Wednesday, October 5, 2016

‹‹››-----የጠፋውን.............ፍለጋ-----‹‹››



(መላኩ አላምረው)
-----‹‹››-----
‹‹እኔ እምልዎት መምሬ ለይኩን... ዘንድሮ የሚጠፋ ነገር የበዛው ዓለም መጥፊያዋ ደርሶ ይሆን እንዴ ?›› አለ አከራያችን ጋሽ ጣሰው ‹‹የሰንበት ቡና ጠጡ›› ተብለን እንደተሰበሰብን፡፡ ‹‹የዓለም መጥፋት›› የሚለው ሐረግ ሁላችንም ሳያስደነግጠን አልቀረም መሰል ዝምታ ሰፈነ፡፡ መምሬም ዝም እኛም ዝም፡፡
ቡና እየጠጣን ነው፡፡ መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም - ዕለተ ሰንበት፡፡
በጋሽ ጣሰው ቤት የተሰበሰብን የቡና ጠጭዎች ዝርዝር፡-
ጋሽ ጣሰውና ባለቤታቸው ወ/ሮ ትርሃስ፣ ጎረቤታቸው መምሬ ለይኩን፣ ከቦሌ ለእንግድነት የመጣችዋ የእትዬ ትርሃስ የእህት ልጅ (ኤኒሃና ትበናላለች - ትርጉም በራሳችሁ)፣ ፈላስፋው ጣሴ፣ እኔ እና 8ኛ ክፍሏ የእነ ጋሽ ጣሰው የመጨረሻ ልጅ ይመኙሻል፡፡
‹‹ምነው ዝም አላችሁ ?›› ጋሽ ጣሰው ንግግሩን ቀጠለ፡፡
‹‹ምን እንበል ልጅ ጣሰው... ደርሰህ የዓለም መጨረሻን፣ ፍጻሜ ዘመንን ስታነሳብን እኮ ደነገጥን...›› መምሬ ለይኩን ሳቅ እያሉ መለሱ፡፡
‹‹ስለመጥፋት ካነሳን አይቀር ለምን የጠፉ ነገሮችን በመዘርዘር ጨዋታችንን አንጀምርም ? በተለይ ባለፈው ዓመት ብዙ የጠፉ ነገሮች ነበሩ... እንዲያውም በእኔ አሰያየም 2008 ዓ.ምን ‹የመጥፋ ዓመት› ብየዋለሁ... ምን ያልጠፋ ነገር አለ......›› ፈላስፋው ጣሴ ቀጠለ፡፡
ትንሽ ተሳሳቅን፡፡ ‹‹በሉ እግዲህ እንዘርዝረዋ... ጨዋታችን ድብልቅልቅ ብሎ የጠፉ ነገሮች እንዳይዘነጉ በየተራ እንናገር›› መምሬ ለይኩን ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
እኔ ‹‹መጥፋት›› የሚለው ቃል ከተነሳ ጀምሮ መስከረም እንደጠባ የጠፋውን ስልኬንና ከስልኬ ጋር የጠፉ መረጃዎቼን እያሰላሰልሁ ነበር፡፡ እናም የመጀመሪያውን የመናገር ዕድል ለማግኘት እጀን አወጣሁ፡፡ ዕድሉ ተሰጠኝ፡፡
‹‹ለምሳሌ የእኔ ስልክ ጠፍቷል፡፤ ያውም ብዙ የጽሑፍ መረጃዎቼን ይዞ ነው የጠፋው፡፡ የጠፋውም ወደ ሰሜን ማለቴ ወደ ባህር ዳር ለእረፍት በሄድሁበት አጋጣሚ ነበር...›› አልሁ፡፡
ጋሽ ጣሰው ቁጣና ሳቅ በተቀላቀለበት ንግግር... ‹አይይይ... አሂሂሂ... እ.... ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን› አሉ፡፡ እኛ ስለሀገራዊ ጉዳዮች መጥፋት እንወያይ አልን እንጅ ስለግለሰብ ንብረቶች መጥፋት አልን እንዴ ? ወጣን ?››
በሐፍረት ዝም አልሁ፡፡ ሳስበው ደግሞ ስልኬ የጠፋው መስከረም እንደገባ እንጅ 2008 ላይ አልነበረም፡፡ የድሃ ነገር... እውነትም ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን!›› ዝምም፡፡
ከእኔ የአፍታ ዝምታ በኋላ... መምሬ ለይኩን ጨዋታውን አስቀጠሉት፡፡
‹‹ልጅ ጣሰው ልክ ብለሃል፡፡ ከተወያየን አይቀር በዚህ ወቅት መወያየት ያለብን ስለ ሀገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የማስተውለው የእኛ ችግር ይሄ ነው፡፡ ብዙ ሀገራዊ ነገሮች ሲጠፉ ምንም አይመስለንም፡፡ ነገር ግን የእኛ ትቂት ንብረት ስትጎዳ ወይም ስትጠፋ አብዝተን እንጮሃለን፡፡ ለሀገራዊ ሀብቶች መጥፋት ምንም ትኩረት ሳንሰጥ ለእኛ አንዲት ቁስ መጥፋት ግን ሀገር እናዳርሳለን፡፡ ዳገት ወጥተን ቁልቁለት ወርደን የምንፈልገው የእኛ ነገር ሲጠፋ እንጅ... ሀገር ስትጠፋ አይደለም፡፡ እናም... ትኩረታችንን ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እናድርግ፡፡››
‹‹ልክ ነዎት መምሬ፡፡ እንዲያውም ልጅ መላኩ ሰሜን - ባህር ዳር ሲል ያስታወሰኝ ከሰሜን አካባቢ ጠፍቶ የተገኘውን ራስ ዳሽንን ነው፡፡ መቼም ሀገራዊ ሀብት ካልን ራስ ዳሽንን ሚያክል ቅርስ አለ ብዬ አላምንም፡፡››
‹‹አ ሂ ሂ... ህምም... ሰው ወዶ አይስቅም መቼም፡፡ ቀልዱን ብንተወው አይሻልም ልጅ ጣሰው ?›› አሉ መምሬ እየሳቁ፡፡
‹‹የምን ቀልድ አመጡ መምሬ ? እውነቴን እኮ ነው፡፡ ራስ ዳሽን ካርታ ላይ ጠፍቶ ሲፈለግ ሲፈለግ... አሁን ሰሞኑን ነው አሉ የሆነ መጽሐፍ ላይ ወደ ሰሜን ሸሽቶ የተገኘው›› አሉ ጣሰው፡፡ ሁላችንም ተሳሳቅን፡፡
ፈላስፋው ጣሴ ጣልቃ ገባ፡፡
‹‹ነገሩ ያስቃል፡፡ መቼም በ2008 ያልጠፋ የለም፡፡ ፈተናው ጠፍቷል፡፡ ሕፃናት ጠፍተዋል፡፡ ሰላም ጠፍቷል፡፡ አንድነት ጠፍቷል፡፡ ብቻ ብዙ ነገር ጠፍቶብናል፡፡ ግን በእኔ እይታ... መፈለግ ያለብን ከነገሮች መጥፋት ጀርባ ያለውን ‹አጥፊ› ነው፡፡ ነገሮች ያለ አጥፊ አይጠፉምና›› አለ ጣሴ አንዴ ጋሽ ጣሰውን አንዴ መምሬ ለይኩንን እያየ፡፡
‹‹ጥሩ ሐሳብ አመጣህ ልጄ...›› መምሬ ለይኩን ቀጠሉ፡፡ ‹‹ልክ ብለሃል፡፡ በአጠቃላይ በሀገር ላይ የብዙ ነገሮች መጥፋት ምክንያቱ የሀገር ፍቅርና የሥነ ምግባር መጥፋት ነው፡፡ ከነገሮች መጥፋት ጀርባ ያለው ዐቢይ ጉዳይ የሀገራዊና ሕዝባዊ ፍቅር መጥፋቱ ነው፡፡ ሥነ ምባባር ጠፍቷል፡፡ ሀገራዊ ስሜት ጠፍቶ ጎጠኝነት ነግሷል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ጠፍቷል፡፡ መደማመጥ፣ መከባበር፣ መተዛዘን... ጠፍቷል፡፡ ለወገን ማሰብና መጨነቅ ጠፍቶ በቦታው ራስ ወዳድነት ነግሶበታል፡፡ እና በዚህ ሁሉ መሐል ብዙ ሀገራዊ ነገሮች ቢጠፉ ምኑ ያስገርማል ? ባይጠፉ ነው እንጅ የሚገርመው፡፡›› መምሬ ዓይናቸው እንባ አቀረረ፡፡
‹‹እውነትዎትን ነው፡፡ አሁን ገና የልቤን ተናገሩ›› አሉ እማማ ትርሃስ፡፡
‹‹እኔም በመምሬ እስማማለሁ›› ፈላስፋው ጣሴ ቀጠለ፡፡ ‹‹መታየት ያለበት፣ መፈለግም ያለበት ይህ መምሬ ያሉት ‹መጥፋት› ነው፡፡ ሀገርን እንደ ሀገር የሚያኖራት፣ ሕዝብንም እንደ ሕዝብ የሚያተሳስረው ዋናው ሀገራዊ ስሜትና ሕዝባዊ ፍቅር ከጠፋ... ሌሎቹ በሙሉ መጥፋታቸው አይቀርም፡፡ ሀገርም መጥፋቷ አይቀርም፡፡ ፍቅር ጠፍቶ እያለ የሚፋቀርን ሕዝብ መፈለግ፣ ሀገራዊ ስሜት ጠፍቶ ሳለ ጠንካራ ሀገርን መጠበቅ፣ ሃይማኖት በሌለበት ሀገር ጻድቃን ሃይማተኞችን መሻት... ከንቱ ድካም ነው፡፡››
‹‹ድንቅ ንግግር ነው፡፡ እስማማለሁ›› አሉ ጋሽ ታሰው፡፡
‹‹እኔም እስማማለሁ›› አልሁ እኔም በመጨረሻ፡፡
‹‹ማነሽ... ኤኒሃና... ነው ያሉት ስምሽን ? አንችስ ሐሳብ የለሽም እንዴ ? ይመኙሻልስ ያው ሕፃን ሆና ነው.... አንች ግን እንግዳ መሆንሽ ነው ዝም ያልሽው ?›› አሉ መምሬ ለይኩን የቦሌዋን እንግዳ፡፡
ኤኒሃና ተናገረች፡፡ ‹‹ሶሪ ዝም አልሁ አይደል፡፡ ታውቃላችሁ ግን..... ሪሊ... ከሁሉም በላይ የገረመኝ የተራራው መጥፋት ነው፡፡ ‹ሃው ኤ ማውንቴን ካን ዲስአፒር ? አይ ካንት ቢሊቭ ኢት!› ባጭሩ የራን ዳሽን መጥፋት ‹ሼም› ነው፡፡››
በኤኒሃና ንግግር ተሳሳቅን... በረካው ተቀዳ፡፡ ደህና ሰንብቱ፡፡ ሳምታዊው የጋሽ ጣሰው ቤት የቡና ጠጡ ጨዋታ ይቀጥላል፡፡

No comments: