(መላኩ
አላምረው)
…
ብዙ ጊዜ ሲባሉ ከሚገርሙኝ
ንግግሮች መካከል፡-
‹‹እግዚአብሔር
ይመስገን ጭፈራ ቤት ከከፈትሁ ወዲህ ጥሩ ገባያ እያገኘሁ ነው››
‹‹ፈጣሪ ፈቃዱ
ከሆነ የመጠጥ ቤቱን አስፋፍቼና የመጠጥ ዓይነቶችንም ጨምሬ ለመስራትና ሀብቴን ለማሳደግ አስቤአለሁ… ሁሉም ፈቃዱ ይሁን!››
‹‹እንደ
እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዓመት የዘፈን አልበሜን እጨርሳለሁ… በተለያዩ ጭፈራ ቤቶችም ሥራዎቼን በማቅረብ ገቢ አገኛለሁ፡፡
ከአምላኬ ጋር መጭው ጊዜ መልካም ይሆናል፡፡ ክብር ለእርሱ ይሁን!››
‹‹አምላክ
ፈቅዶልኝ የዚህ ቢሮ ኃላፊ ብሆን… የምሠራውን አውቅ ነበር፡፡ በተለይ ምስኪን ቤተሰቦቼን ቀን አወጣላቸው ነበር››
…ሌላም ሌላም፡፡
ብቻ እኛ ሰዎች
ስንባል… የምንናገረውን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ ወይም መጽሐፍ እንዳለ… ከእውቀት ማነስ የተነሳ ጠፍተናል፡፡ በእውኑ ሰው
በሙስናና በዘረፋ፣ በመጠጥና በዳኪራ፣ በማጭበርበርና በወንጀል ለሚያገኘው ምድራዊ ኮተት የእግዚአብሔርን እርዳታና ፈቃድ ሰበብ
ሊያደርግ ይችላልን? አንድ ሰው በስሜታዊ ባሕርይው ብቻ እየተነዳ የሚያደርገውንና የሚከናወንለትን ነገር ሁሉ የአምላክ ፈቃድ
ነው ማለት እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርስ የሰው ልጅ በኃጢአት ሥራዎች ባገኘው ምድራዊ ድሎት ምክንያት ያመሰግነው ዘንድ
የሚወድ አምላክ ነውን?
የእግዚአብሔር
ፈቃድ መልካም ነገር ሁሉ እንጅ በተቃራኒው ኃጢአት የሆነና የሰውን ልጅ ስማታዊ አድርጎ ወደ ኃጢአት የሚመራ ነገር አይደለም፡፡
ከመልካም ነገር በተቃራኒ ያሉ ሰውንም በስሜት የሚነዱና ለኃጢአት ባሪያ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ አምላክ የፈቃዳቸው ናቸው
ማለት የአፍ ልማድ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችም፡፡ ሰው በተሰጠው ነጻነት የሚያደርገውን፣ በራሱ የአዕምሮ ፈቃድና የልብ መሻትም
የሚፈጽመውን ሁሉ አምላክ ፈቅዶልኝ ነው ይል ዘንድ እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርስ ሰው ይሰርቅ፣ ይዘሙት፣ ይገድል፣ ይቀማ፣
በስሜት እየተነዳ ይጠጣ፣ ይጨፍርና መንፈሳነቱን ይረሳ ዘንድ ፈቅዶ ከሰው ጋር የሚተባበር አምላክ ነውን? እንዲህ የምናስብ
ከሆነ የአምላክን ባሕርይ አላወቅንም ማለት ነው፡፡ እነዚህን የሥጋ ፍሬዎች እንድናፈራ አምላክ ፈቅዶልናል፣ ረድቶናልም እያልን
ፈጣሪን ከፍጡር ያውም በስሜት ከሚነዳ ዓለማዊ ሰው ጋር እየደመርነው እንደሆነም እናስተውል፡፡
አምላክ
የሚፈቅደውና የሚወደው ሥራ ግን መልካምና ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላ ነው፡፡ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣት፣ እንግዳን መቀበል፣ የተራዘን ማልበስ፣ የታመመን መጎብኘት፣ የታሠረን መጠየቅ እና የመሳሰሉት ሁሉ መልካም ፈቃዱ ናቸው፡፡ ሰላምን መሻት፣ ፍቅርን
መስበክ፣ ከስሜታነት ይላቀቅና በአዕምሮው ያስብ ዘንድ ሰውን ማስተማር፣ መከባበርንና መተሳሰብን ሕይወት ማድረግ ሁሉ ፈቃዱ
ናቸው፡፡ ምድርን ማልማትና ፍሬዋን መብላት፣ በአግባብና በሥርዓት የሥጋን ፈቃድ መፈፈፀም፣ በተሰጠን አዕምሮ ተመራምሮ ለሰው
ልጅ ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ሁሉ የተፈቀዱ
ናቸው፡፡ (ሰው የፈጣሪነት ጸጋ ተሰጥቶታልና)፡፡
(፡› ነገር ግን የሰውን ልጅ ከአዕምሯዊነትና ከመንፈሳዊነት ባሕርይው ይልቅ
በስሜታዊ ባሕርይው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ በግብታዊነት ይኖር ዘንድ ቀፍድደው የሚይዙ ነገሮችን ሁሉ ባደረግን ጊዜ… ይህ
በተሰጠን ነጻ ፈቃድና ምርጫ ተጠቅመን የምናደርገው እንጅ ፈጣሪ ፈቅዶልን እያገዘንም የምናደርገው አይደለም፡፡ አምላክ ለሰው
ልጅ ነጻ ፈቃድና ምርጫን ያለገደብ መስጠቱ የነጻነት አምላክ መሆኑን እንጅ የኃጢአት ተባባሪነቱን አያሳይም፡፡ ይህ ራሳችንን
እያጸደቅንና ለክፋታችን ይቅርታ እያደረግን የመኖር ልምምድ አወዳደቃችንን ያከፋው ካልሆነ በቀር የሚጠቅመን አነዳች ነገር
የለም፡፡
የሰው ልጅ በምድር ብቻ የተወሰነ ሕይወት እንዳለው ካሰበ ግን… ኃጢአትና ዘራዝርቱ
ሁሉ ለጊዜውም ቢሆን ይስማሙታል፡፡ ራሱን ጻድቅ እያደረገና ወንጀሉን በድፍረትና በማናለብኝነት እየፈጸመ ይኖራል፡፡ ይህንንም
አምላክ ፈቅዶልኝ ነው ሊል ይችላል፡፡ ይህ ግ የአለማወቅና የአለማስተዋል ጥግ ነው፡፤ አምላክስ ከመልካም ነገር ውጭ እናደርግ
ዘንድ የሚፈቅድ ባሕርይ የለውም፡፡ መልካም ነገርን ማያደርግና በተቃራኒው የተሰለፈ ሁሉም ከእርሱ ጋር ኅብረት የለውም፡፡
ለራሳችን ኃጢአት ራሳችን ይቅርታ እያደረግን የመኖር ልምምድ አወዳደቃችንን
ያከፋዋልና ወደ ሕሊናችን እንመለስ፡፡