(መላኩ አላምረው)
…
‹‹ይቅርታ አድርጉልኝና
ጋሽ ጣሰው… በዓለም ላይ ከሚገኙና ሃይማኖታዊ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ሀገሮች ውስጥ እንደ ኢትዮጵያውያን የሚጾም አለ ብዬ አላምንም፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያውያን ጾም ለሀገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ መፍትሔን ሳይሆን ችግርን ከሰማዬ ሰማያት እያወረደ የሚደምር… የሚከምር…
የሚጭን… መስሎ ከታዬኝ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ጾም ቢቆም የተሻለ ቀን የሚመጣ ይመስለኛል…›› አለ
የኪራይ ጓደኛዬ ፈላስፋው ጣሴ የዐቢይ ጾምን በጀመርንበት የመጀመሪያ ቀን ምሽት፡፡ ጣሴ መጠየቅ ይወዳል፡፡ ሰው ዝም ሲል አይወድም፡፡
ብዙ ጊዜ ዝምታዎችን የሚሰብርበት መንገድ ደግሞ ጥያቄ ማንሳት ነው፡፡
ትላንትና ምሽት
ከአከራያችን ከጋሽ ጣሰው ቤት የጾሙን መጀመር ምክንያት በማድረግ ቡና እንድንጠጣ ተጠርተን ገባን - ጣሴ እና እኔ፡፡ በጥቁር ቡና
ግብዣው ላይ እኛ አይተናቸው የማናውቅ የጋሽ ጣሰው ጎረቤቶችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ መምህሬ ለይኩንን አይተናቸው አናውቅም፡፡ (ተከራይ
የአከራዩን ጎረቤቶች ሳያውቅ የሚኖርባት ከተማ አዲስ አበባ ናት የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም ትላንት ግን ውስጤን የተሰማው ስሜት የባዕድነት
ነበር፡፡ በጋሽ ጣሰው ግቢ ከ2 ዓመት በላይ ስንኖር ቢያንስ መምህሬ ለይኩንን የመሰለ ሊቅ ጎረቤት ማወቅ አልነበረብንም?)
የጣሴን የዝምታ
መስበሪያ ጥያቄ በሌላ ጥያቄ በመመለስ የቀጠሉት መምህሬ ነበሩ፡፡
‹‹ለእኔም ይቅርታ
አድርግልኛና… ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊት ጾምን የሚጾማት ምዕመን ቁጥር ስንት ይሆናል? እንዴት ባለ ጥናት ላይ ተመርኩዘህ
ነው የእኛን ሀገር ጿሚዎች ቁጥር ከሌላው ዓለም ከፍ ያደረግኸው?››
(፡›መምህሬ ለይኩን
በ50ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ ያሉ ጎልማሳ ቢሆኑም የፊታቸው ቆዳ መሸበሸብና የወገባቸው መጉበጥ… ባጠቃላይ የሰውነታቸው ሁኔታ የ70
እና የ80 ዓመት ሽማግሌ አስመስሏቸዋል፡፡ ጎረቤቶቻቸው እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች በሚነሱ የሃይማኖት ነክ ውይቶች ላይ የሚሰጡትን
ጥልቅ ማብራሪያ መሠረት በማድረግ ‹‹መምህሬ›› ይበሏቸው እንጅ በየትኛውም ደብር አያገለግሉም፡፡ በትምህርት በኩል ግን የሐዲስ
ኪዳን መምህርነት ምስክር አላቸው፡፡ ቅኔና አቋቋምም ተምረዋል፡፡ ልክ የዛሬ 15 ዓመት ከጎጃም መጥተው አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ
አድባራት ውስጥ በአንዱ ለመቀጠር ቤተ-ክህነቱን ደጅ ቢጠኑም ‹‹ሲሆን 7ቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ካልሆን ደግሞ 5ቱን አዕማደ
ምሥጢራት አጥንተህ ተመልሰህ ና፤ ከዚያ ትቀጠራለህ፡፡ ያለበለዚያ በከንቱ አትድከም›› የሚል መልስ ተሰጥቷቸው ይህንን ማድረግ ስላልቻሉና
በአሠራሩም እጅግ ስላዘኑ መጽሐፍ አዟሪ ሆነው ቀሩ፡፡ የተጠየቁት ምሥጢር ሳይሆን 7 እና 5 ሺህ መሆኑ ሲገባቸው አዕምሯቸው ቆስሎ
እንደቀረ በምሬት ይናገራሉ፡፡)
ጣሴ በመምህሬ ድንገተኛ
ጥያቄ ደንገጥ ብሎ… ‹‹ይሄ እኮ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ የሀገራችን ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም በጾም አይታማም፡፡ በአጽዋማት ወቅትም
አድባራቱና መስጂዶቹ ሁሉ በሕዝብ ይጨናነቃሉ፡፡ በተለይ በዓቢይ ጾምማ ይለያል፡፡ ሳይቀደስበት የሚውል ደብርና ገዳም የለም፡፡ እ….››
እያለ ነገር ሊያሰፋ ሲል መምህሬ አቋረጡት፡፡
‹‹ይቅርታ አድርግልኝ
ወንድሜ… የምትለው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ‹መንፈሳዊት ጾምን› አይገልጽም፡፡ በልማድ የሚደረግንና በብዙ ሕዝብ የታጀበን
ጾምና ቅዳሴ በመመልከት ብቻ ‹የሃይማኖተኞች ሀገር ፣ ሀገረ እግዚአብሔር … ምናምን› እያሉ መተረት ትርጉም የለውም፡፡ ወዳጄ…
ለአንተና ለመሰሎችህ ብዙ ያልተገለጠላችሁ ነገር አለ፡፡ በተለይ የሀገራችን ሃይማተኝነት ጉዳይ፡፡ የጠመጠመ ሁሉ ቄስ አይደለም፡፡
ለንግሥ የሚወጣ ሁሉም ሃይማኖተኛ አይደለም፡፡›› አሉ መምህሬ ሀዘን በሚነበብበት አነጋገር፡፡
‹‹ንግግርዎት ሊገባኝ
አልቻለም… ሃይማኖት በተከታዮቹ ቁጥር እንጅ በምን ይለካል? ጾምስ በጿሚው ምዕመን ካልሆነ በምን ይታወቅ?›› አለ ጣሴ ግራ በተጋባው
ስሜት፡፡
ጋሽ ጣሰው ጣልቃ
ገብተው… ‹‹አይ ጣሴ… ምነው ፈላስፋ ነኝ ምናምን እያልህ ስታደነቁረንም አልነበር? እንዴት የመምህሬ ንግግር አልዘለቀህም ጃል?
ነው ፍልስፍና የሃይማኖትን ነገር ማለቴ የጾምንና አጿጿሙን ጉዳይ አያካትትም? አሂሂ… ያንተ ፍልስፍና ሊታይ ነዋ!›› አሉት ፌዝ
በተቀላቀለበት ድምጸት፡፡
‹‹በሃይማኖት ውስጥ
‹አምኖ መቀበል› እንጅ ፍልስፍና ቦታ እንደሌላት ስለማውቅ ነዋ !›› አለ ጣሴ ለጋሽ ጣሰው ጥያቄ መልስ፡፡
‹‹አይ… እንደዚህ
አይነት መረዳት አይኑርህ ወዳጄ ! ፍልስፍና ጥበብ ነው፡፡ ጥበብን በማስተናገድ በኩል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን የሚቀድምም የሚበልጥም
የለም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ ዘመን የሥጋውያንና የብዑላን መሰብሰቢያ ሆነች እንጅ…›› መምህሬ ለይኩን ተናገሩ፡፡ ፊታቸው
ሀዘን እንጅ ቁጣ አይነበብበትም፡፡
‹‹የጾሙን ጉዳይ
ያጠቃሉልንማ… መምሬ›› አሉ ጋሽ ጣሰው የመምህሬን ንግግር መርዘም ያልፈለጉ በሚመስል ጣልቃ ገብነት፡፡
‹‹የጾሙ ጉዳይማ…
ባጭሩ በሀገራችን በተለይም በከተማችን ‹መንፈሳዊት ጾም› እየተጾመች ስላልሆነ ነው ልጁ (ጣሴን ነው) ያለውን ሁኔታ የምናስተውለው፡፡
በየደብሩ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ኪዳን ይደረሳል፤ ሕዝቡም በተለይ በዓላትንና አጽዋማትን እየጠበቀ ይሰበሰባል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በዓለማውያን
ዘንድ እንኳን የሌለ ዘረኝነትና አድሏዊነት፤ ጥላቻና መገፋፋት ያለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ… ያውም አገልጋዮች ነን በሚሉትና በተለያዬ
የሊቅነት ማዕረግና ሥልጣን በተሸከሙት ዘንድ ነው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ውጩ ነጠላ ለብሶ እንደሚታየው ንጹህ አይደለም፡፡ ከተንኮልና
ከክፋት ሳይጾሙ ከእህልና ውኃ ቢከለከሉ ምን ትርጉም አለው? ከክፉ ሥራ ሁሉ ርቀውና ንሰሐ ገብተው ያልጾሙት ጾም… ልጁ እንዳለው
ምን አልባት መዓትን እንጅ ምህረትን እንዴት ሊያመጣ ይችላል? መነፈሳዊት ጾምስ እንዲህም አይደለች፡፡››
መምህሬ ይህንን
እንዳሉ በቀጣይ ተገናኝተን ስለ ብዙ ጉዳዮች እንደምንነጋገር ቃል አስገብቻቸው ወጣሁ፡፡
ሰላም ይብዛልን
!