Wednesday, October 5, 2016

እ ው ነ ት ?

(መላኩ አላምረው)
...
ያው የእነርሱ እውነት
ለሌሎቹ ሐሰት
እየሆነ እንጂ...
ሃይማተኞችም
ፖለቲከኞችም
የሚሰብኩት እውነት፡-
ለአንዳንዶቻችን - ለጆሮ አይሰለችም
ያው ለሌሎቻን ፍጹም አይመችም
‹‹እውነት አለ የለም አሁን በዚህ መሐል ?››
ብለህ ብትጠይቀው አንዳንዱ ያማሃል
አንዳንዱም በድፍረት ይሳለቅብሃል !
* * * * *
ያው አንተም ባንተ ቤት የልብህ ውስጥ እውነት
እየሆነ እንጂ ለሌላኛው ሐሰት
እንዳንተ ማን ያውቃል ? እውነትን ተራቆ
ማንስ ሚያስብ አለ ? እንዳንተ ተጨንቆ
ልቡ እንዳንተ ሩህሩህ ይገኝ ይሆን ከሰው ?
እውነትህን በሐሰት ሌላው እስኪከሰው…
* * * * *
የሰው ልጅ ምስኪን ነው ያስባል በልቡ
እውነትና እውቀት ከውስጡ እንደገቡ
አላወቀም እርሱ በሌላኛው ሰፈር
ሐሰተኛነቱ/ማይምነቱ ጎልቶ እንደሚነገር
* * * * *
በትንሽ ሕሌና ስንመረምራት
ልክ እንደ ሃይማኖት…
ሀገር የጋራ ናት - ‘እውነት የግል ናት’
እውነትህን አልነካም - እውነቴን አትንካት
ብለን ብንደመድም
ይሄኛውም እውነት ከቶ አይወደድም፡፡
እና ምን ይሻላል… ?
ሰው እውነቱን ይዞ ዝም ቢል ምን ይላል ?
....ችግሩ…
በሌላኛው ዓለም
ዝም… እውነት አይደለም፡፡
…..›››››››

No comments: