Wednesday, October 5, 2016

መፍትሔ የምናመጣው ‹‹ስለተናገርን›› ሳይሆን ‹‹ከተደመጥን ብቻ›› ነው፡፡



(መላኩ አላምረው)
-----//-----
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለአንድ ሬዲዮ ጣቢያ (ካዳ ውስጥ) በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ብሏል፡፡
‹‹የሚናገሩ ሳይሆን የሚደመጡ የሃይማትም ሆነ የሀገር መሪዎች መጥፋታቸው ነው ችግሩን ያባባሰው፡፡ እየተናገርህ ነው ማለት እየተደመጥህ ነው ማለት አይደለም፡፡ የመናገር መብት የመደመጥን ሥልጣን አይሰጥም፡፡››
...
ዲ/ን ዳንኤል ያለውን ሐቅ ማስተዋል ወቅታዊ መፍትሔ ነው፡፡ አሁን የተቸገርነው የምንናገር ሁሉ የምንደመጥ እየመሰለን ነው፡፡ መናገራችንን እንጅ የተናገርነው ነገር በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው አናስብም፡፡ ሕዝቡ ‹‹ለእናንተ ወሬ መስሚያ ጆሮዬ ጥጥ ነው›› እንዳለን አናስተውልም፡፡ ብቻ መናገር የፈለግነውን እንናገራለን፡፡ መናገር ስለምንችልና የመናገሪያ መድረኩም በእጃችን ስለሆነ ብቻ እንናገራለን፡፡ መሪ ስለሆን ብቻ የምንናገረው ሁሉ የሚደመጥና የሚተገበር ይመስለናል፡፡
ሐቁ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ምን አልባትም የምንናገረው ሁሉ እተደመጠና እታመነ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹‹መሪ›› መናገር ያለበት የሚመራውን ሕዝብ ድምጽ መሆን ሲገባው ‹‹የራሱን ሐሳብ›› ብቻ ከሆነ ስለሰነባበተ ሕዝቡ ሰልችቷል፡፡ ሕዝቡ ‹‹እየመራንህ ነው›› የሚሉትን ሁሉ የሚሰማ ቢሆንማ ኖሮ ለምን እንዲህ አለመደማመጥ ነገሠ ? አሁን እኮ ካለመደማመጥም አልፎ መናናቅና መሰዳደብ ተጀምሯል፡፡   
...በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ሕዝቡ ‹‹እገሌ ምን አለ›› ብሎ የሚዳምጣቸውና በሚናገሩትም የሚምንባቸው በንግግር ማሳመር ሳይሆን በተግባር የተመሰከረላቸው መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ የሀገር መሪዎች ይቅርና... ቃላቸው የሚከበር፣ ከእውነት ጋር ቆመው ጥፋተኛውን የሚገሥጹ፣ መክረው የሚመልሱና አውግዘው የሚለዩ ቁርጠኛ የሃይማኖት አባቶች ቢበዙልን (በቁራቸው ልክ ቢሆኑ) ኖሮ... እንዲህ ግራ ተጋብተን ባልቆምን ነበር፡፡ ለሕሊናው የሚያድርና ለእውነተኛ መፍትሔ የሚተጋ መሪ ጠፋና ከዚህ ደረስን፡፡
ቀጣይስ ? አሁንም ችግሮችን በመሸፋፈን እንቀጥላለን ወይስ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ለመታረቅ ወስነናል ? ምን እስኪሆን ይሆን የሚጠበቀው ? ይሄ ‹‹ከአፈርሁ አይመልሰኝ›› ጉዞ የት ሊያደርሰን ይሆን ?
አሁን ነገሮች ሁሉ ተባብሰው ወደ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሳንገባ ወደ መደማመጥ ብሎም ወደ እርቅና ይቅርታ መምጣት አለብን፡፡ ለራሳችን ክብርና ስም ብቻ ከመቆም አንዳንዴ ለሀገርም እናስብ፡፡ መደመጥ ከፈለግን እናዳምጥ፡፡
ምንም ችግር ውስጥ ብንሆንም አሁንም ‹‹መሸ እንጅ አልጨለመም›› ብዬ አምናለሁ፡፡ ምሽቱ ግን በፍጥነት ወደ ድንግዝግ ጨለማ እየገሰገሰ ነው፡፡ ይህኔ ቆም ብለን የብርሃን ምንጮችን ካልፈለግን ወደ ድቅድቁ መግባታችን የሚቀር እንዳይመስለን፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከገባን ደግሞ ሁላችንም መንገዱ አይታየንም፡፡ መውጫ ጠፍቶ የጨለማው ንጉሥ እራት ሆነን እንዳንቀር..... ይህኔ ብርሃን ሳለ አማራጭ መንገዶችን እንይ፡፡ በብርሃን ያዩት መንገድ በጨለማም አይጠፋምና !!!
መንገዱን ሁሉ በግልጽ የሚያሳየው ብርሃን ግን... መደማመጥ ብቻ ነው፡፡ በግልጽ ተነጋግረን ካልተደማመጥን አንግባባም፡፡ ካልተግባባን ደግሞ... መፍትሔ ብሎ ነገር አይታሰብም፡፡ በራሳችን መንገድና ስሌት ብቻ እያሰብን የምናመጣው መፍትሔም እያመጣው ያለውን ለውጥ እታዘብነው ነው፡፡ ከስሜታነትና ከእልኸኝነት ወጥተን በአዕምሯዊነት እንቁም፡፡ ከየቆምንበት ጽንፍ ተንቀሳቅሰን ወደ መሐል እንምጣና በትክክል ‹‹ከሕዝቡ ጋር›› እንነጋገር፣ እንደማመጥ፡፡ የመደመጥ እድሉን ካገኘንና እርሱንም ካመጥነው መፍትሔው በሕዝቡ እጅ ነው፡፡
-----//-----

No comments: