(መላኩ አላምረው)
...
የቅዱሱ አርበኛ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቀድሞ የክብር ቦታው በተመለሰ ማግስት የሚወራው ሁሉ ይዘገንናል። የእርሳቸውን
የጀግንነት ታሪክ እያነሱ ለትውልዱ የሀገር ፍቅርን ወኔ ከማስታጠቅ ይልቅ በእርሳቸው ላይ አንድ አቋምና ተመሳሳይ ክብር ያለውን
ሕዝብ ለመከፋፈል ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ ማየት በእውነት ያሳፍራል፡፡
የዘረኝነት ጥጋችን ሰማይ እንደነካ
ለማሳየት
የአቡነ ጴጥሮስን ነፍስ ከገነት መጣራት ጀምረናል። የዘረኝነት መርዛችን ሥር መስደዱን ለማሳየትም ሥጋቸውን ከመቃብር እየቀሰቀስን ነው። ብንችል አስነስተናቸው አንዱን ብሔር ወግነው ሌላውን ኢትዮጵያዊ
እንዲሰድቡልን ሁሉ እተመመኘን ይመስላል፡፡ ደግነቱ አንችልም፡፡
በእውነት
ታመናል፡፡ በያዙት የሃይማኖት አባትነት (የጵጵስና) ሥልጣን ለአንዲቷ ኢትዮጵያ ነፃነትን አውጀውና ቅኝ መገዛትን ገዝተውት ባርነትንም አውግዘውት ክቡር ነፍሳቸውን ለሀገራቸው አሳልፈው የሰጠትን ሰማእት አርበኛ ብሔርና ዘር መቁጠር ጀምረናል።
ምነው የዚህን ትውልድ የአንድነት መመኪያዎች ባንነካካቸው ? ምናለ እንደአቡነ ጴጥሮስ ዓይነት የአንዲቷ ኢትዮጵያ የነፃነት ምልክቶች በልባችን ታትመው ቢቀመጡልን? ምናለበት በሽታችንን ለሌሎች ከማዛመት ይልቅ
ለመታከም ብንሞክር፡፡ ይሄ እኮ ትልቅ በሽታ ነው፡፡ በጊዜ ካልታከምነው እኛንም የሚከተሉንንም ከሰውነት ተራ ያወጣል፡፡
እንዲያው አዕምሯችንን ተብትቦ የያዘው በሁሉም ነገር ላይ ዘር የመቁጠር ልክፍት በሉ
በሉ ቢለን እንጅ አቡነ ጴጥሮስ የሞቱበትን የጵጵስና ስማቸውን ትቶ የልጅነት ስማቸውን፣ የሞቱላትን ኢትዮጵያን ትቶ የትውልድ ሰፈራቸውን፣ የተናገሩትን የነፃነት ድምጽ ትቶ ቋንቋቸውን መፈለግ ተገቢ ነውን??? በእውነት ይሄ ምን ዓይነት ድንዛዜ ምንስ ይሉት በሽታ ነው???
(፡))› ለእኩይ ዓላማችን መፈፀሚያ የሚሆን ትውልድ መቼ አጣንና ነው የሞቱ ጀግኖቻችንን እየቀሰቀስን በዘር የምናቧድናቸው???
ይኸውና ወጣቱ ፊት ለፊታችን ግራ ተጋብቶ ቆሞልናል። ብንፈልግም ሕፃናትን መርዝ በሚተፋ ምላሳችን ንጹህ ጭንቅላታቸውን እየነደፍን የዘረኝነት ክትባቱን እንከትባቸው፡፡ በማይራራ አንጀታችንም በለጋ ሰውነታቸው እናሰራጭባቸው። በሕይወታቸው ለአንዲት ኢትዮጵያ ነፃነት ሲደክሙ ኖረው በሞተ ሥጋ ያረፉትን ጀግኖቻችንን ግን እንተዋቸው። እስኪ እነርሱ እንኳን ይረፉ። ለቆሻሻ ምኞቶቻችንና ለእኩይ ተግባራችን የእነርሱን ስም መጥራት ተገቢ ያልሆነ ከነውርም ነውር ነውና አንነካካቸው፡፡
እኛ በቁማችን ሞተን የምናስበውን የወረደ ነገር እነርሱ በሥጋ ሞት ካረፉበት ያስቡልን ዘንድ ከንቱ ቅዠትን አንቃዥ፡፡
እስኪ ሐቁን እንቀበል፡፡ አቡነ ጴጥሮስ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጳጳስና ጀግና ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው። ጀግንነታቸውን እንጅ ኦርቶዶክስነታቸውን፣ ብሔራቸውን
እንጅ ኢትዮጵያዊታቸውን ለመስማት ያመኛል የሚል ካለ መፈወስ ያለበት በሽታ ከሆነው አመለካከቱ ነው። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይና የማንኛውም ብሔረሰብ ተወላጅ ለአንዲት
ኢትዮጵያ ሕይወቱን እስከሰጠ ድረስ በሁሉም ኢትዮጵዊ ዘንድ ጀግና ነው፡፡ ሕይወቱን የሰጠላትን ሀገር ዜግነት ልንቀማው ቀርቶ ስሟን
በክፉ ልንጠራበት አይገባም፡፡ ለሀገሩ የሕይወቱን ዋጋ ከፍሎባታልና፡፡ ቅዱሱ አርበኛ አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ነጻነት
ሲሉ የሰጡት ምትክ የሌላት ነፍሳቸውን ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ቢያደርጉ ይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ሊያከብራቸው የሚችለው፡፡
‹‹የንጹህ ኢትዮጵያዊነት፣ የጀግና አርበኝነት፣ የሀገርና ሕዝብ ወዳድነት ልኩ እርሳቸው አይደሉምን›› ???
ኧረ
እንፈር፡፡ ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር አሉ፡፡ ትውልዱ የሚያፍርብን ማፈሪያች ሆነን ሳለ ምነው አሳፋሪ ሀሳቦቻችንን ይዘን አደባባይ
ለመቆም መድከማችን???
…..ጭራሽ ጽንሰ ሀሳቡን በወጉ ባልተረዳነው የሃይማኖትና
የመንግሥት መለያያየት (Secularism?) ሰበብ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለምን በሃይማኖታዊ ዝማሬ ታጀበ ብሎ አቧራ ማስነሳት
ምን ይሉታል ? አንዳንዶቻንም ‹‹መንግሥት መፍቀድ አልነበረበትም ፤ ምክንያቱም የሌላ እምነት ተከታዮች (ለምሳሌ ሙስሊሞች) ይከፋቸዋል…››
ምናምን… ቅብጥሴ… እያልን ነው፡፡ ቆይ ግን እንዲህ ለሙስሊሙ መብት ተሟጋች መስለን ሌላ መርዝ የምንዘራ ሁሉ… እንኳን ለጋራ ሀገራችን ለኢትዮጵያ ነጳነት ለሞተ አርበኛ ቀርቶ
፣ ለፍቅር ሲል ኦርቶዶክሱን ብቻ ለሚመለከተው ለጥምቀት የሚወጣን ታቦት የሚያጅብ ሙስሊም ባለባት ሀገር ላይ
እንደምትኖሩ አታቁምን??? በዚህ ቅር የሚለው አንድም
‹‹ኢትዮጵያዊ ሙስሊም›› እንደሌለ እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ቅር ያላችሁ እናንተው ናችሁ፡፡ ቅሬታችሁንም ይኸው በአደባባይ ሳታፍሩ ገለጻችሁ፡፡
ለምን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሲመለስ በሃይማታዊ ሥርዓት ታጀበ ብሎ ቅሬታውን የገለፀ አንድም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም አላየሁም፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን
በፈቃዱ የሰረዘ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች አቡነ ጴጥሮስን ከኦርቶዶክሱ እኩል ነው የሚያከብሯቸው፡፡ ይህ ካመማችሁ
ከበሽታችሁ ታከሙ እንጅ ህመማችሁን ወደ ሌላው አታባዙት፡፡
(፡((› በተለይ ደግሞ የገረመኝ
የስማቸው ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ ጭራሽ …‹‹በተለምዶ አቡነ ጴጥሮስ የሚባሉት….›› ብሎ ጽፎ አየሁ፡፡ ‹‹በተለምዶ›› የሚለው ቃል
ለምን ገባ ? ኧረ አይባልም!!! አለማወቅ ከሆነ… በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት አንድ ካህን ጵጵስና ሲሾም አዲስ የአገልግሎት/የአባትነት
ስም ነው የሚሰጠው፡፡ ከሐዋርት ፣ ከነቢያት ፣ ከሰማእታት ፣ ከጻድቃን ወይም ከሊቃውንት የአንዱ ስም ይሰጠዋል፡፡ የበፊቱ ስሙ
ምንም ይሁን ምን ጵጵስና ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ በአዲሱ ስሙ ነው የሚጠራው፡፡ በቃ !!! ሌላ ትንታኔ ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡
ይሄ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንጅ የማንም ፍላጎትና ልዩ ዓላማ አይደለም፡፡ ቅዱሱ አርበኛ በተሰውበት ቅጽበት ‹‹ብጹዕ አቡነ
ጴጥሮስ›› የሚል የጵጵስና ስም ነበራቸው፡፡ አሁን የሚጠሩት በዚሁ ስማቸው ላይ ‹‹ሰማእት›› የሚል በመጨመር እንጅ የነበራውን
በመሰረዝ አይደለም፡፡ ስለ ጀግንነታውም ‹‹አርበኛው›› የሚል እንጨምርላቸዋለን፡፡ ከዚህ ውጭ የልጅነትና የሰፈር ስማቸውን እየፈለጉ
‹‹ስማቸው ይህ ነው እንጅ አቡነ ጴጥሮስ የሚለው አይደለም›› ማለት አላዋቂነትን ከማሳበቅ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ጵጵስና
ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የቀድሞ ስማቸው/ስሞቻቸው ቀርተዋልና፡፡
›፡) በአጠቃላይ አቡነ ጴጥሮስ
ለኢትዮጵያ ነፃነት የተሰው ኦርቶዶክሳዊ ጳጳስ ናቸው፡፡ የጵጵስና ሥልጣናቸው ቅኝ ገዥን ከመዋጋት አላገዳቸውም፡፡ ዘርና ሃይማኖት
ለይተው ሳይሆን ለአንዲት ሀገር ነፃነት ነው የሞቱት፡፡ እንኳን ሰውን ምድርን እንዳትገዛ ያወገዙ የነፃነት አርበኛ ናቸው፡፡ አቡነ
ጴጥሮስ የሁሉም ሕዝብ ሀብት ናቸው፡፡ እንኳን ክቡራን በሆኑና የየትኛውም እምነት ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውን ይቅርና በምድሪቱም
ጭምር ተከብረው ይኖራሉ፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለቅዱሱ አርበኛ
አቡነ ጴጥሮስ !!!
No comments:
Post a Comment