Sunday, February 21, 2016

‹‹ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን›› !




(መላኩ አላምረው)
‹‹የሕግ ያለህ! ኧረ የዛሬውስ የጉድ ነው ወገኖቼ ! ሰው ለማን አቤት ይላል? ኧረ እባካችሁ አሳልፉኝ ስዕለት አለብኝ !...”››
ሴትየዋ እጅግ በጣም ያመረሩ ይመስላሉ። ሲናገሩ ጉሮሯቸውን ሲቃ ይተናነቀዋል። ዓይኖቻቸውም እምባ አዝለዋል። ጩኸታቸውን ግን ማንም አያዳምጥም። መልስም የሚሰጣቸው የለም።
‹‹ሕግ ሆይ! ወዴት አለህ? ሥርዓትስ ወዴት ተሰደድሽ?...›› ሴትየዋ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መጮሃቸውን ቀጠሉ። እኔም ወደርሳቸው አቅጣጫ እየተጋፋሁ ነው፡፡
ዕለተ ሚካኤል ጠዋት ነበር፡፡ ሰዓት ሳይረፍድብኝ ለትምህርት ለመድረስ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍጥነት በመጓዝ ላይ ነበርሁ። ዕለቱ ወርሃዊ በዓል በመሆኑ በቅ/ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ምዕመናን እንደሚበዙ ብገምትም ከየካቲት 12ሰማዕታት ሐውልት ጀምሮ መንገዱ ይዘጋጋል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበርና ወደ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ ለመግባት 5ኛ በርን ምርጫዬ አደረግሁ። ልክ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልቱን እንዳለፍኩ ጀምሮ ግን አይደለም በፍጥነት ተጉዤ በሰዓቱ ክፍል መግባት ቀርቶ ለመንቀሳቀስም ተቸግርሁ። ከአስፓልቱ የቀኝ ጠርዝ እስከ ዩኒቨርስቲው አጥር ድረስ የጤፍ መጣያ እስኪጠፋ ድረስ በሸቀጣሸቀጦችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም በተላላፊ ሰዎች ተጠቅጥቆ ተሞልቷል።
ሰው ማለፊያ ሲያጣ ወደ አስፓልቱ እየገባ፣ መኪኖቹንም ግራ እያጋባቸው፣ ሾፌሮችም እየተቆጡና ‹‹ክላክስ›› እየነፉ. . . ይህ ሁሉ ደግሞ ከሸቀጣሸቀጥ ግዙን ባዮች ልፍለፋ፣ በሞንታርቦ ከተለቀቁ መዝሙሮችጩኸት ባህታውያንነን ባዮችስብከትጋር ተደማምሮ ለአካባቢው ልዩ ትዕይንትን ፈጥሯል። አንዳንዴ መርካቶን፣ አንዳንዴ መዝሙር ቤቶችን፣ አንዳንዴ ደግሞ የሀብታም ሠርግን (የታክሲዎችን ክላክስ) ያስታውሳል። ውስጤን ሁለት ሀሳቦች ወጠሩት፡ አንደኛው የትምህርት ሰዓቴ መርፈድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስመቼ እንዲህ ይደረጋል? ለምን እንዲህ ይሆናል? ይህን የማስቆም ኃላፊነቱስ የማነው? የሚለው ሀሳብ። ‹‹ወርሃዊ በዓላት በመጡ ቁጥር አብያተ ክርስቲያናት ወደ ገበያ ማዕከልነት ይለወጡ!›› የሚል አዋጅ ወጣ እንዴ? ወይስ እኔ ያልሰማሁት ‹‹ልዩ ዐውደ ርእይ›› ይኖር ይሆን? ይሄኛው ደግሞ ልዩ ነው። መንገድ እንዲህ ሰው መንቀሳቀሻ እስከሚያጣ ድረስ ‹‹በመንፈሳዊ መዝሙርና ስብከት›› እንዲሁም በሸቀጣሰቀጥ ነጋዴዎችና ገዥዎች ሲጨናነቅ አይቼ አላውቅም፡፡ ግሩም ነው መቼም። እሺ ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም የሚፈልጉ ምዕመናን እንዴት ይለፉ?
በርካታ ሐሳቦችን በአዕምሮዬ እያውጠነጠንሁና እንደምንም እየተጋፋሁ በማፍለፍ ላይ እያለሁ ከጫጫታው መሐልሴትዮዋ ‹‹የሕግ ያለህ›› ጩኸት ጎልቶ ተሰማኝ። እዕምሮየን ረበሸው፡፡ በዙሪያቸው ያለው ሰው በመደናገጥም በመገረምም ዓይኑን ወደርሳቸው እያዞረ ያያቸዋል። የሚናገሩት ኃይለ ቃል ውስጤን ነካው። ለትምህርት ክፍለ ጊዜ በሰዓቱ እንደማልደርስ ሲገባኝ ተስፋ ቆረጥሁ። እንዴት አልፌ? በሴትዮዋ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሴትየዋ ንግግር ዙሪያ የተለያየ አስተያየት መስጠት ጀመሩ። አንዳንዱልክ ናቸው ሴትዮዋ። ምን ሕግና ሥርዓት አለ? ሕግ ቢኖር እንዲህ የቤተ ክርስቲያን መሳለሚያ እናጣ ነበር?” ይላል። ሌላው ደግሞቢጨንቃቸው እኮ ነው። ዝም ብለው ቢጋፉና ቢያልፉ ይሻላል። ማን ይሰማኝ ብለው ነው አሁን እንዲህ የሚጮኹት ኤዲያ ! የባቴት ነገር !እያለ ያሽሟጥጣል። አንዳንዱ የባሰበትምእባክዎትን እርስዎም ብሰው አያድርቁን። ሄደው ፖሊስ ጣቢያ አይጮሁም ከፈለጉ?” በማለት የበለጠ ሆድ ያሰብሳቸዋል።
እንደምንም ተጋፍቼ ወደ እርሳቸው ተጠጋሁናአይዞዎት ማዘር እንደምንም ተጋፍተን እንለፈውአልኳቸው።አይ ልጄ... የመጣብን ጉድ ተጋፍተን የምናልፈውም አይመስልም። አቅም ካላችሁ ሞክሩአሉኝ። በንግግራቸው ትንሽ ግራ ተጋባሁናንግግርዎት በደንብ ግልፅ አልሆነልኝምአልኋቸው።ነገርኩህ ልጄ! እኛ ይሄን ችግር የመጋፋት አቅም ያለን አይመስለኝም። ጩኸታችንን የሚሰማም የለም። ቤተ ክርስቲያን ዝም። መንግስትም ዝም። ሥርዓት ጠፋ። አሁን ይሄ ለማን አቤት ይባላል? ሰላማችን እኮ ጠፋ። ሰው ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ፣ መንፈሱን አድሶና ሰላም አግኝቶ ለመመለስ ነው የሚመጣው። ግን ሰላም የት አለ? ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከሚመጣው እኮ ለገበያ የሚመጣው በዛ። ቅዳሴ ከሚያስቀድሰው እኮ የጎዳና ላይ የሞንታርቦ መዝሙር የሚያዳምጠው በዛ። አሁን የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ነበር?” ብለው እኔን አፍጠው ተመለከቱኝ።
ከእኔ መልስ የሚሹ ስለመሰለኝ ደንገጥም ፈራም አልሁናኧረ ልክ ነዎት. . .. . .” ብዬ ያሰብኩትን ሳልናገርተመልከትአሉኝ አንድ ባህታዊ ነኝ ባይን ከበው ወደ ቆሙ ሰዎች እየጠቆሙኝ።ተመልከት እንግዲህ። ሥርዓተ ቅዳሴው በቤተመቅደስ እየተካሄደ ምዕመኑ በሥርዓቱ መሰረት ከካህናቱ ተሰጥኦ እየተቀበለ ማስቀደስ ሲገባው አንድ አወናባጅ መነኩሴ ነኝ ባይ ከቦ ቆሞልሃል፡፡ ደግሞ እኮ እነዚህ የሐሰት ባህታውያን ሰላምን የሚሰብኩ እንዳይመስልህ፤- ጠብን እንጅ።እስኪ ቀረብ ብለህ ስማአሉኝና አብረን ጠጋ አልን።ባህታዊውአነስተኛ የድምፅ ማጉያውን በመጠቀም እንዲህ ሲል ሰማሁና ደነገጥሁ።
ምዕመናን፣ በአሁኑ ሰዓት ካህን ያለ እንዳይመስላችሁ። ሌባ ብቻ ነው።  መንግሥትም ሌባ ነው። ጳጳሳትም ፖለቲከኞች ናቸው። መንግሥት ጳጳሳትን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው. . . የመጨረሻው ዘመን ስለሆነ ድርቁ፣ ረኃቡ፣ በሽታው፣ ጦርነቱ፣ አመጹ፣ መቅሰፍቱ… በዝቷል፡፡ እ… በነገራችን ላይ ውድ ምዕመናን!እጅግ ፈዋሽ የሆነ ከኢየሩሳሌም የመጣ ቅብዓ ቅዱስ› ስላለ እየገዛችሁ፤ ዋጋው ኪስን አይጎዳም፡፡ ለሌባ ካህናት ቦርጭ መሙያ ሙዳዬ ምጽዋት ከምትጥሉ ይልቅ ቅብዓ ቅዱሱን ግዙ፡፡ ከሁሉም በሽታ ትፈወሳላችሁ፡፡ እ… እናም ካህናትን አትመኗቸው... መንግሥትንም አትመኑት… እኛን ባህታውያንን ካልሰማችሁ አትድኑም”… በጣም ገረመኝ። እውነትም ሴትዮዋ ልክ ናቸው። እንዴት ነው ነገሩ ?
እውነትም የሕግ ያለህ ማለት ይህኔ ነው። ይህ ጉዳይ እኮ እንደቀላል መታየት የለበትም። ጋዜጦች ብዙ ፃፉ - ዝም። ሕዝብ በየጎዳናው ምሬቱን ያሰማል - ዝም። በእንደዚህ ዓይነት ግርግሮች በርካታ ሰዎች ሞባይልና ሌላ እቃ እየተሰረቁ ያለቅሳሉ - ዝም። ለመሆኑ እነዚህን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዙሪያ የሚካሄዱ ንግዶችንና ከስርዓት ውጪ የሆኑ የመዝሙርና ባህታውያንጩኸቶችን የማስቆም ኃለፊነቱ የማነው? የቤተክርስቲያን ወይስ የመንግሥት? እስከመቼስ በዚህ መልኩ ይቀጥላል? እስመቼስ ዝም ይባላል? ለመሆኑ ማን ፈቅዶላቸው ነው ወርሃዊ በዓላትን እየጠበቁ ሸቀጥ የሚዘረጉነጋዴዎችየዋህ ምዕመናንን የሚረብሹት?
(፡ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው ጉዳይ እነዚህ በየመንገዱ ሸቀጥ የሚዘረጉ ሰዎች ሠርተው መብላቸውና ጎዳናዎችን እንደአማራጭ መጠቀማቸው ከችግርና ከንግድ ቦታ እጥረት እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ይሄ ሥራቸው የተፈቀደና ሕጋዊ ከሆነ ሥርዓትን ጠብቀውና ከቤተ ክርስቲያኑ ራቅ ብለው ሊደርጉት ይገባል እንጅ አስቀዳሹንና በአጠቃላይ መንፈሳዊ ሥርዓቱን በሚረብሽ መልኩ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም በአግባብና በሥርዓት መሆን አለበት፡፡))
በተለይ በተለይ መዝሙርና የስብከት ካሴት ሻጭ ነን ባዮች በሞንታርቦ ድምፅ በሥርዓት እያስቀደሱ ያሉ ምዕመናንን የሚረብሹበትና ዝም የሚባሉበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በየትኛው ሥርዓትስ ነው ይህ የተፈቀደው ? ሲጀመር ሥርዓትን አያውቁም፡፡ የቅዳሴ ሥርዓትን እየረበሹ ‹‹መንፈሳዊ›› መዝሙርና ካሴት መሸጥ ብሎ ነገር አይገባኝም፡፡ ዘመናዊ ንግድ ነው፡፡
ምንም ፈቃድ ሳይኖራቸው በየመንገዱ እየቆሙ በሕዝቡ ዘንድ መለያየትንና ጥላቻን የሚሰብኩባህታውያን› ነን ባዮችስ ጉዳይ ማንነው የሚመለከተው? ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ማን ሥርዓት ያስይዝ ? መንግሥት ወይስ ቤተ ክህነት ?
ቤተክርስቲያንና መንግሥት ሆይ! እባካችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ የየድርሻችሁን ተወጡ። ለህዝቡ ሰላም አይገዳችሁምን? ቤተ አምልኮና የንግድ ቦታ መለያየት የለበትምን? ፈቃድ የሌላቸው አወናባጆችስ በየጎዳናው የጥላቻና የመከፋፈል ስብከትን ለህዝቡ ያዳርሱ ዘንድ ተፈቅዷልን? ቤተክርስቲንና መንግሥት ድርሻችሁን ለይታችሁ አውቃችኋልን? እውነት ይሄ ጉዳይ ዝም ከተባለ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ታስቦበታል?
መንግሥት ያላት ሀገር ሕግ ማስከበር ካቃታትና ሲኖዶስ ያላት ቤተክርስቲያን ሰባኪዎቿንና ዘማሪዎቿን በሥርዓት ካላሰማራች ማን መጥቶ ሕግና ሥርዓት ያስከብር? ይከብዳልም፤ ይገርማልም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆይ! የመዝሙርና የስብከት ካሴቶች ከሸቀጣሸቀጦች ጋር አብረው ተሰልፈው ሲሸጡ እያያችሁ ለምን ዝም ትላላችሁ? የቤታችሁን ሥርዓት ማን መጥቶ ሊያስከብርላችሁ ነው? ኧረ ይሄ ነገር ያሳፍራል እኮ። መንፈሳዊ አገልግሎትን ለሀብት መፍጠሪያ ለማዋል ሲባል ሥርዓተ ቅዳሴውን በመረበሽ ጭምር በአዋጅ ሲሸጥ ዝም !? ጉድ እኮ ነው። ማስተዋል ይገባናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንናመንግሥትም የሚመለከተው አካል ይህን ጉዳይ ሥርዓት ለማስያዝ ብትነጋገሩ/ብትተባበሩ መልካም ነው እላለሁ።
………..

No comments: