Tuesday, November 12, 2013

ትዝታ……

ትዝታ……

ልክ እንደ ዓባይ ወንዝ ሲሄዱት ቢኖሩ
እንደ ዋሽንት ዜማ እያንቆረቆሩ
ምንም ቢያጣጥሙት
ምን ቢደጋግሙት
ትዝታ ጥልቅ ነው ከቶ አይደረስም
ትዝታ ኃያል ነው ከቶ አይሸነፍም
የማያልፍ ታሪክ የጥንት ማስታወሻ
የኋልዮሽ መንገድ የትላንት መድረሻ
ትዝታ ሀሳብ ነው የምንተክዝበት
ትዝታ ስንቅ ነው የምንጽናናበት
ትዝታ ቅጣት ነው ምንጸጸትበት
ትዝታ ደስታ ነው የምንቦርቅበት
ትዝታ ሀዘን ነው የምናለቅስበት
ትዝታ ሕግ ነው የምንቀጣበት
ትዝታ አብሮነት ነው ትዝታ ባዶነት
ትዝታ ሀብት ነው ትዝታ ድህነት
ትዝታ እምነት ነው ትዝታ ክህደት
ትዝታ……..








Tuesday, November 5, 2013

“በአዲስ ዓመት- አዲስ ቃል- ለቤተ ክርስቲያን!”


አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር- አዲስ ነገር እናስባለን
       አዲስ ቃልም እንገባለን፣
ይህንን ራእይ ሰንቀን- ይሄኛውን ደግሞ አቅደን
      ያኛውንም እናልማለን፣
ግን ቃል በገባን ቁጥር- ፈፅመነው እናውቃለን?
       በምንስ እንለካዋለን?
የራእያችንን መሳካት- የዕቅዳችንን ግብ መምታት
     እንዴት ነው የምንለካው?
ለተፈጠርንበት ዓላማ- ለመኖር ላለመኖራችን
     መመዘኛችን ምንድነው?
ከተፈጠርን ጀምሮ- በዚህች ምድር እየኖርን
    ብዙ ነገር አሳልፈናል፣
ለርሀባችን መታገስ- ለገላችንም ልብስ መልበስ
    ብዙ ወጥተን ወርደናል፣
ለእዕምሯችንም ምግብ- ሥጋዊ ዕውቀትን ፍለጋ
    ብዙ ዘመናት ደክመናል፡፡
ነገር ግን ምንም እንኳን- ለኑሯችን ስንደክም
    ዘመናችንን ብንጨርስም፣
በዓለም እርካታ የለምና- አሁንም በቃን አላልንም
   ጎደሏችንን አልሞላንም፡፡
ታዲያ ለሥጋዊ ሕይወት ብቻ- እስከመቼ እንደክማልን?
     ከመነንፈሳዊነት ርቀን፣
መቼስ ይሆን የምንኖረው?-በመንፈሳዊ ሕይወት
    ወደ ሰማየ ሰማያት መጥቀን፡፡
መቼስ ይሆን የምንከተለው?-የአባቶቻችንን መንገድ
    አገልግሎታቸውን ማን ያሳየን?
መንፈሳችንን ምን ሰለበው- ከሰማያዊት ጥሪ
    ከቅዱሳን ሕብረት ማን ለየን?

Friday, November 1, 2013

በአገራችን ለሙስና መስፋፋትና ለሥነ ምግባር ብልሹነት ተጠያቂው ማን ነው?

January 18, 2013 at 2:30am
በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ላይ አንድ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም፣ አሳዛኝም ዘገባ አነበብኩ። በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የግል ት/ቤቶች ውስጥ በአንዱ (ምንአልባትም የእኛ ቋንቋዎች በማይነገሩበትና ልጆች እንግሊዝኛ በመናገራቸው ብቻ የእውቀት ጣሪያ ላይ የደረሱ በሚመስሉበት) የተፈፀመ አስነዋሪ ተግባር።
ሰባት ተማሪዎች (3 ወንድና 4 ሴት) የማጠናከሪያ ትምህርትና ጥናት አለን በማለት ያመሻሉ። ከዛም (ከጥበቃዎች ጋር በመስማማት ይመስላል) ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአንድ ክፍል ውስጥ በቦርሳቸው ደብቀው ያስገቡትን ሁለት ጠርሙስ ውስኪ እየጠጡ ጭፈራ ይጀምራሉ። ይጠጣሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይጮሀሉ… ድምፁ እየተሰማ ተው የሚል አልነበረም። እስከ ምሽቱ 7 ሰዓት አስረሽ ምችው ከጨፈሩ በኋላ ድምፃቸው ይጠፋል።
በማግስቱ ጠዋት ተማሪዎች ወደ ክፍል ሲገቡ የታየው ነገር አስደንጋጭ ነበር። ሴቶችም ወንዶችም እርቃናቸውን በወንበሩም በወለሉም ላይ ተረፍርፈዋል። ክፍሉ በትውኪያና ሽንት ተጥለቅልቋል። ሁለት የውስኪና ሦስት የአምቦ ውሃ ጠርሙሶች በየቦታው ወድቀዋል። የምግብ ፍርፋሪም በክፍሉ ይታያል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በላፕቶፓቸው ሲመለከቱት (ምንአልባት ያንኑ ሲለማመዱት) የነበረው አስፀያፊ የ“ኦንላይን” ልቅ የወሲብ ፊልም አልተዘጋም ነበር። አገር ሰላም ያሉት ቀበጦቹ ተማሪዎች ግን እንቅልፍ ላይ ነበሩ።

Tuesday, October 29, 2013

አስተውል!

የእግዜርን ስም ጠርቶ የለመነህን ሰው፣
እንዲሁ አትመልሰው፤
       ቢቻልህ መጽውተው፣
           ከራበው አጉርሰው፣
           ከራዘው አልብሰው፡፡
አደራ ተጠንቀቅ፡-
በአምላከክ ሥራ ገብተህ-
      እርሱን እንዳትወቅሰው፤
በክፉ ፊት ገርፈህ ለማኝ እንዳትለው፣
ክፉም ቃል ተናግረህ እንዳታሳዝነው፡፡
ከቶ አይኖርምና ወዶ የሚለምን፣
ፈጥነህ እንዳትስት አስተውል ዓለምን፡፡
ነገር ሲገላበጥ በፍትህ ጎዳና፣
ሲለ'መኑ ኖሮ መለመ'ን አለና፤
እግዜር ሲፈጥረንም፡-
አንዱን ለመለመን- ሌላውን ለመስጠት
                    ከቶ አይደለምና፡፡
እንዳገኙ መኖር ተደስቶ መሞት፣
እንደተለመኑ በክብር መሸኘት፤
      ትፈልግ ከሆነ የክብርን ገድል፣
      በተለመንህ ጊዜ በጥልቀት አስተውል፡፡

እምነት ያለ ሥራ ብቻውን ያድናልን???

መልካም ሥራ አያስፈልግም፣ ማመን ብቻ ያድናል የምትሉ እስኪ እነዚህን ጥቅሶች አንቡ፡፡ ጽድቅበእምነት ብቻ ቢሆን ኖሮ እነዚህ የእግዚአብሔር ቃላት ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጻፉ??? እውነት ነው የጽድቅ በር የተከፈተልንበጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የጽድቃችን መሰረትም በሩም እርሱ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በማመን ብቻ መዳንእንደሚቻል ተደርጎ ሊወሰድ ኣይገባውም፡፡ መልካም ሥራ ካልሰራን የክርስቶስ መሆናችንስ በምን ይታወቃል፡፡ በማመናችን ብቻ ለእርሱልንሆን አንችልም፡፡ ማመን ብቻው አያድንም፡፡ መታመንን መጨመር አለብን፡፡ መታመን ማለት ደግሞ ላመኑት መገዛት፣ የታዘዙትን መፈጸምማለት ነው፡፡ ይኸውም የሚገለጸው በመልካም ሥራ ነው እንጅ አምናለሁ እያሉ በመናገር ብቻ አይደለም፡፡ ለማነኛውም የሚከተሉትን ጥቅሶችአንብቡና ፍረዱ፡፡ እምነት ብቻውን ቢያድን ኖሮ እነዚህ ለምን ተጻፉ???

የያዕቆብ መልእክት
14 
ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።

125 

ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል።