሩ ለዘርፉ ለውጥ መነቃቃት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡
በአንዳንድ ክልሎችም የዓለም ቱሪዝም ቀንን መከበር ምክንያት በማድረግ በተደረጉ ውይይቶችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ በተለይም የየክልሉን ፕሬዝዳንቶችና ወሳኝ አካላትን ባካተተ መልኩ በተደረጉ መግባባቶች በዘርፉ በነበሩ የአደረጃጀት ክፍተቶች ላይ ማስተካከያዎችን እስከማድረግ ድረስ ተችሏል፡፡ በየዓመቱ በበዓሉ ላይ በሚሳተፉ የመንግሥትም ሆነ የግል ብዙኃን መገናኛዎች አማካኝነትም የየክልሉን ቱባ ባህልና እምቅ የቱሪዝም ሀብት በስፋት ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ በየዓመቱ በተለይም መስከረም ወር ላይ የአገራችን ኅብረተሰብ ከዳር እስከ ዳር ስለቱሪዝም እንዲያወራና እንዲወያይ ለማደረግ ሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ ወቅት በየደረጃው ቀኑን በደማቅ ዝግጅት እያከበሩት ይገኛሉ፡፡ ከዋናው በዓል ቀጥሎ በሚከናወኑ የብዙኃን መገናኛዎች ዘገባና ሌሎች ተከታታይ ሥራዎች አማካኝነት ቱሪዝም ዓመታዊ አጀንዳ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ በየክልሉ በመዘዋወር የሚከበረው ይህ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል እጅግ ደማቅ፣ የሁሉንም ቀልብ የሚስብና ለዘርፉ ለውጥ የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ተወዳጅ ዝግጅት እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ዓይነተኛ መንገድ እየሆነ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመትም ከአገራችን ክልሎች ብቻ ሳይሆን ከዓለምም ጭምር እጅግ ዝቅተኛው ቦታ (Danakel Depression) መገኛ ወደሆነውና የዓለምን ቱሪስቶች ቀልብ እየሳበ የሚገኘው የኤርታ-አሌ የማያቋርጥ እሳተ ገሞራ (Arta-Alle Active Volcano) ወደሚገኝበት የአፋር ክልል በመጓዝ ዝግጅቱን በድምቀት እናከብራለን፡፡ በዚህ ልዩ ዕትማችንም የክልሉን መስህቦች ባጭሩ እናስቃኛችኋለን፡፡ ስለ አምናው የዓለም ቱሪዝም ቀን ትውስታ እንዲኖራችሁም በተወሰነ መልኩም ቢሆን  ወደ ኋላ ሄደን ከዚህ ዓመቱ በዓል ጋር በማስተሳሰር ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡
የየበዓላቱን መሪ መልእክታትና የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ፣ በዓላቱ የተከበሩበት/ የሚከበሩበት ክልልና የመሪ ቃላቱ ልዩ አጋጣሚያዊ ትስስር፣ የነበሩ/የሚኖሩ ልዩ ገጽታዎችና ሌሎችም ጉዳዮች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ፡፡ ዓባይ በሕዳሴ ግድብነት ከትሞ የአገራችንን ታላቅነት ለማሳየት ወደ ጉባ (ቤኒሻንጉል) ለመጓዝ ከተፀነሰባቸውና ረጃጅም እግሮቹን ከዘረጋባቸው የጎጃምና የጎንደር ተራራዎች ተነስተን የሚወለድበትን ጣናንና የልደት አጃቢዋን/አድማቂዋን ውቢቷ ባህር ዳርን ቃኝተን እጅግ በፈጠነ ጉዞ ወደ አፋር እንወረወራለን፡፡

በፈጣኑ የወፍ በረር ጉዟችንም አፋርንና ድንቃድቆቿን እየጎበኘን በአማራዎቹ የሰሜን ተራራ በረዶና በዓባይና ጣና ውኃ ቅዝቃዜና ብርድ ሲሰማን ከአፋሩ ኤርታ-አሌ እሳት እንሞቃለን፡፡ በአፋር በረኃና በኤርታ-አሌ እሳት ሙቀት ሲሰማን ደግሞ ወደ ሰሜን ተራራ በረዶና ወደ ጣና ሐይቅ በትዝታ መለስ ብለን ቀዝቀዝ እንላለን፡፡ ሁሉም በቤታችን አለ፡፡ ሜዳው፣ ተራራው፣ ሙቀቱ፣ ቅዝቃዜው፣ ሐይቁ፣ አሸዋው፣ ጫካው፣ ብርቅዬ አዕዋፍና የዱር እንስሳት….. የፈለግነው ሁሉ አለ፡፡ ምክንያቱም ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ዓይናችን የሚራበውም ሆነ በማየት የሚሰለቸው ነገር አይኖርም፡፡ ለዓይናችን፡- እነሆ የመስህብ በየዓይነቱ!….. ጉዟችን ከጣሪያ ወደ መሠረት- ከበረዶ ወደ እሳት ነው፡፡ መልካም ጉዞ!...... To be Continued...