Tuesday, November 5, 2013

“በአዲስ ዓመት- አዲስ ቃል- ለቤተ ክርስቲያን!”


አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር- አዲስ ነገር እናስባለን
       አዲስ ቃልም እንገባለን፣
ይህንን ራእይ ሰንቀን- ይሄኛውን ደግሞ አቅደን
      ያኛውንም እናልማለን፣
ግን ቃል በገባን ቁጥር- ፈፅመነው እናውቃለን?
       በምንስ እንለካዋለን?
የራእያችንን መሳካት- የዕቅዳችንን ግብ መምታት
     እንዴት ነው የምንለካው?
ለተፈጠርንበት ዓላማ- ለመኖር ላለመኖራችን
     መመዘኛችን ምንድነው?
ከተፈጠርን ጀምሮ- በዚህች ምድር እየኖርን
    ብዙ ነገር አሳልፈናል፣
ለርሀባችን መታገስ- ለገላችንም ልብስ መልበስ
    ብዙ ወጥተን ወርደናል፣
ለእዕምሯችንም ምግብ- ሥጋዊ ዕውቀትን ፍለጋ
    ብዙ ዘመናት ደክመናል፡፡
ነገር ግን ምንም እንኳን- ለኑሯችን ስንደክም
    ዘመናችንን ብንጨርስም፣
በዓለም እርካታ የለምና- አሁንም በቃን አላልንም
   ጎደሏችንን አልሞላንም፡፡
ታዲያ ለሥጋዊ ሕይወት ብቻ- እስከመቼ እንደክማልን?
     ከመነንፈሳዊነት ርቀን፣
መቼስ ይሆን የምንኖረው?-በመንፈሳዊ ሕይወት
    ወደ ሰማየ ሰማያት መጥቀን፡፡
መቼስ ይሆን የምንከተለው?-የአባቶቻችንን መንገድ
    አገልግሎታቸውን ማን ያሳየን?
መንፈሳችንን ምን ሰለበው- ከሰማያዊት ጥሪ
    ከቅዱሳን ሕብረት ማን ለየን?

የመንፈስ ልዕልናችንቀርቶድክመታችንን ተመልክቶ
    ዓለምስ ስለምን ይሳለቅ?
አጋንንት እንዴት ይበርታብን?-በመናፍቃን ማታለል
    አማኝ እስከመቼ ይነጠቅ?
በመንፈስ ባዶ እየሆንን- እስከመቼ አንገት እንድፋ
   እንዴት ዓለማውያንስ ይናቁን?
እስኪ በአባቶች ወኔ- ለጽድቅ በእውነት እንታጠቅ
   ማንንነታችንን ይወቁን፡፡
እስኪ ደግሞ በዚህ ዓመት- ቃላችን በመንፈስ እናድስ
   ቤተ ክርስቲያንን እናስባት፣
ፈተናዋ በዝቷልና- ልጆቿ ዓለማዊ ሆነን
    መንፈሳችንም ዝሎባት፣
አጽራረ ቤተ ክርስቲያን- እንደ አሸን ፈልተዋልና
   የዘመኑ ፍጻሜ ደርሶባት፡፡
እስኪ ሁላችንም ባንድ መንፈስ- ቃላችንን እናድስና
    እናታችንን ደስ ይበላት፣
እኔ ግን ይሄው ለራሴ- ቃሌን እንደዚህ አድሻለሁ
    የድርሻዬን ልወጣላት፡፡
ባለፀጋዋ እናቴ- አንቺ ስንዱ እመቤት ሆይ!
    ሠላም ይሁን ለሁለንተናሽ፣
የፍቅርሽ ስፋት ጥልቀት- ለኔ ያደረግሽው ሁሉ
    ገረመኝ እናትነትሽ፡፡
በዓለም ከወለደችኝ- ከሥጋዊቷ እናቴ
    የአንቺ ፍቅር ይለያል፣
በረቀቀው ምሥጢርሽ- በግብረ መንፈስ ቅዱስ
   ዳግም ልደቴን ሰጥተሽኛል፡፡
በልዩ እንክብካቤሽ- በመላዕክት ጠባቂነት
    በቅዱሳንሽ ጸሎት፣
በያሬዳዊ ዜማሽ- በቅኔ በማኅሌቱ
     በሰማያዊ ሥርዓት፡፡
ትህትናን በተመላ- የካህናት የሊቃውንት
    የመምህራን አስተምህሮ፣
በአ-ቡ-ጊ-ዳ በአንቺው ጥበብ- በገበታ ፊደልሽ
    አንደበቴ ፊደል ቆጥሮ፡፡
በውዳሴ ማርያም ዜማ- በድጓ በጾመ ድጓሽ
    ከመላእክት ጋር ዘምሬ፣
ኪዳኑን አስደርሼ- ቅዳሴውን አስቀድሼ
   በሥጋ ወደሙ ከብሬ፡፡
በብራና ላይ ጽሑፍሽ- በግድግዳ ላይ ሥዕልሽ
     ጥበብሽን አይቻለሁ፣
በፍልፍል አብያትሽ- በረቀቁ ህንፃዎችሽ
    ማንነትሽን አውቄአለሁ፣
ጠበልሽን ጠጥቼ- እምነትሽን ተቀብቼ
    ተአምርሽን አድንቄአለሁ፡፡
የመጻሕፍትሽን ምሥጢር- የገድል የድርሳናቱን
    የቅዱሳንን ማንነት፣
ለአንቺ ህልውና ሲሉ- የተቀበሉትን መከራ
   የከፈሉትን ሰማዕትነት፡፡
የአባቶችን ልዩ ጥበብ- እንዴት ቅርሶችሽን ጠብቀው
   ለእኔ እንዳደረሱልኝ፣
ትውፊትሽን ለማቆየት- አንችን ለእኔ ለማስረከብ
   መስዋዕትነት ሲከፍሉልኝ፡፡
መከራ ስደታቸውን- ርሀብ ጥማታቸውን
    በዓይነ ህሌናዬ አይቻለሁ፣
ፍቅር ፅናታቸው አስደንቆኝ- እነባቸውን አንብቻለሁ
    ርሀባቸውን ተርቤአለሁ፡፡
እናም ይኸው እናታለም- ምንም አንቺን ለመረከብ
    ማንነቴ ባይፈቅድልኝም፣
የእምነት የእውቀት ጉድለቴ- የልቤ አመንዝራነት
    ባዶነቴ ቢያስጨንቀኝም፡፡
ከእኔ የአዕምሮ መርከስ- ከሐጢአት ከጉድፈቴ
     የአንቺ ፍቅር ይበልጣልና፣
ይኸው ተረክቤሻለሁ፡-
የጻድቃን የሰማዕታትን- የቅዱሳን መላእክትን
    ተራዳኢት አምናለሁና፡፡
እናም ከዛሬ ጀምሮ- ይኸው ቃሌን ሰጥቻለሁ
    ተንበርክኬ ከእግርሽ ስር፣
ማንነትሽን ባላሳውቅ- ታሪክሽን ለዓለም ሁሉ
    ያለ ፍርሃት ባልመሰክር፣
ትውፊትሽን ባላስጠበብቅ- የአምልኮና የዜማ
     ሥርዓትሽን ባላስከብር፤
ምሥጢራትሽን አመሥጥሬ- ንዋያትሽን ደርድሬ
     ከፍ ከፍ ባላደርግሽ፣
ልጆችሽም ይበዙ ዘንድ- ለሰማያዊ መንግሥት ጥሪ
    ወንጌልሽን ባልሰብክልሽ፤
ይኸው በዳዊት መሐላ- እየማልሁ ከደጅሽ ልውደቅ፣
“ቤተ ክርስቲያን ሆይ!- ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ
ባላስብሽም ምላሴ- ከጉሮሮዬ ትጣበቅ፡፡”


No comments: