Wednesday, December 30, 2015

ብቻችንን አይደለንም! - የሚጠብቁን መላእክት አሉ!


(መላኩ አላምረው)

እኔ እስካሁን ባለኝ ግንዛቤ መላእክት እንዳሉ የማያምን ሃይማኖት/የእምነት ተቋም በእኛ ሀገር እንዳለ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለምእመናን ባላቸው ድርሻ አንዱ ከሌላው የተለዬ አስተምህሮና እምነት ቢኖራቸውም በመላእክት መኖር ግን ያምናሉ፡፡ ኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት… ሁሉም የመላእክትን መኖር ይቀበላሉ፡፡ መላእክት ለሰው ልጆች በሚሰጡት አገልግሎት ግን አንዱ ከሌላው ይለያያሉ፡፡ የተወሰኑት መላእክት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚላላኩ መናፍስት ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሰው ከኃጢአቱ ይድን ዘንድ በአማላጅነት ይራዳሉ፣ ለጽድቅ ሥራ ሰውን ያግዛሉ፣ በነገረ ድኅነት ውስጥ ድርሻ አላቸው… ብለው ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ መኖራቸውን ተቀብለው አማላጅነታቸውን (ለድኅነት ያላቸውን ድርሻ) በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የመላእክትን አማላጅነት/አለማማለድ ወይም ሌላ የአገልግሎት ድርሻ ለመስበክ አይደለም፡፡ ‹‹የሰው ልጆች ብቻችንን እንዳልሆንና በመላእክት እንደምንጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?›› የሚለውን ለማሳየት እንጅ፡፡ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ መጽሐፍ ነው ብሎ የሚቀበል ሰው ይህንን እውነት ያውቅ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመላእክት መኖር የሚያምን ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ሰውም ቢሆን ይህንን ጽሑፍ ቢያነበው ስለ መላእክት ያለውን እውቀት ያሰፋለታል እንጅ አይጎዳውም፡፡
ወደ ጥቅስ ከመሄዳችን በፊት እንዲሁ በአመክንዮ (Logical Reasoning) ለማየት እንሞክር፡፡ መላእክት አሉ ብለን ካመንና መኖራቸውም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው ካልን… ‹‹የእነርሱ መኖር ለእኛ አስፈላጊነቱ ምንድነው? እነርሱ ባይኖሩ ምን ይቀርብናል? ወዘተ…›› የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ አለብን፡፡ የመላእክት መኖር ለሰው ልጅ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም ብለን ካመንን ደግሞ ‹‹ለሰው የማያስፈልግ ነገር ግን ከሰው ጋር ወይም በሰውና በፈጣሪ መሐል የሚኖር ፍጥረት ሊኖር ይችላልን?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለብን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ግን መለስ የሚኖረን አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ ለእኛ የማያስፈልግ ምንም ነገር በዙሪያችን ሊያኖር አይችልም፡፡ እኛ ጥቅማቸውን አላወቅንም ማለት አይጠቅሙንም ማለት አይደለም፡፡
ፈጣሪ አምላክ የማይታይ መንፈስ ነው ካልን በቅርበት ሊያገለግሉት የሚችሉት መናፍስት ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ለመንፈስ ባሕርይ ከሥጋ ለባሽ ፍጥረታት ይልቅ መናፍስት ይቀርባሉና፡፡ ለዚህም ነው ሰው ሥጋ እንደለበሰ ወደ ሰማይ (ወደ መናፍስት ዓለም) መሄድ የማይችለው፡፡ ነገር ግን በሥጋ ከሞተ በመንፈሳዊ ባሕርይው (በነፍሱ) እስከተገባው ቦታ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይቀርባል ብለን እናምናለን፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ሥጋው ተለውጦና እንደ መናፍስት የማይሞት ባሕርይን ይዞ ነው የሚነሳው (በትንሣኤ ሙታን)፡፡
መንፈስ ለሆነው አምላክ መናፍስት የሆኑ አገልጋዮች አሉት/ሊኖሩት ይገባል በሚለው ከተስማማን ደግሞ አገልግሎታቸው በፈጣሪና በፍጡራን መሐከል ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ (በቀላል ምሳሌ ለመመሰል… የአንድ ሀገረ ገዥ የቅርብ አገልጋዮች/ሹማምንት ማለት የሚገዛውን ሕዝብ ከእርሱ ጋር የሚያገናኙ፣ መልእክትን ከእርሱ ወደ ሕዝቡ፣ ከሕዝቡም ወደ እርሱ የሚደርሱ ናቸውና - ይህ ካልሆነም የቅርብ አገልጋይ አስፈላጊነቱ ምንም ነውና)፡፡
መላእክት ለፈጣሪ ከሰው ልጆች ይልቅ ቅርብ የሆኑ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ፍጡሩን ሁሉ ሲገዛ በየደረጃው ለፍጡራኑም የገዥነት ሥልጣንን በጸጋ ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ አዳም ለምድር ፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፡፡ መላእክትም በየደረጃቸው ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ የፍጡራን ሥልጣን ግን ከፈጣሪ ዘንድ በጸጋ የሚገኝና ከፈጣሪ ፈቃድ ውጭም ሊሆን የማይችል መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ፈጣሪ የዓለም ሁሉ ገዥ ነው፡፡ በየፍጥረቱ (በየወገኑ) የሾማቸው መናፍስት የሆኑ ፍጥረታት ደግሞ ይኖሩታል/አሉት፡፡ እነርሱም መላእክት ናቸው፡፡ ፈጣሪ ዓለምን ሲገዛ በጸጋ ሌሎች ገዥዎችን እንደሚሾም ከአዳም ተፈጥሮ መረዳት ይቻላል፡፡ እርሱን የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማለክት አምላክ የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡ ከሁሉም ግን ለእርሱ በባሕርይ መናፍስት የሆኑ መላእክት ይቀርቡታል፡፡ እነርሱንም ወደ ሌላው ፍጥረት ሁሉ ይልካቸዋል፡፡ ወደ ሰውም ጭምር፡፡ መላእክት ከመላው ፍጥረት ጋር ስላላቸው ግንኙነት በዚህ ጽሑፍ ማንሳት አልፈልግም (ካስፈለገ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)፡፡
የመላእክት ጠባቂነት ለሰው ልጆች እንዴት ?
በመጀመሪያ ደረጃ መላእክት እኛን የሰው ልጆችን ከልጅነት ጀምሮ በመንከባከብ ይጠብቁናል፡፡ ለዚህ ማስረጃነት ከመጽሐፍ ቅዱስ 2 ጥቅሶች ብቻ እንመልከት፡፡ ከብሉይ ኪዳን ለመጀመር ከደጋግ አባቶች አንዱ የሆነው ያዕቆብ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ የመገበኝ እግዚአብሔር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ የጠበቀኝ/ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች/ሕጻናት ይባርክ›› በማለት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እንዳዳነውና እንደጠበቀው ያስረዳል …ዘፍ 48፥16፡፡ ይህም መልአክ ልጆቹንም ይባርክለት/ያከብርለት ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ቃል በትንቢተ ዳንኤል ላይ… ዳንኤልን መልአኩ እንዴት ይጠብቀው እንደነበር… በኋላም ሠልስቱ ደቂቅን (ሦስቱን ሕጻናት) የእግዚአብሔር መልአክ ከእቶን እሳት እንዴት ጠብቆ እንዳዳናቸው ተጽፏል፡፡
አይ… ይሄ የሐዲስ ኪዳንን አምልኮ አይወክልም ካልን ደግሞ የሚከተለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል እንመለከት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.18፡ቁ.10 ላይ… ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ ‹‹አንዱን›› እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ ‹‹መላእክቶቻቸው›› ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።›› ይላል፡፡ ይህ ቃል ሁሉም ሰው መላእክት እንዳሉት ያሳያል፡፡ እነዚህ መላእክት ሊጠብቋቸው ካልሆነ ለምን ከታናሾች ጋር ይኖራሉ? ልብ ብለን እንመልከት… ‹መላእክቶቻቸቸው› ‹ዘወትር› የፈጣሪን ፊት ያያሉ… ማለት ስለሚጠብቋቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ይጠየቃሉ፣ ይናገራሉም፡፡ ‹ፊቱን ያያሉ› ማለት ለአገልሎት/ለመልእክት መቅረብን እንጅ ፈጣሪን እንደ ሰው ገጹን ማየትን አያመለከትም፡፡ ይህ ለፍጡራን አይቻልምና፡፡
ከዚህ ላይ ሌላ ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ… ማንንም ሰው ታናሽ ነው… አቅመ ቢስ ደካማ ነው… ብሎ መናቅና በእርሱም ላይ በደል ማድረስ በሰው ፊት ባይሆን እንኳን በፈጣሪ ፊት እንደሚያስከስስ ነው፡፡ ሰው ብቻውን አይደለም፡፡ ዘወትር ስለበደላቸው ለፈጣሪ የሚናገሩ መላእክት አሉና፡፡ ለዚህም ነው ምዕመናን የመላእክትን ጥበቃ ተስፋ የሚደርጉት፡፡
እስኪ ማጠቃለያ ጥያቄ እናንሳ… ለመሆኑ አንድ መልአክ በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላልን ? ለምሳሌ የገብርኤል በዓል ዕለት በሁሉም ቦታ ሕዝቡ ወጥቶ የሚያነግሰው በሁሉም ቦታ ካልተገኘ ለምን? ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የመላእክትን ተፈጥሮ ነው፡፡ መልአክ በባሕርይ ተፈጥሮው መንፈስ ነውና ይችላል፡፡ በሥጋ ስሌት ካላሰብነው በቀር ይህ ለመናፍስት የተሰጠ ጸጋ ነውና በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላል፡፡ በመዝ. 33፥7 ላይ የተጻፈውን ልብ እንበል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ‹መልአክ› ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹ዙሪያ› ‹ይሠፍራል›፣ ‹ያድናቸውማል››› ይላል፡፡ ‹‹መልአክ›› ብሎ አንድ መሆኑን… ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹‹ይሰፍራል›› ሲል ደግሞ ለብዙ ቁጥር የሚሆነውን ቃል ተጠቀመ፡፡ ሰፈረ… ብዙ ቦታ ላይ ተገኘ… እንደማለት ነው፡፡ እንዲያውም በብዙ ሰዎች ‹ዙሪያ› ነው ሚሰፍረው፡፡ አንድ ሰው ቢሆን ኖሮ በሌላው ሰው ‹‹ዙሪያ›› ሳይሆን ወይ በፊት ወይ በጎን ነበር ሚቆመው፡፡ እዚህ ላይ አንዱ መልአክ ግን በዙሪያቸው ሲሰፍር ያሳያል፡፡
በመጨረሻም… ለሰው ልጆች የመላእክት ጥበቃ ያስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት ፈጣሪ በራሱ ፍጡሩን መጠበቅ ስለማይችል ወይም በደላችንን የማያውቅ ሆኖ ሳይሆን ለፍጡራኑ የአገልግሎት ድርሻ ለመስጠት ነው፡፡ በመላእክትም ጠበቀን በራሱም ጠበቀን ዞሮዞሮ ጥበቃው የፈጣሪ ነው፡፡ ፍጡር በየደረጃው እያገለገለ መንግሥቱን ይወርስ ዘንድ የአምላክ ፈቃድ ነውና… በምድርም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ምድርንም እርሱ ፈጥሮ ይገዛት ዘንድ ለሰው ልጅ ሰጠ፡፡ የሰው ልጅም አገልጋይነቱን ከተረዳና በሥርዓት ከኖረ ለሌላ ሰማያዊ መንግሥት ይበቃል፡፡ መላእክትም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአገልግሎታቸው ካልተጉ እንደ ሣጥናኤል ከፈጣሪ ክብር ይርቃሉና ዘወትር በትጋት ያገለግላሉ፡፡
ይቆየን……
.....
(ይህ ጽሑፍ በእኔ የመረዳት ደረጃ ብቻ የተጻፈ ነው፡፡ ለእርማት ዝግጁ ነኝ)
……………….

በሃይማተኞች ሀገር ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች ባይዘነጉ …




(መላኩ አላምረው)
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን እየሠራ ያለ አንድ በጣም የምወደው ጓደና አለኝ፡፡ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀን በሥራ ዓለምም ለ4 ዓመታት ያህል በአንድ ግቢ ነው ተከራይተን የኖርነው፡፡ ብዙ ጊዜ… ስለብዙ ነገሮች እንወያያለን፡፡ ስለ ሀገር ፣ ሃይማኖት ፣ ፍቅር ፣ ትዳር ፣ ጓደኝነት ፣ ትምህርት ፣ … ብቻ የማናነሳው ነገር የለም፡፡ በተለይ ወቅታዊ ጉዳዮችን አናልፋቸውም… እንዲያውም ብዙ ጊዜ የውይይት አጀንዳዎቻችን እነርሱው ናቸው፡፡ የችግሮችን መንስኤ በአቅማችን ለመተንተን እንሞክራለን… እንከራከራለን… ከዛም መፍትሔ ያልነውን (ለራሳችን) እናስቀምጣለን፡፡ ነገር ግን እኛ መፍትሔ የምንለው… ያው ለአዕምሯችን እረፍት ይሆን ዘንድ እንጅ… ከእኛ ወጥቶ አያውቅም፡፡ በተለይ በሀገራዊ መፍትሔ ሰጭ አካላት ዘንድ እንኳን መፍትሔዎቻችን የእኛ መኖርም አይታወቅም፡፡
[ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር… ሁሉም በየቤቱ (በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ) ይወያያል… ይከራከራል… የየራሱን መፍትሔም ያስቀምጣል፡፡ ሕዝቡን በነፃነት የሚወያይበትና አማራጭ ሀሳቡን የሚያካፍልበት ሥርዓት ቢዘረጋለት… ‹ትክክለኛ› መፍትሔ የሌለው ነገር ይኖር ይሆን? አሁን ለተለያዩ ነገሮች መፍትሔ ናቸው የሚባሉትስ እውነት ለመፍትሔነት የመጨረሻ አማራጭ ይሆኑ ይሆን? እውነት ለመናገር በሕዝብ ውስጥ ላሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ በዚሁ ሕዝብ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሕዝብ መፍትሔ ደግሞ….. በቃ መፍትሔ! ነው፡፡ ሕዝቡ ተወያይቶ ፣ ተከራርክሮና ተስማምቶ ያደረገው ምንም ነገር ቢሆን መፍትሔው ያ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ ከልቡ አመንጭቶ በአንደበቱ ያላጸደቀው መፍትሔ… ትክክለኛ ቢሆንም እንኳን የመፈጸሙ ነገር እምብዛም የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ‹ሕዝቡ ይናገር ! ሕዝቡ ካልተናገረና ሲናገርም ካልተደመጠ እርሱም ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጠውና አዳምጦም በተግባር የሚያውልለት የመፍትሔ አካል አይኖርም፡፡›]
እናም ይህ ጓደኛዬ… ትላንት ምሽት ላይ ለተለመደው ውይይታችን እንደተገናኘን ያነሳው የመወያያ አጀንዳ… ‹‹ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችና የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ›› የሚል ነበር፡፡ ርዕሱ ብዙ አላከራከረንም፡፡ ባጭሩ ‹‹ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት ፤ ስለዚህ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ችግር ሲከሰት (ከፖለቲካዊ መፍትሔዎች ጎን ለጎን ወይም በራሳቸው ጊዜና ቦታ) ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችም መሰጠት አለባቸው፡፡ ለዚህም የሃይማኖት/የእምነት ተቋማት የቤት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ውይይታችንን በጊዜ ቋጨነው፡፡
ለሁላችንም አዲስ ባይሆንም… በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ ከተከሰቱት ድርቆች ሁሉ የከፋ የተባለው ድርቅ ተከስቷል፡፡ ከ10 ሚሊዮን ሕዝብ በላይም ለእርዳታ እጁን ዘርግቷል፡፡ መንግሥትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች እየሠሩበት ቢሆንም… የሃይማኖት ተቋማት ግን ‹ሃይማኖታዊ መፍትሔ› ሲወስዶ አላየንም፡፡ እርግጥ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ አሉ፡፡ ለተራበ ሰው መጀመሪያ መደረግ ያለበት ድጋፍ የገነንዘብ መሆኑንም እረዳለሁ፡፡ ይህ ግን ለሃይማኖታዊ ተቋማት በቂ መፍትሔ አይደለም፡፡ ገንዘብ ያላቸው እሺ ይርዱ… የሌላቸውስ? እንደ ሃይማኖት ተቋም (ከገንዘቡ ባሻገር) መወሰድ ያለባቸው መፍትሔዎች የጾም ፣ የጸሎት (ምኅላ) እና ተያያዥ መንፈሳዊ ክዋኔዎችም መሆን አለባቸው፡፡ እስካሁን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ተብሎ በየትኛውም የሃይማት ተቋም የታወጀ ጾምና ጸሎት አልሰማሁም፡፡ (ካለ ይቅርታ… የመረጃ ክፍተት ነው)፡፡
በተለይ በእንደዚህ ዓይነቱ ችግር ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች በአዋጅ ሲተገበሩ ካልታዬ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገርነት ለመቼ ነው? ገንዘብማ ማንም ዓለማዊ ተቋም ሊረዳ ይችላል፡፡ ሃይማኖት ግን ከገንዘብ ባሻገር የሚረዳው ምሥጢራዊ መፍትሔ አለ፡፡ የሰማይን በር የሚያንኳኳ መፍትሔ… ጾም ፣ ጸሎት ፣ (ምኅላ)….፡፡
በድርቁ ብቻ ሳይሆን… በተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች (ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ጉዳይ) ላይ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ… ‹ዝምምም›… ነው እንዴ መሆን ያለበት? ይህችን የሃይማኖት ሀገር በፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ማስተዳደር ሊቻል ቢችልም… ለእኔ ትክክል አይደለም፡፡ ምዕመኑ (ከመሪ እስከ ተመሪው) በየሃይማኖቱ… የሚመከረው መመከር ፣ የሚገሠጸው መገሠጽ ፣ የሚወገዘውም መወገዝ አለበት ባይ ነኝ፡፡ በሃይማኖተኞች ሀገር ያለ ሃይማኖታዊ መፍትሔ ችግሮችን መጋፈጥ….??? አይከብድም? የሃይማኖትም የሆነ የተቋማቱ የመኖር ትርጉም በተግባር ካልታየስ ለምን ይኖራሉ?
….

Sunday, November 1, 2015

ስግደቴ ...


...
በቤትህ ላስቀድስ ስገኝ...
"ስግዱ" ይላል ዲያቆኑ - ራሱም እየተንበረከከ
"ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ ወንሰብሐከ"
ይመልሳል ምዕመኑ - በተግባር እየገለጠ
መሬታዊ ጉልበቱን - ለፈጣሪው እየሰጠ...
...
የእኔ ልብ ግን ጠማማው - ፖለቲካዋን ጨማምሮ
ብሶቱን ለአምላኩ ይጮሃል - በስንኝ ነገር ቋጥሮ
...
<<አምላክ እንኳንስ ላንተ - በፍቅርህ ለምትገዛ
በባለጊዜ ወጠምሻ - ጉልበቴ በጽኑ ተይዛ
መንበርከክን ለምዳለች - መስገድ አይደለም ብርቋ
ባይሆን ለኋላ ርስቷ - ለሰማያዊ ጽድቋ
የአምልኮ ስግደቴን ተቀበል - ከመሬታዊው ለይና
ሥጋዬን ቢገዟትም - ነፍሴ በተስፋ ትጽና!>>
...
(መላኩ - መስከረም 30/2008)

Thursday, August 20, 2015

ጤና... ምግብ...




<<የጤናን ሀብትነት የውኃን ምግብነት አለማወቅ ካለማወቅ ሁሉ ይከፋል፡፡>>
(ብፁዕ አቡነ ቶማስ - ነፍስ ይማር)

Monday, April 27, 2015

እንግድነቱን ያልተረዳ ሕዝብና ጉዞው….


(መላኩ አላምረው)
...
የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሰው በዚህች ዓለም ላይ ሲኖር በፍጹም የተረጋጋ ሰላም/ሕይወት ውስጥ ይኖር ዘንድ እንዳልተፈጠረ ነው፡፡ ምን አልባትም ይህች ዓለም ለሰዎች ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ መኖሪያ ስላይደለች ይሆናል፡፡ አዎ! ሰው በእንግድነት በሚኖርበት ዓለም ሁሉም ይሟላልኝ የማለት መብት የለውም፡፡ እስኪ አስቡት…. እንግዳ ሆናችሁ ከሄዳችሁበት ቤት የፈላግችሁትን ሁሉ የማዘዝ መብት/ሞራል አላችሁ? አይመስለኝም:: የሰጧችሁን በልታችሁ ባገኛችሁት ተኝታችሁ ትመለሳላችሁ እንጂ እንደ ቤታችሁ “ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ”… የፈለግሁት ይምጣልኝ ያልፈለግሁት ይሂድልኝ አትሉም፡፡
ሰፋ አድርገን ብናየው በዚህች ዓለም ያለው ኑሯችንም ይሄው ነው፡፡ ማን የፈለገውን ሁሉ አሟላ? (ፍላጎት ገደብ ባይኖረውም ቅሉ)፡፡ ነጻነታችንን በሙሉ የምጠቀምባት ምድር/ሀገር አለች? ፍጹም የሆነ ሰላም የሰፈነባት፣ ክፉ ነገር የሌለባት ብቻ ሳትሆን የማይወራባት፣ ምንም መከልከል የሌለባት፣ ሁሉም እኩል ተናግሮ፣ እኩል ሠርቶ፣ እኩል አግኝቶ… የሚኖርባት ሀገር አለች? የትም!!!! ሁሉም እንግዳ ስለሆነ ተሸማቆ፣ ተሳቆ፣ ተጨንቆ ነው የሚኖረው፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ፍርሃት አለበት፤ ሁሉም ችግር አለበት፤ ሁሉም ህመም አለበት፤ ሁሉም ክልከላ አለበት፤ ሁሉም ስለነገ እርግጠኛ አይደለም፤ …. እንግዳ ነዋ፡፡ የሚኖረው በራሱ ሀገር አይደለማ፡፡
እስኪ አሁን በዚህ ሰዓት በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን አስቡት፡፡ ስደት፣ ጦርነት፣ ረኃብ፣ ሱናሜ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ አመጽ፣ ሽብር፣ ግጭት፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ሙስና/ስርቆት፣ … የማያስጨንቃት ሀገር አለች? መጠኑ ቢለያይም በዚህ የማይሳቀቁ ሕዝቦች አሉ? ዛሬ ባይሳቀቁ ነገ ይጨነቃሉ፡፡ ዛሬ የሚስቁ ነገ ያለቅሳሉ፡፡ ዛሬ በሰላም የሚኖሩ ነገ ይረበሻሉ፡፡ ዛሬ የሚገሉ ነገ ሲሞቱ ይታያሉ፡፡ ዓለም እና ‘ገዥዋ’ እየተመካከሩ የፈለጉትን ሁሉ ያፈራርቃሉ፡፡ በቃ ሁሉም የእንግድነት ዓለሙ ላይ ስለሚኖር የማይሸከመው ሸክም የለም፡፡ ሁሉም ሲደርስበት ይቀበላል፡፡ እምቢ ቢልም ከመፍጨርጨር ያለፈ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ ምን አልባት ከአንዱ ችግር ወደ ሌላው ስቃይ ይሄዳል እንጂ ዓለምን ከችግር ሊያጸዳት አይችም፡፡ የእርሱ አይደለችማ፡፡ በሰው ዓለም ላይ መወሰን ብሎ ነገር የለም፡፡
ለዓለም ሰላምን እናመጣለን የሚሉትን ሀገራትም አየናቸው፡፡ የባሰ ጦርነትና ሰቆቃ እንጂ መፍትሄ ሲያመጡ አልታዩም፡፡ በአሜሪካ የሚመሩት ምዕራባውያኑ አምባገነኖችን አስወገድንላቸው ያሏቸው ሀገራት ዛሬ የአሸባሪ (የሰወ-በላ) ድርጅቶች መፈልፈያና መፈንጫ ሆነው ችግሩንና ሰቆቃውን እያባዙት ይገኛሉ፡፡ ኢራቅንና ሊቢያን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ ዓለም ባልገባው/በማያውቀው ጉዳይ ነው ገብቶ የሚዳክረው፡፡ የሰው ልጅ ማንነቱን/ምንነቱን እስከሚረዳና ወደ ሕሌናው እስኪመለስም ሁሉም ችግሮች እየተባዙ ይቀጥላሉ፡፡ በሰዎች ስሌት የሚመጣ መፍትሄ የለም፡፡ የራሳቸው ባልሆነ ዓለም ላይ ለምን እንደመጡ እንኳን በውል ሳይረዱ ማን የመፍትሄ አካል አደረጋቸው? ስህተቱ በእንግድነት ባረፉበት ዓለም ላይ የመቆጣጠር ምኞትንና ሙከራን ያውም በጉልበት ማምጣቱ ላይ ነው፡፡ በቃ እንደ እንግድነታችን ዓለም የምትሰጠንን ተቀብለን አመስግነን መሄድ እንጂ…. ሌላ ምኞት ስናመጣ ሌላ ጣጣ እያመጣን ነው፡፡
እንግድነቱን ያልተረዳ የዓለም ሕዝብ ዓለምን የሰቆቃ መናኸሪያ እያደረጋት ነው፤ እንዳደረጋትም ይቀጥላል፡፡ እንግዳ በሰው ቤት ላዝዝ ሲል የሚፈጠረው ጠብ ብቻ ነው፡፡ የሰውን ቤት ለእኔ ይገባኛል የሚልም ሰው ኑሮው ሰላም-አልባ ይሆናል፡፡ ባለቤቱን አስወግዶ/ገድሎ ቢኖርበት እንኳን እርሱ ያልሰራውን ቤት መውጫና መግቢያ፣ የቤተሰቡን ባሕርይ፣ የጎረቤቱን ጸባይ… ጠንቅቆ ሊያውቅ አይችልም፡፡ ራሱ አልሰራውምና ፍጹም ነጻነትን አይሰጠውም፡፡ ሁሌም በመጨነቅና በመሳቀቅ ውስጥ ይኖራል፡፡ እንግዶች ሚያምርባቸው ባለቤቱ እንደወደደና እንደፈቀደ ብቻ ተስተናግደው ሲሄዱ ነው፡፡
የሰው ልጅ ለምን ወደ ዓለም መጣ? ሊገዳደል? አንዱ አንዱን ሊገዛ? ዓለምን ሊወርስ?.... ሁሉም የሰው ልጆች ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ እስከሚኖረራቸውና በተግባርም እስከሚተረጉሟቸው ድረስ ዓለም በእብደቷ ትቀጥላለች፡፡ የሰው ልጆችም ለመጡበት ዓላማ ሳይኖሩ እንዲሁ እንደባዘኑ፣ እንደተሰደዱ፣ እንደተቀዋወሙ፣ እንደተሰዳደቡ፣ እንድተገዳደሉ ያልፋሉ፡፡
ስደት መፍትሄ የሚሆነው ይመስል ሰው ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ይሄዳል፡፡ ግን በዚያም የተሻለ ነገር አያገኝም፡፡ ምን አልባት ችግሮቹ መልካቸውን ቀይረው ይጠብቁታል፡፡ ተረቦ የተሰደደው እንጀራ ያገኝና ነጻነቱን ምን አልባትም ሕይወቱን ያጣል፡፡ ከምግብ ሲጠግብ ከፍቅር ይራባል፡፡ ፖለቲካ አስመርሮት የሄደው ከጠላቸው/ከጠሉት ፖለቲከኞች በመራቁ ሰላም ያገኘሁ ሲመስለው ሌላ የመረረ ዘረኝነት ይጠብቀዋል፡፡ ከዚህ በአመለካከቱ ከጠሉት/ከተጸየፋቸው ሲርቅ በቆዳ ቀለሙ የሚጠሉት ይጠብቁታል፡፡ በቃ ይሄው ነው የዓለም እውነት፡፡
ሁሉም ዓለም ላይ ያሉት መኖሪያዎች የእንግድነት ቤት ስለሆኑ አንዱ ሲሞላ ሌላው ይጎድላቸዋል፡፡ እናም ምንም ይሁን ምን ባላወቅነው እና ባልመረጥነው መንገድ ተፈጥረን ወደዚህች ዓለም በመጣንባት ቀዬ በዚህችው መኖር ሳይሻል አይቀርም፡፡

·         ሚያዝያ 19/2007 ዓ.ም - አዲስ አበባ