(መላኩ አላምረው)
…
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን እየሠራ ያለ አንድ በጣም የምወደው ጓደና አለኝ፡፡ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀን በሥራ
ዓለምም ለ4 ዓመታት ያህል በአንድ ግቢ ነው ተከራይተን የኖርነው፡፡ ብዙ ጊዜ… ስለብዙ ነገሮች እንወያያለን፡፡ ስለ ሀገር ፣ ሃይማኖት
፣ ፍቅር ፣ ትዳር ፣ ጓደኝነት ፣ ትምህርት ፣ … ብቻ የማናነሳው ነገር የለም፡፡ በተለይ ወቅታዊ ጉዳዮችን አናልፋቸውም… እንዲያውም
ብዙ ጊዜ የውይይት አጀንዳዎቻችን እነርሱው ናቸው፡፡ የችግሮችን መንስኤ በአቅማችን ለመተንተን እንሞክራለን… እንከራከራለን… ከዛም
መፍትሔ ያልነውን (ለራሳችን) እናስቀምጣለን፡፡ ነገር ግን እኛ መፍትሔ የምንለው… ያው ለአዕምሯችን እረፍት ይሆን ዘንድ እንጅ…
ከእኛ ወጥቶ አያውቅም፡፡ በተለይ በሀገራዊ መፍትሔ ሰጭ አካላት ዘንድ እንኳን መፍትሔዎቻችን የእኛ መኖርም አይታወቅም፡፡
[ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ ነገር
ቢኖር… ሁሉም በየቤቱ (በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ) ይወያያል… ይከራከራል… የየራሱን መፍትሔም ያስቀምጣል፡፡ ሕዝቡን በነፃነት
የሚወያይበትና አማራጭ ሀሳቡን የሚያካፍልበት ሥርዓት ቢዘረጋለት… ‹ትክክለኛ› መፍትሔ የሌለው ነገር ይኖር ይሆን? አሁን ለተለያዩ
ነገሮች መፍትሔ ናቸው የሚባሉትስ እውነት ለመፍትሔነት የመጨረሻ አማራጭ ይሆኑ ይሆን? እውነት ለመናገር በሕዝብ ውስጥ ላሉ ችግሮች
ሁሉ መፍትሔ በዚሁ ሕዝብ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሕዝብ መፍትሔ ደግሞ….. በቃ መፍትሔ! ነው፡፡ ሕዝቡ ተወያይቶ ፣ ተከራርክሮና
ተስማምቶ ያደረገው ምንም ነገር ቢሆን መፍትሔው ያ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ ከልቡ አመንጭቶ በአንደበቱ ያላጸደቀው መፍትሔ… ትክክለኛ
ቢሆንም እንኳን የመፈጸሙ ነገር እምብዛም የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ‹ሕዝቡ ይናገር ! ሕዝቡ ካልተናገረና ሲናገርም ካልተደመጠ እርሱም
ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጠውና አዳምጦም በተግባር የሚያውልለት የመፍትሔ አካል አይኖርም፡፡›]
እናም ይህ ጓደኛዬ… ትላንት
ምሽት ላይ ለተለመደው ውይይታችን እንደተገናኘን ያነሳው የመወያያ አጀንዳ… ‹‹ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችና የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ››
የሚል ነበር፡፡ ርዕሱ ብዙ አላከራከረንም፡፡ ባጭሩ ‹‹ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት ፤ ስለዚህ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ችግር ሲከሰት
(ከፖለቲካዊ መፍትሔዎች ጎን ለጎን ወይም በራሳቸው ጊዜና ቦታ) ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችም መሰጠት አለባቸው፡፡ ለዚህም የሃይማኖት/የእምነት
ተቋማት የቤት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ውይይታችንን በጊዜ ቋጨነው፡፡
ለሁላችንም አዲስ ባይሆንም…
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ ከተከሰቱት ድርቆች ሁሉ የከፋ የተባለው ድርቅ ተከስቷል፡፡ ከ10 ሚሊዮን ሕዝብ በላይም
ለእርዳታ እጁን ዘርግቷል፡፡ መንግሥትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች እየሠሩበት ቢሆንም… የሃይማኖት ተቋማት ግን ‹ሃይማኖታዊ መፍትሔ›
ሲወስዶ አላየንም፡፡ እርግጥ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ አሉ፡፡ ለተራበ ሰው መጀመሪያ መደረግ ያለበት ድጋፍ የገነንዘብ መሆኑንም እረዳለሁ፡፡
ይህ ግን ለሃይማኖታዊ ተቋማት በቂ መፍትሔ አይደለም፡፡ ገንዘብ ያላቸው እሺ ይርዱ… የሌላቸውስ? እንደ ሃይማኖት ተቋም (ከገንዘቡ
ባሻገር) መወሰድ ያለባቸው መፍትሔዎች የጾም ፣ የጸሎት (ምኅላ) እና ተያያዥ መንፈሳዊ ክዋኔዎችም መሆን አለባቸው፡፡ እስካሁን
በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ተብሎ በየትኛውም የሃይማት ተቋም የታወጀ ጾምና ጸሎት አልሰማሁም፡፡ (ካለ ይቅርታ… የመረጃ ክፍተት
ነው)፡፡
በተለይ በእንደዚህ ዓይነቱ ችግር
ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች በአዋጅ ሲተገበሩ ካልታዬ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገርነት ለመቼ ነው? ገንዘብማ ማንም ዓለማዊ ተቋም ሊረዳ
ይችላል፡፡ ሃይማኖት ግን ከገንዘብ ባሻገር የሚረዳው ምሥጢራዊ መፍትሔ አለ፡፡ የሰማይን በር የሚያንኳኳ መፍትሔ… ጾም ፣ ጸሎት
፣ (ምኅላ)….፡፡
በድርቁ ብቻ ሳይሆን… በተለያዩ
ወቅታዊ ችግሮች (ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ጉዳይ) ላይ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ… ‹ዝምምም›… ነው እንዴ መሆን ያለበት? ይህችን
የሃይማኖት ሀገር በፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ማስተዳደር ሊቻል ቢችልም… ለእኔ ትክክል አይደለም፡፡ ምዕመኑ (ከመሪ እስከ ተመሪው)
በየሃይማኖቱ… የሚመከረው መመከር ፣ የሚገሠጸው መገሠጽ ፣ የሚወገዘውም መወገዝ አለበት ባይ ነኝ፡፡ በሃይማኖተኞች ሀገር ያለ ሃይማኖታዊ
መፍትሔ ችግሮችን መጋፈጥ….??? አይከብድም? የሃይማኖትም የሆነ የተቋማቱ የመኖር ትርጉም በተግባር ካልታየስ ለምን ይኖራሉ?
….
No comments:
Post a Comment