(መላኩ አላምረው)
…
እኔ እስካሁን ባለኝ ግንዛቤ መላእክት እንዳሉ የማያምን ሃይማኖት/የእምነት ተቋም በእኛ ሀገር እንዳለ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለምእመናን ባላቸው ድርሻ አንዱ ከሌላው የተለዬ አስተምህሮና እምነት ቢኖራቸውም በመላእክት መኖር ግን ያምናሉ፡፡ ኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት… ሁሉም የመላእክትን መኖር ይቀበላሉ፡፡ መላእክት ለሰው ልጆች በሚሰጡት አገልግሎት ግን አንዱ ከሌላው ይለያያሉ፡፡ የተወሰኑት መላእክት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚላላኩ መናፍስት ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሰው ከኃጢአቱ ይድን ዘንድ በአማላጅነት ይራዳሉ፣ ለጽድቅ ሥራ ሰውን ያግዛሉ፣ በነገረ ድኅነት ውስጥ ድርሻ አላቸው… ብለው ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ መኖራቸውን ተቀብለው አማላጅነታቸውን (ለድኅነት ያላቸውን ድርሻ) በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የመላእክትን አማላጅነት/አለማማለድ ወይም ሌላ የአገልግሎት ድርሻ ለመስበክ አይደለም፡፡ ‹‹የሰው ልጆች ብቻችንን እንዳልሆንና በመላእክት እንደምንጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?›› የሚለውን ለማሳየት እንጅ፡፡ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ መጽሐፍ ነው ብሎ የሚቀበል ሰው ይህንን እውነት ያውቅ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመላእክት መኖር የሚያምን ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ሰውም ቢሆን ይህንን ጽሑፍ ቢያነበው ስለ መላእክት ያለውን እውቀት ያሰፋለታል እንጅ አይጎዳውም፡፡
ወደ ጥቅስ ከመሄዳችን በፊት እንዲሁ በአመክንዮ (Logical Reasoning) ለማየት እንሞክር፡፡ መላእክት አሉ ብለን ካመንና መኖራቸውም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው ካልን… ‹‹የእነርሱ መኖር ለእኛ አስፈላጊነቱ ምንድነው? እነርሱ ባይኖሩ ምን ይቀርብናል? ወዘተ…›› የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ አለብን፡፡ የመላእክት መኖር ለሰው ልጅ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም ብለን ካመንን ደግሞ ‹‹ለሰው የማያስፈልግ ነገር ግን ከሰው ጋር ወይም በሰውና በፈጣሪ መሐል የሚኖር ፍጥረት ሊኖር ይችላልን?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለብን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ግን መለስ የሚኖረን አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ ለእኛ የማያስፈልግ ምንም ነገር በዙሪያችን ሊያኖር አይችልም፡፡ እኛ ጥቅማቸውን አላወቅንም ማለት አይጠቅሙንም ማለት አይደለም፡፡
ፈጣሪ አምላክ የማይታይ መንፈስ ነው ካልን በቅርበት ሊያገለግሉት የሚችሉት መናፍስት ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ለመንፈስ ባሕርይ ከሥጋ ለባሽ ፍጥረታት ይልቅ መናፍስት ይቀርባሉና፡፡ ለዚህም ነው ሰው ሥጋ እንደለበሰ ወደ ሰማይ (ወደ መናፍስት ዓለም) መሄድ የማይችለው፡፡ ነገር ግን በሥጋ ከሞተ በመንፈሳዊ ባሕርይው (በነፍሱ) እስከተገባው ቦታ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይቀርባል ብለን እናምናለን፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ሥጋው ተለውጦና እንደ መናፍስት የማይሞት ባሕርይን ይዞ ነው የሚነሳው (በትንሣኤ ሙታን)፡፡
መንፈስ ለሆነው አምላክ መናፍስት የሆኑ አገልጋዮች አሉት/ሊኖሩት ይገባል በሚለው ከተስማማን ደግሞ አገልግሎታቸው በፈጣሪና በፍጡራን መሐከል ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ (በቀላል ምሳሌ ለመመሰል… የአንድ ሀገረ ገዥ የቅርብ አገልጋዮች/ሹማምንት ማለት የሚገዛውን ሕዝብ ከእርሱ ጋር የሚያገናኙ፣ መልእክትን ከእርሱ ወደ ሕዝቡ፣ ከሕዝቡም ወደ እርሱ የሚደርሱ ናቸውና - ይህ ካልሆነም የቅርብ አገልጋይ አስፈላጊነቱ ምንም ነውና)፡፡
መላእክት ለፈጣሪ ከሰው ልጆች ይልቅ ቅርብ የሆኑ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ፍጡሩን ሁሉ ሲገዛ በየደረጃው ለፍጡራኑም የገዥነት ሥልጣንን በጸጋ ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ አዳም ለምድር ፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፡፡ መላእክትም በየደረጃቸው ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ የፍጡራን ሥልጣን ግን ከፈጣሪ ዘንድ በጸጋ የሚገኝና ከፈጣሪ ፈቃድ ውጭም ሊሆን የማይችል መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ፈጣሪ የዓለም ሁሉ ገዥ ነው፡፡ በየፍጥረቱ (በየወገኑ) የሾማቸው መናፍስት የሆኑ ፍጥረታት ደግሞ ይኖሩታል/አሉት፡፡ እነርሱም መላእክት ናቸው፡፡ ፈጣሪ ዓለምን ሲገዛ በጸጋ ሌሎች ገዥዎችን እንደሚሾም ከአዳም ተፈጥሮ መረዳት ይቻላል፡፡ እርሱን የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማለክት አምላክ የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡ ከሁሉም ግን ለእርሱ በባሕርይ መናፍስት የሆኑ መላእክት ይቀርቡታል፡፡ እነርሱንም ወደ ሌላው ፍጥረት ሁሉ ይልካቸዋል፡፡ ወደ ሰውም ጭምር፡፡ መላእክት ከመላው ፍጥረት ጋር ስላላቸው ግንኙነት በዚህ ጽሑፍ ማንሳት አልፈልግም (ካስፈለገ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)፡፡
የመላእክት ጠባቂነት ለሰው ልጆች እንዴት ?
በመጀመሪያ ደረጃ መላእክት እኛን የሰው ልጆችን ከልጅነት ጀምሮ በመንከባከብ ይጠብቁናል፡፡ ለዚህ ማስረጃነት ከመጽሐፍ ቅዱስ 2 ጥቅሶች ብቻ እንመልከት፡፡ ከብሉይ ኪዳን ለመጀመር ከደጋግ አባቶች አንዱ የሆነው ያዕቆብ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ የመገበኝ እግዚአብሔር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ የጠበቀኝ/ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች/ሕጻናት ይባርክ›› በማለት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እንዳዳነውና እንደጠበቀው ያስረዳል …ዘፍ 48፥16፡፡ ይህም መልአክ ልጆቹንም ይባርክለት/ያከብርለት ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ቃል በትንቢተ ዳንኤል ላይ… ዳንኤልን መልአኩ እንዴት ይጠብቀው እንደነበር… በኋላም ሠልስቱ ደቂቅን (ሦስቱን ሕጻናት) የእግዚአብሔር መልአክ ከእቶን እሳት እንዴት ጠብቆ እንዳዳናቸው ተጽፏል፡፡
አይ… ይሄ የሐዲስ ኪዳንን አምልኮ አይወክልም ካልን ደግሞ የሚከተለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል እንመለከት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.18፡ቁ.10 ላይ… ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ ‹‹አንዱን›› እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ ‹‹መላእክቶቻቸው›› ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።›› ይላል፡፡ ይህ ቃል ሁሉም ሰው መላእክት እንዳሉት ያሳያል፡፡ እነዚህ መላእክት ሊጠብቋቸው ካልሆነ ለምን ከታናሾች ጋር ይኖራሉ? ልብ ብለን እንመልከት… ‹መላእክቶቻቸቸው› ‹ዘወትር› የፈጣሪን ፊት ያያሉ… ማለት ስለሚጠብቋቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ይጠየቃሉ፣ ይናገራሉም፡፡ ‹ፊቱን ያያሉ› ማለት ለአገልሎት/ለመልእክት መቅረብን እንጅ ፈጣሪን እንደ ሰው ገጹን ማየትን አያመለከትም፡፡ ይህ ለፍጡራን አይቻልምና፡፡
ከዚህ ላይ ሌላ ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ… ማንንም ሰው ታናሽ ነው… አቅመ ቢስ ደካማ ነው… ብሎ መናቅና በእርሱም ላይ በደል ማድረስ በሰው ፊት ባይሆን እንኳን በፈጣሪ ፊት እንደሚያስከስስ ነው፡፡ ሰው ብቻውን አይደለም፡፡ ዘወትር ስለበደላቸው ለፈጣሪ የሚናገሩ መላእክት አሉና፡፡ ለዚህም ነው ምዕመናን የመላእክትን ጥበቃ ተስፋ የሚደርጉት፡፡
እስኪ ማጠቃለያ ጥያቄ እናንሳ… ለመሆኑ አንድ መልአክ በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላልን ? ለምሳሌ የገብርኤል በዓል ዕለት በሁሉም ቦታ ሕዝቡ ወጥቶ የሚያነግሰው በሁሉም ቦታ ካልተገኘ ለምን? ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የመላእክትን ተፈጥሮ ነው፡፡ መልአክ በባሕርይ ተፈጥሮው መንፈስ ነውና ይችላል፡፡ በሥጋ ስሌት ካላሰብነው በቀር ይህ ለመናፍስት የተሰጠ ጸጋ ነውና በአንዴ በብዙ ቦታ መገኘት ይችላል፡፡ በመዝ. 33፥7 ላይ የተጻፈውን ልብ እንበል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ‹መልአክ› ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹ዙሪያ› ‹ይሠፍራል›፣ ‹ያድናቸውማል››› ይላል፡፡ ‹‹መልአክ›› ብሎ አንድ መሆኑን… ‹በሚፈሩት ሰዎች› ‹‹ይሰፍራል›› ሲል ደግሞ ለብዙ ቁጥር የሚሆነውን ቃል ተጠቀመ፡፡ ሰፈረ… ብዙ ቦታ ላይ ተገኘ… እንደማለት ነው፡፡ እንዲያውም በብዙ ሰዎች ‹ዙሪያ› ነው ሚሰፍረው፡፡ አንድ ሰው ቢሆን ኖሮ በሌላው ሰው ‹‹ዙሪያ›› ሳይሆን ወይ በፊት ወይ በጎን ነበር ሚቆመው፡፡ እዚህ ላይ አንዱ መልአክ ግን በዙሪያቸው ሲሰፍር ያሳያል፡፡
በመጨረሻም… ለሰው ልጆች የመላእክት ጥበቃ ያስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት ፈጣሪ በራሱ ፍጡሩን መጠበቅ ስለማይችል ወይም በደላችንን የማያውቅ ሆኖ ሳይሆን ለፍጡራኑ የአገልግሎት ድርሻ ለመስጠት ነው፡፡ በመላእክትም ጠበቀን በራሱም ጠበቀን ዞሮዞሮ ጥበቃው የፈጣሪ ነው፡፡ ፍጡር በየደረጃው እያገለገለ መንግሥቱን ይወርስ ዘንድ የአምላክ ፈቃድ ነውና… በምድርም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ምድርንም እርሱ ፈጥሮ ይገዛት ዘንድ ለሰው ልጅ ሰጠ፡፡ የሰው ልጅም አገልጋይነቱን ከተረዳና በሥርዓት ከኖረ ለሌላ ሰማያዊ መንግሥት ይበቃል፡፡ መላእክትም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአገልግሎታቸው ካልተጉ እንደ ሣጥናኤል ከፈጣሪ ክብር ይርቃሉና ዘወትር በትጋት ያገለግላሉ፡፡
ይቆየን……
.....
(ይህ ጽሑፍ በእኔ የመረዳት ደረጃ ብቻ የተጻፈ ነው፡፡ ለእርማት ዝግጁ ነኝ)
……………….